በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለኢትዮጵያ ቡና የሚጫወተው አቤል ከበደ ቡድናቸው በሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም ሆነ ከውጤት አንፀር እያስመለከተ ያለው ነገር የሚያበረታታ እና ይበልም የሚያሰኝ እንደሆነ ከሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽን ሰጥቷል፡፡
በባህርዳር ከተማ ላይ ለተጀመረው የ12ኛው ሳምንት የሊግ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናን ለመግጠም ከተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ የሆነው አቤል ከሀትሪክ ጋዜጣ ጋር ያደረገው አጠቃላይ ቆይታም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ላይና በጅማ ከተማ ላይ ባደረገው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ምርጥ ነበር ማለት ይቻላል…..ወይንስ?
አቤል፡- በጣም ምርጥ ነው እንጂ! በሁለቱም ከተሞች ላይ ከውጤት አንፃርም ሆነ በሜዳ ላይ ከነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ አኳያ አሪፍ ጊዜንም አሳልፈናል፤ ይበል የሚያስብል አበረታች ውጤትንም አስመዘግበናል፤ በዛ ላይ ደግሞ አንድም ተጨዋች ከቡድናችን ስብስብ ውስጥ ጉዳትን ያስተናገደም ስላልነበር ይሄ ባህርዳር ከተማ ላይ ለምናደርጋቸው ቀጣይ ጨዋታዎቻችን የሚጠቅመን ሆኖ ስላገኘነውም ለእኛ መልካም ዜና ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ያለፉት ጊዜ ጨዋታዎቻችሁ በጣም የተቆጫችሁበት ነገር አለ?
አቤል፡- አዎን፤ እኛ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ጥሩ ሆነን ሳለ አለአግባብ ነጥብን የጣልንባቸው ግጥሚያዎቻችን አሁንም ድረስ የሚያስቆጩን ናቸው፤ በእነዛ ጨዋታዎች ቡድናችን ማሸነፍ እየቻለ ነበር ሽንፈትን ያስተናገደው እና በሁለቱ ግጥሚያ ላይ ነጥብን ይዘን ብንወጣ ኖሮ ቡድናችን በመሪነት ደረጃም ላይ ይቀመጥ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- አስቆጭቶናል የምትላቸው ጨዋታዎች የትኞቹ ነበሩ….?
አቤል፡- በአዲስ አበባ ስታድየም ከሐዋሳ ከተማ ጋር ያደረግነው እና በጅማ ዩንቨርስቲ ሜዳ ላይ ከወላይታ ድቻ ጋር ያደረግነው ነው፤ በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ የኳስ ነገር ሆኖና አልፎአልፎ በሚያጋጥም አይነት ሽንፈት ስኬቶቹን ልንይዝ ባንችልም እንደ አመጣቱ ግን ውጤቱን ልንቀበለው ነው የቻልነው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ወደ ባህርዳር ከተማ ሲያመራ ከባለፉት ጨዋታዎቹ የተማራቸው ነገሮች አሉ?
አቤል፡- አዎን፤ ያም ሆኖ ግን መጀመሪያ ላይ እኛ ሁሌም ትምህርትን የምንወስደው ከባለፉት በርካታ ጨዋታዎቻችን ሳይሆን ካለፈው አንድ ግጥሚያችን ብቻ ነው፤ በየጨዋታውም ነው ስህተቶቻችንን በመማር እዚህ ደረጃ ላይም የደረስነው፤ ለምሳሌ ባለፈው ግጥሚያ ሲዳማ ቡናን 5-0 አሸንፈናል፤ በማሸነፍ ውስጥ ክፍተት እንዳለ ስለምናውቅ ከሀዲያ ከተማ ጋር ላለብን ጨዋታ የተዘጋጀነው ከእዚህ ጨዋታ በመነሳት ነው፤ የእኛ ቡድን ሁሌ የሚመራውም በእዚህ መልኩም ነውና እየሄድንበት ባለው ጉዞ እየተሻሻልንም ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ከሌሎች ቡድኖች አንፃር እየተከተለ ያለው አጨዋወት ማራኪ እና ሳቢ ነው ማለት ይቻላል?
አቤል፡- ይሄ በሜዳ ላይ የሚታይ ስለሆነ አይቶ መፈረድ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዋንጫውን የማንሳት እድሉ የቱን ያህል ይመስልሃል?
አቤል፡- የሊጉ ፍፃሜ እኮ ገና ነው፤ መቼስ የአንደኛው ዙር ተጠናቀቀ፤ ከፊታችን በርካታ ጨዋታዎችም አሉ፡፡ ይሄን ካልኩ ቡድናችን በአሁን ሰዓት ከያዘው ጥሩ ውጤትና በሜዳ ላይም ከሚከተለው የጨዋታ እንቅስቃሴ አንፃር የውድድር ዓመቱ ሻምፒዮና ለመሆን ከኮቺንግ ስታፉ ጋር እየሰራንም በመሆኑ ዘንድሮ ጥሩ እና ጣፋጭ የሚባል ውጤት የምናስመዘግብ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ምን የተለየ ነገርን ተመለከትክ?
አቤል፡- ከከዚህ በፊቱ የሊግ ውድድር አንፃር ግጥሚያዎቹ በቶርናመንት ደረጃ ከተሞች እየተመረጠላቸው መካሄዱ ለየት ብሎብኛል ይሄን ነው በዋናነት የተመለከትኩት፡፡
ሀትሪክ፡- በእዚህ መልኩ ውድድሩ መካሄዱን ወደድከው?
አቤል፡- በጣም፤ በተለይ ደግሞ ለእኛ ኢትዮጵያ ቡናዎች መልካም ነገርም ነው እየሆነልን ያለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከምን አንፃር?
አቤል፡- የሊግ ውድድራችንን ከእዚህ በፊት በደርሶ መልስ ጨዋታ በምናደርግበት ወቅት ካለው ከፍተኛ ጫና አንፃር ክልል ሜዳዎች ላይ ተጉዘህ ጨዋታን ማሸነፍ በጣም ከባድ ነበር፤ ብዙ ጊዜም ከቻልክ ነጥብ ተጋርተህም ለመመለስ ነበር የምትጓዘው፤ አሁን ግን በአንድ ከተማ ላይ ቢያንስ ለአንድ ወራት እዛው በመቀመጥ እና ሞቃት እና ከባድ የሆነውን የአየር ንብረትንም በመላመድ ያለምንም ጫናና በተለይ ደግሞ በኮቪድ ወረርሽኝ የተነሳም ያለ ብዙ ደጋፊም እየተጫወትን ያለበት ሁኔታም ስላለ፤ እንደዚሁም ግጥሚያው በዲ.ኤስ.ቲ.ቪም በቀጥታ እየተላለፈ ያለበት ሁኔታም ስለተፈጠረ ጨዋታዎቹ እየተመረጡ ባሉ ከተሞች ላይ መካሄዱ ብዙ ነገሮችን እያቀለለልን ይገኛል፤ ቡድናችን ፈረሱም ሜዳውም ይኸው በሚል ሁኔታም እግር ኳሱን በጥሩ መልኩ እየተጫወተውም ይገኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ቤት ኪንጉ ላይ የቱ ተጨዋች ጎልቶ ወጣብህ?
አቤል፡- የእኛው ተጨዋች አቡኪ ነዋ! እሱ በየጨዋታው ጥሩ ነገርን እያሳየ ይገኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በቤት ኪንጉ ዘንድሮ ስኬትን እያስመዘገበ ካለው ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነገ የምታደርጉት ጨዋታ በጣም ይጠበቃል፤ ማን? ጨዋታውን በድል ይወጣል?
አቤል፡- ሁሌም የእኛ ጨዋታ የሚጠበቀው ከሀዲያ ሆሳዕና የምናደርገው ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ቡድኖችም ጋር የምናደርጋቸው ናቸው፤ የነገውን ፍልሚያ በተመለከተ ለእነሱ ብለን የተዘጋጀነው ነገር የለም፤ ለሁሉም ቡድኖች እኩል ትኩረትንም ነው የምንሰጠው፤ ተጋጣሚዎቻችንንም እናከብራለንና ሀዲያን አሸንፈን ለመውጣት በሙሉ መንፈስም ዝግጁ ሆነናል፡፡
ሀትሪክ፡- አቤል ዘንድሮ ይለያል?
አቤል፡- ስለራሴ እንዲህ ማለትን አልፈልግም፤ እናንተ አይታችሁኝ ፍረዱ፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና በእዚህ ዓመት ምን ልትሰራለት ዝግጁ ነህ?
አቤል፡- ኢትዮጵያ ቡና ህዝባዊ ክለብ ከመሆኑ የተነሳ በቀጣይ ጊዜ የቡድኑ ጨዋታዎች እኔ ለእዚህ ለምወደው ቡድኔ ማድረግ የምፈልገው ከዚህ በፊት ከነበረኝ አቋም አንፃር የተሻለ የሚባል ጥቅምን ሰጥቼው እና ታሪክንም ሰርቼ ነው ማለፍን የምፈልገው፤ በተለይ ደግሞ ከቡድኑ ጋር ሻምፒዮና መሆንንም እፈልጋለውና ይሄ ቢሳካልኝ በጣም ነው ደስተኛ የምሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በዲ.ኤስ.ቲቪ በመተላለፉ ብዙዋኑ እየተመለከታችሁ ነው፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
አቤል፡- ለእኛ ከዚህ ቀደም በእግር ኳሱ ካሳለፍነው ቆይታችን አንፃር እነዚህ ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭትን አግኝተው መተላለፋቸው በጣም አሪፍ ነው የሆነልን፤ የሀገራችን የሊግ ጨዋታዎች በዲ.ኤስ.ቲ.ቪ ተላለፉ ማለት ተጨዋቹ በኳሱ ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስና ከሀገር ወጥቶም ለመጫወት እንዲችል እንዲያስብ እና በውስጡ ያለውን እምቅ አቅምም አውጥቶ እንዲጫወትም ያደርገዋል፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ስለ አንተ ጥሩም ሆነ ጥሩ ያልሆነ ችሎታህም የሚፈረድብህ በሁሉም የኳሱ ህብረተሰብ ውስጥ አቋምህ /ፐርፎርማንስህ/ በደንብ እና በቀጥታም ታይቶ በመሆኑ ይሄን እድል ሁላችንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- በቤት ኪንጉ አቤል እና ጎልን መቼ ያገናኛቸዋል?
አቤል፡- ለኢትዮጵያ ቡና ስጫወት ሁሌም ወደ ሜዳ የምገባው ቡድኔን ለአሸናፊነት እንዲበቃ ከሚያስችሉት ነገሮች ውስጥ ሁለቱን ማለትም ጎል ማስቆጠርንና ለቡድኔም ጥሩ ተጫውቼ ለጓደኞቼ የጎል ኳስንም ስለማቀብልበት ሁኔታ ነው የማስበው፤ ጎል ማስቆጠርን በጣም እፈልጋለው፤ አንዴ በሩ ከተከፈተልህም ደግሞ ሌሎች ጎሎችንም ልታስቆጥር ትችላለህና ዘንድሮ ይሄን እየጠብቅኩኝ ነው፤ ለእስካሁኑ ግን ጎል ማስቆጠሩ ላይ አንድአንዴ ሊጠምብህም ስለሚችል አላስቆጠርኩም ብዬ አላዝንም፤ ለእኔ ከሁሉም በላይ የሚያሳስበኝም ቡድናችን ግጥሚያዎችን አሸንፎ ስለሚወጣበት መንገድም ብቻ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና እየተከተለ ስላለው አጨዋወት፣ ስለ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እና ስለ ኮቺንግ ስታፋችሁስ ምን የምትለው ነገር አለ?
አቤል፡- አጨዋወታችንን በተመለከተ የልምምድ ሜዳው ላይ ሁሌም ከምናደርጋቸው ያለፉ አንድ አንድ ጨዋታዎቻችን በኋላ በታዩ ክፍተት ጎናችን ላይ ራሳችንን ለማረም የምንሰራቸው ታክቲኮች ስላሉና እነዛም ምክንያታዊ የሆኑ ነገሮችም ስለሆኑ በእዚህ መልኩ የምንከተለው አጨዋወት በጣም ተመችቶኛል፤ በእዚህ አጨዋወት ውስጥም አይደለም አሸንፈን ተሸንፈን እንኳን የሚያበረታታንን እና ደስተኛ እንድንሆንም የሚያደርገንን የኮቺንግ ስታፍንም ለማግኘት መቻላችን ለቀጣይ ጥንካሬያችን ብዙ የሚጠቅመን ነገርም ይኖራናልና ይሄን በተለየ መልኩ ቡድናችን ውስጥ አይቼዋለው፡፡ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን በተመለከተ በእስካሁን የሀላፊነቱ አንድም ቀን በእኛ ላይ ጫና ፈጥሮብን አያውቅም፤ እግር ኳስን በእውቀትም ነው በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብንም ምክንያቶችን ጠቅሶ እያሰለጠነን የሚገኘውና ለእሱም ሆነ የእሱን አስተሳሰብ እየተከተሉ ላሉ የኮቺንግ ስታፎች ምስጋናዬን ልገልፅላቸው እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?
አቤል፡- ኢትዮጵያ ቡና በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እየሄደበት ያለው ጉዞ ጥሩ እና አሪፍ ነው፤ ከመሪው ክለብ ፋሲል ከነማም በነጥብ ብዙም አልራቀም፤ ይህን ለመመልከት ስለቻልንም ባህርዳር ላይ የምናደርጋቸውን ቀጣይ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብን ለማስመዝገብ ከቻልን ከአሁን የተሻለ እና ወደ ሻምፒዮናነቱም ዋንጫ እንድናመራም የሚያንደረድረን ስለሆነ ለዛ እየተዘጋጀን ነው፤ የእዚህ ዓመትን ዋንጫ እንድናነሳም የፈጣሪ እርዳታ ይጨመርበት፡፡
አስተያየት ይስጡ