የእግርኳስ ህይወቱ እየጨመረ የመጣ ነው ….. በከፍተኛ ሊግ ለሀላባ ከተማ በመጫወት የከፍታ ጉዞውን የጀመረው እንግዳችን ሁለት አመት ከተጫወተ በኋላ በፕሪሚየር ሊጉ ለሚጫወተው ድሬዳዋ ከተማ ፊርማውን አኖረ …ጉዞውን ቀጥሏል … ለድሬዳዋ ከተማ ሁለት አመት ከተጫወተ በኋላ የአሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይሌው ጅማ አባጅፋር አስፈረመው አንድ አመት ተጫወተ …ከጅማ አባጅፋር ጋር የመጀመሪያ የሊግ ዋንጫውን አንስቶ ዋንጫ የቀማውንና ረጅም አመት /6 ዓመት/ ማሊያውን የለበሰለትን ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቀለ … ከፈረሰኞቹ ጋርም ሁለት የሊጉን ዋንጫዎች ደጋግሞ አነሳ…እንደ አጠቃላይ ባለፉት 7 አመታት ሶስት የሊግ ዋንጫዎችን ከፍ አድርጓል….. እንግዳችን የቀኝ መስመር ኮሪደር ባለሟሉ ሄኖክ አዱኛ… በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከታችኛው ሊግ እስከ ዋናው ፕሪሚየር ሊግ የቀኝ መስመር ኮረደር ላይ የተንፈላሰሰው ሄኖክ የከፍታ ጉዞውን ጨምሮ ዘንድሮ ያደገውና በግብጽ ሊግ የሚጫወተውን ሃራስ አልሁዳድን ለመቀላቀል ከቀናቶች በኋላ ዝውውሩን ለማጠናቀቅ ወደ ካይሮ ያቀናል … ሃራስ አልሁዳድ ድንበር ጠባቂ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ተጨዋቹ የመከላከል መስመሩን ድንበሩን ሊያጠናክር ተዘጋጅቷል…. ለሀትሪክ ድረገጽ ባልደረባው ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቃለምልልሱን የሰጠው ሄኖክ አዱኛ ለቀረቡለት ጥያቄዎች በግልጽነት ምላሹን ሰጥቷል
ሀትሪክ :-በዚህ ሰአት እንደ ሄኖክ አዱኛ ደስተኛ አለ..?
ሄኖክ:-/ ሳቅ በሳቅ/ ደስ ብሎኛል ብቻ …
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ :– ፕሮፌሽናል ተጨዋች የመሆን ዕድሉን በማግኘትህ እንኳን ደስ አለህ….?
ሄኖክ :- አመሰግናለሁ … ከዚህ በፊት እፈልገው የነበረውን እድል ስላገኘሁ ደስ ብሎኛል ….አንድ ሰው ያለመውን ሲያገኝ በጣም ያስደስታልና ደስ ብሎኛል
ሀትሪክ :- ወደ ግብጽ የመጓዙ ሂደት ምን ይመስላል..?
ሄኖክ:- መጀመሪያም ህልሜም ከሀገር ወጥቶ መጫወት ስለነበር እድሉን ሳገኝ አይኔን አላሸሁም እንጂ ሀገር ውስጥ ካሉ ትልልቅ ክለቦች ጋርም ና እኛ ጋር ተጫወት የሚል ጥያቄ ቀርቦልኝ ግንኙነት ጀምሬ ነበር በርግጥ ባይሳካ ሀገር ውስጥ የመጫወት ሰፊ እድል ነበር…አሁን የጨረስኩት ክለብ ሃራስ አል ሁዳድ ይባላል ….ከእሱ በፊት ደግሞ ሽመልስ በቀለ የተጫወተበት “ፔትሮጄትና መሃላ” ከተሰኙ ክለቦች ጋር ግንኙነት ነበር የእነሱ ባለመሳካካቱ ፊቴን ወደዚህ ክለብ አዙሬ ተሳክቷል…ከታችኛው ሊግ ያደገ ቡድን ነው የቪዛ ፕሮሰሱ ተጀምሯል … በቀጣዩ 10 ቀናት ውስጥ ወደ ካይሮ እጓዛለሁ ብዬ አስባለሁ… እዚያ ካለው እንደ ወንድሜ ከማየው አቤል ያለው ጋር እንነጋገራለን ስለ ሊጉ ጥሩ ጥሩ መረጃ ይሰጠኛል.. በቅዱስ ጊዮርጊስ አምስት አመት ተኩል ያህል አንድ ክፍል ውስጥ ነው ያሳለፍነው … ክለቡ አራስ አልሁዳድ ከታች አድጎ የመጣ ቡድን ነው ስምምነቱን ጨርሼ የጤና ምርመራ አድርጌ ኮንትራቴና ጥቅማ ጥቅም ላይ እደራደራለሁ
..በኔ በኩል ገና አዲስ ክለብ እንደ መሆኑ ረዘም ያለ ሳይሆን አጠር ያለ ኮንተራት እንዲሰጡኝ ነው የምፈልገው ግቤ እዚያ አይደለም … ተሻግሬ መጫወት ትላልቅ ክለብ መግባት እፈልጋለሁ… ብቻዬን እሄድና አመቻችቼ በቀጣይ ደግሞ ቤተሰቤን እወስዳለሁ
ሀትሪክ :- ፈረሰኞቹ ጋር ኮንትራትህን የማደስ ዕድሉ ነበረህ ..?
ሄኖክ:- የውጪው ዕድል ባይሳካ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመቅረት ዕድሉ ነበረኝ… ፍላጎቴም ነበር በግለሰቦች ምክንያት ተገፍቼ የምወደውን ክለቤን ለቅቄ ወጥቻለሁ የሰሩት ነገር ስለነበር እኔም ጉዳዩን ስለሰማሁ ጠርተው አላናገሩኝም ከምወደው ቅዱስ ጊዮርጊስ የለቀቅኩት ተገፍቼ ነው ደጋፊው ደግሞ ይህን አያውቅም ይሄ ይሆናል ብዬ ባለመጠበቄ ቅር ብሎኛል አቶ አብነትና ደጋፊው ለኔ ባላቸው አክብሮት ደስተኛ ነኝ እኔም ለነሱ ትልቅ ክብርም አለኝ…. ቤቴም የቆየሁበትም በመሆኑ ቅር ብሎኛል ያው ግን እግርኳሰ ላይ ያጋጥማል…
ሀትሪክ :- ገንዘብ ጥቅማ ጥቅም አላጣላችሁም..?
ሄኖክ:- በፍጹም ገንዘብ አያጣላንም ለኔ ገንዘብ ምክንያት አይደለም ክለቡን እወደዋለሁ እንደራደራለን እንስማማለን ይሄ ከባድ ጉዳይ አይደለም እነሱ ግን ለኔ ክብር አልነበራቸውም ደስታዬን መንጠቅ ፈለጉ ክብሬን ዝቅ አደረጉ ከአቶ አብነትና ከደጋፊው ውጪ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ገፍተውኝ ነው የለቀኩት… ደጋፊውና ፕሬዝዳንቱ እንደማይጠሉኝ አውቃለሁ …ይሄን እውነት ግን ሙሉ ደጋፊው ማወቅ አለበት
ሀትሪክ :- የውጪ ዕድሉን እንደ ካሳ ቆጠርከው …?
ሄኖክ:- ፕሮፌሽናል ሆኖ ከሀገር ወጥቶ መጫወት ህልሜ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ ውስጥ ተጫውቻለሁ .ዋንጫ ደጋግሜ ወስጃለሁ ይሄ ትልቅ ታሪክ ነው ግን ከምወደው ክለቤ ተገፍቼ ስወጣ ያገኘሁት የውጪ ዕድል አስደስቶኛል መገፋት ጥሩ ነው ካሳ ያሰጣል /ሳቅ/
ሀትሪክ :- በግብጽ ሊግ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች አምባሳደርነት አይሰማህም …?
ሄኖክ :- በደንብ ነው የሚሰማኝ… ትልቅ ሃላፊነት ይዤ ነው የምሄደው ይሄን ለመወጣት እጥራለሁ ሌሎች የሊጉ ክለቦች ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾችን እንዲፈልጉ እንዲመለከቱ የሚጋብዝ አቅም ለማሳየት እጥራለሁ ከፈጣሪ ጋርም ይሳካል ብዬ አምናለሁ
ሀትሪክ :-ከሊጉ መጠናቀቅ በኋላ በደንብ ዕረፍት አደረክ….?
ሄኖክ :- የምር ነው ያረፍኩት ….ከቤተሰቦቼ ጋር አሪፍ የዕረፍት ጋዜ ነበረኝ ለጨዋታ ለቀጣይ ሲዝን በጥሩ አዕምሮ እንድዘጋጅ የሚያደርግ ዕረፍት ለማድረጌ ርግጠኛ ነኝ
ሀትሪክ – 2016 ለቅዱስ ጊዮርጊስና ላንተ አሪፍ ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል …?
ሄኖክ:- በግሌ አመቱ ለኔ አሪፍ የውድድር አመት ነበር ጥሩ ጊዜ እንደነበረኝ አምናለሁ… መጨረሻ ላይ ጉዳት ቢገጥመኝም ጥሩ የውድድር አመት አሳልፌያለሁ ብዬ አምናለሁ… እንደ ክለብ ግን ሁሌ ዋንጫ የለመደ ነው ቡድኑ የሚታወቀው በሻምፒዮንነት ነው ሁለት ተከታታይ አመታት አሸንፈናል ዘንድሮ ግን ብዙ ተጨዋቾችን ለቅቆ በወጣት ብቻ የተሞላ አብዛኛውን ታዳጊ በምትለው ደረጃ ነው የቀረበው ጥቂት ሲኒየር ቢኖር ነው ከዚህ አንጻር ለክፉ የሚሰጥ ነበር ብዬ አላምንም..
ሀትሪክ:- ነጥብ ከጣላችሁበት ጨዋታ በይበልጥ ያበሳጨህ የትኛው ነው .?
ሄኖክ :- ከሁሉም እየመራን ባለቀ ሰአት ግብ ገብቶብን አቻ የወጣንበትና ከወላይታ ድቻ ጋር ያደረግነው ጨዋታ አበሳጭቶኛል…. ከዚያ ውጪ ሁሉም ሽንፈት አበሳጭቶኛል በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ሁሉም ሽንፈት ያበሳጫል ደረጃ የምሰጠው ሽንፈት የለም የሚያሳምነኝም ሽንፈት የለም .. ሽንፈት አይመቸኝም በጣም ያናድደኛል
ሀትሪክ– እንደ ተጨዋች የትኛውን ቡድን መግጠም ደስ ይልሃል..? ያስቸገረህ ተጨዋችስ..?
ሄኖክ :- የሸገር ደርቢ ነዋ …., ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረግናቸው ጨዋታዎች ሁሉ ያስደስተኛል .. በተጨዋችነት ጊዜዬ በቦታዬ በጣም ያሰቸገረኝ ደግሞ ቸርነት ጉግሳ ነው በጣም ታግለናል ብዬ አምናለሁ አጨዋወቱን የምወድለት የፈተነኝም እሱ ነው
ከሀትሪክ:- ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፈርሞ ስትጫወቱ እፎይ አልካ..?
ሄኖክ:- /ሳቅ ቀሳቅ/ አዎ አርፌያለሁ /ሳቅ/
ሀትሪክ :- ምላሽ ስትሰጥ በጣም ተጠንቅቀህ ነው ልክ ተከላካይነት ቦታህ ላለመበለጥ ይመስላል ..
ሄኖክ :-/ ሳቅ በሳቅ / አዎ የሚጠቅም የተሻለ የታሰበበት ምላሽማ የግድ ነው /ሳቅ /
ሀትሪክ :- በቦታው ምርጡ ማነው ..?
ሄኖክ :- ከሀገር ውስጥ ሱሌይማን ሀሚድ ነው ….
ከውጪ. ደግሞ ሃኪሚ ሃሺራፊ ምርጫዎቼ ናቸው ሁለቱም በየደረጃቸው ምርጥ ናቸው ..
ሀትሪክ– በአመቱ ውስጥ ትልቅ የምትለው ክለብ ገጥሞሃል ..?
ሄኖክ :-የለም የለም… አልነበረም ቀዝቃዛ ሲዝን ነበር የወጣ ከሌሎቹ የተሻለ አቋም ያሳየ ክለብ አልገጠመኝም
ሀትሪክ :- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የመቻልን ፍልሚያ እንዴት አየኧው ..?
ሄኖክ :- እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ የነበረው ፉክክር ደስ የሚል ነበር ለሊጉም እድገት ጥሩ እንደነበር መናገር ይቻላል … መቻልም ጥሩ የውድድር አመት አሳልፏል… ያው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተሻለ ነጥብ በመሰብሰቡ ዋንጫውን አሸንፏል ሰርተው ላገኙት ድል ክብር አለኝ …በዚሁ አጋጣሚ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ሀገር ወክለው እየተጫወቱ እንደመሆኑ በቀጣይም እንዲሳካላቸው እመኛለሁ…
ሀትሪክ:- አብዛኛው ተጨዋች ከባድ ልምምድ አይወድም ይባላል .. አንተስ ልምምድ ትወዳለህ ..?
ሄኖክ:- አዎ በጣም ወሳኙ ልምምድ ነው አማራጭ የለምኮ .. ዓላማ ያለው የተሻለ እንዲከፈለው የሚፈልግ ተጨዋች ልምምዱን መውደድና ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ ይሄ የግድ ነው አሰልጣኙ ከሚሰጠህ ልምምድ ውጪ የራስ ተጨማሪ ዝግጅት የግድ ነው ለውጥ ከፍ ማለት መፈለግ ያማረው መዘጋጀት አለበት ጂም ገብቶ መስራት ይጠበቃል የዝግጅት አቅምህ ነው ውጤታማነትህን የሚወስነው ብዬ አምናለሁ
ሀትሪክ:- ከልምምድ በኋላስ ዕረፍትህን በትክክል ትጠቀማለህ..?
ሄኖክ :- የግድ ነው በጣም አርፋለሁ እሱ ግዴታ ነው ጨዋታው ሁለት ቀን ሲቀረው ደግሞ ለኮንሰንትሬሽን ራሴን አዘጋጃለሁ እንደ አጠቃላይ መስራት ደጋግሞ መዘጋጀት ተገቢ ዕረፍት መውሰድማ የግድ ይላል
ሀትሪክ :- ቲየሪ ኦነሪ ብለን አርሴን ቬንገር ካልን ሄኖክ ብለንስ ማንን እንጥራ..?
ሄኖክ :- /ሳቅ / ሁሉን ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞችን ነው ማመስግነው የተለያየ ነገር ጨምረውልኛልና ሁሉንም አመሰግናለሁ
ሀትሪክ :- እነሱን እናመስግን ….እንደ ኦነሪስ የምትጠራው ለተጨዋችነትህ ትልቅ ድጋፍ ያደረገ አሰልጣኝ ማነው ነው ያልኩህ …?
ሄኖክ :- / ሳቅ / አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይሌ ያመዝናል .. ጅማ አባጀጅፋር እያለን ለውጥ እንዲኖረኝ በደንብ ተከታትሎ የረዳኝ አንገቴን አንቆ እያሳየ እንዴት ክሮስ እንደሚደረግ ያስተማረኝ እሱ ነው በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ… ብዙ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለኦኪኪ አፎላቢ እየየሰጠሁ ለቡድኑ ድል የበኩሌን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ለዚህ ደግሞ አሰልጣኝ ገብረ መድህን ትልቅ ድጋፍ አድርጎልኛል ….
ሀትሪክ:- ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ለስንብት የምትለው ካለ..?
ሄኖክ :- የሚገርም ደጋፊ ነው በጣም እወዳቸዋለሁ ለሰጡኝ ክበርና ሞራል በጣም አመሰግናለሁ ..ቤተሰባዊ ክለብ ነው ለደጋፊውና ለአቶ አብነት ትልቅ ክብር አለኝ አቶ አብነት ብዙ ነገር ረድተውኛል ደግፈውኛል አመሰግናቸዋለሁ ለአቶ አብነት ምንም ነገር ይገባል ደጋፊው ስለወጣሁ ቅር ሊለው ይችላል የተደረገብኝን እንደማያውቁ አውቃለሁ ሁሌም የጊዮርጊስ ደጋፊ ነኝ ይህን መናገር እፈልጋለሁ ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝና ለምወደው ክለቤ አመቱ የስኬት እንዲሆን እመኛለሁ
ሀትሪክ :- ከጅማ አባጅፋርና ከቅዲስ ጊዮርጊስ ጋር ትልቁን የሊግ ውድድር አሸንፈህ ዋንጫ ወስደሃል…ይሄ ምን ስሜት ይፈጥራል ….?
ሄኖክ :- ዋንጫ ያነሳሁበት ጊዜ የፈጠረው ስሜት ይለያያል … ከቅዱስ ጋር ካነሳኋቸው ፋሲል ከነማን በአንድ ነጥብ በልጠን ዋንጫ የወሰዴነው የራሱ ትልቅ የደስታ ስሜት አለው … የጅማውም የመጀመሪያ መሆኑ የውድድሩ ፎርማት በሜዳና ከሜዳ ውጪ ተጫውተን ዋጋ ከፍለን ያገኘነው በመሆኑ ሌላ የደስታ ስሜት ይፈጥራል ….. እንደ አጠቃላይ ሰርተን ያገኘናቸው ድሎች በመሆናቸው ዋንጫዎቹ ሁሉ ደስ ይላሉ
ሀትሪክ :- ከሀላባ እስከ አሁን ከፍ እያልክ እየሄድክ አይመስልህም ..?
ሄኖክ :- አዎ ራሴን እያየሁ ከፍ እያልኩ እንደሆነ ይሰማኛል … በዚህም ደስተኛ ነኝ ውጤትና ዕድገት አልተለየኝም በተጨዋችነቴ በጣምም ደስተኛ ነኝ
ሀትሪክ . ጨረስኩ የመጨረሻ የምታመሰግነው ካለ …?
ሄኖክ :- የቅድሚያ ምስጋና ለእግዚአብሄር ይሁንልኝ፣ ለመላው ቤተሰቤ፣ እስካሁን ከእኔ ጎን የነበሩ መልካሙን የሚመኙልኝ የረዱኝን በሙሉ አመሰግናለሁ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የቦርድ ፕሬዝዳንት ጋሽ አብነት ገብረመስቀልና የምወዳቸውን ደጋፊዎች በሙሉ አመሰግናለሁ አንተም ለሰጠኧኝ ዕድል ትልቅ ክብር አለኝ …አመሰግናለሁ