በፔሩ ሊማ በመካሄድ ላይ ባለው የዓለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ቀን አንድ የወርቅ እና ሁለት የብር ሜዳልያዎችን አሳክታለች።
በሴቶች 5 ሺህ ሜትር በተደረገው ውድድር አትሌት መዲና ኢሳ 14:39.71 በመግባት የውድድሩን ክብረወሰን በመስበር ጭምር አሸንፋለች።
የርቀቱ ክብረወሰን አስቀድሞ በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የነበረ ነው።
አትሌት መዲና ኢሳ በ2022 በኮሎምቢያ ካሊ በተደረገው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ውድድርም በርቀቱ አሸናፊ ነበረች።
- ማሰታውቂያ -
ይህም በዓለም ከ20 አመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በተከታታይ ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት እንድትሆን አሰችሏታል።
በውድድሩ አትሌት መቅደስ አለምሸት በ14:57.44 በሁለተኝነት በማጠናቀቅ የብር ሜዳልያ አስመዝግባለች።
በወንዶች በተደረገው የ5 ሺህ ሜትር የፍፃሜ ውድድር ደግሞ አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በ13:41.56 በሁለተኝነት አጠናቋል።
በውድድሩ የተካፈለው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ንብረት ክንዴ በ13:44.67 በስድስተኛ ደረጃ ውድድሩን ፈፅሟል።
በዚህም ኢትዮጵያ በሜዳልያ ሰንጠረዡ በአንድ የወርቅ እና ሁለት የብር በድምር ሶስት ሜዳልያዎች አንደኛ ላይ ተቀምጣለች።