“ለቅዱስ ጊዮርጊስ እያንዳንዱ ጨዋታ የዋንጫ ያህል ነው”አስቻለው ታመነ ቅ/ጊዮርጊስ/

ቅ/ጊዮርጊስ ወላይታ ዲቻን በሳላህዲን ሰይድ ብቸኛ ግብ 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ተከላካዩ አስቻለው ታመነ ለቡድኑ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን ይኸው ተጨዋች በዘንድሮው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ዙሪያ ክለባቸው የሊጉ ሻምፒዮና እንደሚሆንና እያንዳንዱ ጨዋታዎቻቸውም የዋንጫ እንደሆኑም ከሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ባደረገው ቆይታ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የቅ/ጊዮርጊሱ ጠንካራው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች አስቻለው በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ዙሪያ እና ከራሱ ወቅታዊ አቋም ጋር በተያያዘ ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ የሰጠው አጠቃላይ አስተያየትም ይህንን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡

ሀትሪክ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ቅ/ጊዮርጊስ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎቹን በድል ተወጥቶ ወደ አሸናፊነት መንፈሱ ተመልሷል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን ማለት ይቻላል?

አስቻለው፡- የእውነት ነው እኛን ቅ/ጊዮርጊሶችን የሚመጥነንም እንደዚህ አይነት የድል ውጤቶችን ይዘን ለመውጣት ስንችልም ነው፤ ቅ/ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት መንፈሱ ሊመለስ የቻለው በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎው በመጀመሪያው ቀን ግጥሚያ በፋሲል ከነማ ከቆይታዎች በኋላ ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና ያስተናገድናቸው ሽንፈቶች በእያንዳንዳችን ተጨዋቾቻችን ላይ ከፍተኛ የቁጭት ስሜትን ፈጥሮብን ስለነበር ከእነዛ ጨዋታዎች ክፍተቶቻችንና ድክመቶቻችን በመነጋገር ስለታረምንና ከጨዋታ ወደ ጨዋታም እየተሻሻልን ስለመጣንም ነው ወደ አሸናፊነቱ መንፈስ ልንመለስ የቻልነው፡፡

ሀትሪክ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ለክለብህ እያሳየክ ያለው አቋም የወትሮ አይደለም…..?

አስቻለው፡- የእውነት ነው፤ ይሄንን እኔም ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ በሊጉ ባደረግናቸው አንድ አንድ ጨዋታዎች ላይ ከዚህ ቀደም በምታወቅበት ምርጥ ብቃቴ ላይ ላልገኝ የቻልኩት በአቋም መውረድ ሳይሆን በተከሰተብኝ የጤንነት ችግር ነበር፤ ዘንድሮ ከብሔራዊ ቡድን መልስ ከክለቤ ጋር በቂ የሆነ ልምምድን አልሰራሁም፤ የብሽሽት ህመም አጋጥሞኝ ስለነበር ከሰበታ ከተማ እና ከቡና ጋር በነበረን ጨዋታ መርፌ ተወግቼም ነበር ልጫወት የቻልኩት፤ በዛ ላይ እኔ የምጫወትበት የተከላካይ ቦታ ራሱ እንደ ስሙ ከፍተኛ ወኔ የሚፈልግ ስለሆነም በደጋፊ ታጅበህ ስትጫወት ከፍተኛ ሞራል እንዲኖርህም ያደርጋል፤ እነዚህ ምክንያቶች እና የደረሰብኝ ጉዳት ጭምርም ነው በእነዛ ግጥሚያዎች ላይ ጥሩ አቋሜን እንዳላሳይ ያደረጉኝ አሁን ግን ወደ መልካም ጤንነቴ ስለተመለስኩ ለክለቤ በጥሩ ሁኔታ ነው እየተጫወትኩኝ ያለሁት፡፡

ሀትሪክ፡- የቅ/ጊዮርጊስ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው በምን ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስልሃል?

አስቻለው፡- እያንዳንዱ ጨዋታዎቻችን የፍፃሜ ግጥሚያዎች ስለሆኑ በዋንጫ ባለቤትነት ነዋ! ከእዛ ውጪ እኛ ጋር የትኛውም ውጤት እንዲመጣ ፈፅሞ አይታሰብም፤ ቅ/ጊዮርጊስ የሊጉን ዋንጫ ከዚህ ቀደም አልፎ አልፎ በተለያዩ ምክንያቶች ቢያጣም ሁሌም የሚጫወተው ለሻምፒዮናነት ነው፤ ዘንድሮም ይሄን ድል ምንም እንኳን ካጣነው ሶስት ዓመታትን ብናስቆጥርም ጣፋጭ ስኬቱን ዳግም ወደ ቤታችን እንመልሰዋለን፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ከተለያዩ ቡድኖች በመምጣት ስለሚቀላቀሉት ተጨዋቾች ምን የምትለው ነገር አለ?

አስቻለው፡- ራሴን ጨምሮ ብዙ ጊዜ ወደ እኛ ቤት የሚመጡት ተጨዋቾች ዋንጫን እንጂ ገንዘብን ፈልገው እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለው፤ ቅ/ጊዮርጊስ ቤት ስትመጣ የመጀመሪያ ዓላማህም ብዙ ጊዜ በሌላ ቡድኖች ውስጥ የማታገኘውን ድል በዚህ ቡድን ውስጥ ለመጎናፀፍ ትችላለህና ለእዛም ነው ክለባችንን እነዚህ ተጨዋቾች የሚቀላቀሉት፡፡

ሀትሪክ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ የተጨዋቾች ስብስብ እንዳላችሁ እንጂ ምርጥ አሰልጣኝ እንደሌላችሁ ከአንድ አንዶች አንደበት ሲነገር ይደመጣል?

አስቻለው፡- ይሄን ፈፅሞ አንቀበለውም፤ አንድአንዴ ውጤት ሲበላሽም ነው እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲነሱ የሚደመጡትና አሰልጣኛችንን በተመለከተ እንደዛ የሚሉ ሰዎች ካሉም እንደተሳሳቱ መናገርን እፈልጋለውኝ፤ የቅ/ጊዮርጊስ አመራር እኮ ተጨንቆ እና ተጠቦ ነው ጥሩ አሰልጣኝን ከውጪ ሀገር አፈላልጎ እና አወዳድሮ የሚያስመጣው ክለቡን ከሀገር አልፎ በአፍሪካ ክለቦች የውድድር መድረክ ላይም ታላቅ ስፍራ ላይ ለማድረስ ስለሚያቅድም አመራሮቻችን ያመጡልን አሰልጣኝ ጥሩ ብቃት ያለው እና እኛን መለወጥ የሚችልም እንደሆነ ደግሜ መናገር እፈልጋለውኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጎልቶ የተመለከትከው ተጨዋች ማንን ነው?

አስቻለው፡- እከሌ እከሌ አልልም ብዙዎቹ ተጨዋቾች ጥሩ እና ከፍተኛ መሻሻልን የተመለከትኩባቸው ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ጎሎች እየተቆጠሩ ነው፤ ምክንያቱ ምንድን ነው ትላለህ?

አስቻለው፡- በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአብዛኛው ጨዋታዎች ላይ ብዙ ጎሎች እየተቆጠሩ ያሉት የሊጉ ጨዋታዎች በዲ.ኤስ ቲቪ ከመተላለፋቸው አንፃር ተጨዋቾች ራሳቸውን በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ወደ ውጪ ሀገር ለመሸጥ ጠንክረው ሰርተው በመምጣታቸው ነው፡፡

ሀትሪክ፡-የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ለቅ/ጊዮርጊስ ማንኛው ቡድን ስጋት ይሆንበታል? ጠንካራ ተፎካካሪውስ ማን ይሆናል?

አስቻለው፡-የሊግ ዋንጫውን ለማንሳት ስጋት ይሆንብናል ብዬ የምፈራው ቡድን ማንም የለም፤ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ግን አሉን፤ ሁሉም የሊጉ ቡድኖች ናቸው ለእኛ ጠንካራ ተፎካካሪዎቻችን፤ ቡድኖቹ ከእኛ ጋር ሲጫወቱም በሌላ ግጥሚያ ላይ 5-0 ተሸንፈው ቢመጡ እንኳን ከእኛ ጋር ሲጫወቱ 200 ፐርሰንት ጨምረው ስለሚመጡ ያ እኛን የበለጠ ያጠናክረናል፡፡

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor