“ለብሔራዊ ቡድን ከተጠሩት 41 ተጨዋቾች ውጪ መሆኔ በጣም አበሳጭቶኛል”ፈቱዲን ጀማል

ለብሔራዊ ቡድን ከተጠሩት 41 ተጨዋቾች ውጪ መሆኔ በጣም አበሳጭቶኛል”

“እንዴት ሳትጠራ ቀረህ እያለ ለሚወተውተኝ አእምሮዬ መልስ መስጠትም አቅቶኛል”
ፈቱዲን ጀማል


ባሳለፍነው ሣምንት ሁለት የተዘበራረቁ ስሜቶችን አስተናግዷል፤በቃላት የማይገለፅ ከፍተኛ ደስታንና በተቃራኒው የመረረ ሀዘንን አስተናግዶ አሳልፏል፡፡ የረዥም ጊዜ የፍቅር ጓደኛው ከሆነችው ፈቲያ ሱናሙ ጋር በአንድ ጣሪያ ስር የሚያኖራቸውን ጋብቻ በይፋ በመፈፀሙ “የደስታዎች ሁሉ ቁንጮ” ያለውን ደስታ ያጣጠመ ቢሆንም የኢትዮጵያ ብ/ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለተጨዋቾች ጥሪ ሲያደርግ ከጠራቸው 41 ተጨዋቾች ውጪ መሆኑ ለብስጭት ዳርጎት የሞቀ ደስታውን ሊነጥቀው ታግሎታል፤በዚህም “በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የአሰልጣኝነት ዘመን 23 ውስጥ የነበርኩ ሰው እንዴት አሁን ከተጠሩት 41 ተጨዋቾች ውጪ እሆናለሁ?” ሲልም በቁጭት ይጠይቃል፡፡

በኢትዮጵያ ቡና ስሙ ከፍ ብሎ የተጠራበትን ድንቅ የጨዋታ አመት ያሳለፈው ፈቱዲን ጀማል “ለብሔራዊ ቡድን ከተጠሩት 41 ተጨዋቾች ውጪ መሆኔ በጣም አበሳጭቶኛል፤እንዴት ሳትጠራ ቀረህ? እያለ ለሚተውተኝ አዕምሮዬም መልስ መስጠትም አቅቶኛል” ብሏል፡፡
“ምናልባት አቅሜ ወርዶ ነው ብዬ ለአዕምሮዬም እንዳልነግረውና ውስጤን እንዳላሳምን በኮቪድ ምክንያት ውድድሩ እስከተቋረጠበት ድረስ በጥሩ አቅም እንደጨረስኩ ሚዲያው፣የስፖርት ቤተሰቡና አሰልጣኞች በተደጋጋሚ ሲመሰክሩልኝ የአዲስ ከተማ ዋንጫ ክብርንም አግኝቼ ነበር” የሚለው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና የአሁኑ የሲዳማ ቡና ተጨዋች የሆነው ፈቱዲን ጀማል “41ዱም የብ/ቡድኑ ተጨዋቾች ጥሪ የተደረገላቸው ባለፈው አመት ባሳዩት አቋም…በነበራችው ችሎታና ስም ነው፤እውነታው ይህ ከሆነ ታዲያ ባለፈው ብ/ቡድን 23 ውስጥ የነበርኩ ተጫዋች በምን መመዘኛ ከ41ዱ ተጫዋቾች ዝርዝር ውጪ አሆናለሁ? ለዚህ ጥያቄዬም እስከ አሁን አሳማኝ መልስ ማግኘት አልቻልኩም” በማለት ቁጭት በተሞላበት ስሜት ይጠይቃል፡፡
“ምናባልባት አሰልጣኙ አያውቀኝም እንዳልል እኔ ስጫወት የነበረው ፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ ለታላቁ ኢትዮጵያ ቡና…አሰልጣኙም ሲያሰለጥን የነበረው በፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ የሚጫወት ክለብን በመሆኑ እንደማልጠፋው እገምታለሁ” በማለት በአስተያየቱ የቀጠለው ፈቱዲን ጀማል “የማንኛውም ተጨዋች ህልምና ፍላጎት ሀገሩን ማገልገል ነው፤እኔ ደግሞ ሀገሬን በብቃት ማገልገል በምችልበት ሰዓት ከመጀመሪያ 41 ተመራጮች ውጪ መሆኔ በጣም አበሳጭቶኛል፤ሞራሌንም ነክቶታል” ብሏል፡፡

“እስቲ አንተም ህዝቡም ይፍረደኝ ውድድሩ በኮቪድ ምክንያት እስከ ተቋረጠበት ድረስ በነበረው ብ/ቡድን 23 ውስጥ ሆኜ አሁን ከኮቪድ በኋላ በተጠራው ብ/ቡድን ውስጥ ሌላው ቢቀር እንዴት በመጀመሪያ ከተጠሩት 41 ተጨዋቹች ውጪ እሆናለሁ?” በማለት የሚጠይቀው ፈቱዲን “አሰልጣኙ የሚፈልጋቸውን ተጨዋቾች የመምረጥ መብቱ የእሱ ነው እኔም ብግድ ካልተመረጥኩ እያልኩ አይደለም ነገር ግን ቢያንስ ያልተመረጥኩበትን ትክክለኛ ምክንያት ባውቀው ራሴን ለማሻሻል ይረዳኛል” ብዬ አስባለሁ” ብሏል፡፡
የፈቱዲንን አለመመረጥና ከ41ዱ ተጨዋቾች ውጪ መሆንን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገፅና በተለያየ መንገድ “ከኢትዮጵያ ቡና በመልቀቁ ነው ያልተመረጠው እንጂ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች ቢሆን ይመረጥ ነበር” የሚል አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ አስተያየቱን የተጠየቀው ፈቱዲን “እውነት ይሄ ተደርጎ ከሆነ የሚያሳዝን ነው…በእርግጥ ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ክለብ ነው…የሀገሪቱ ኃያላን ክለቦች ከሆኑት ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከኢትዮጵያ ቡና ብዙ ተጨዋቾች ይመረጣሉ…ግን አንድን ተጨዋች ለብ/ቡድን ለመምረጥ መስፈርቱ መሆን ያለበት ችሎታውና ሀገሩን በአግባቡ ማገልገል የሚያስችል ችሎታ አለው ወይ? የሚለው ነው፤ችሎታ ካለውና ሀገሩን የሚጠቅም ተጨዋች ከሆነ በታችኛው ሊግም የሜጫወት ቢሆን እንኳን በችሎታው ምክንያት ሊመረጥ ነው የሚገባው” የሚለው ፈቱዲን “ለብ/ቡድን ለመመረጥ የምትጫወትበት ክለብ ሳይሆን ችሎታህ ብቻ ዋነኛው መመዘኛ ሊሆን ይገባል” ሲል አስምሮ ይናገራል፡፡
አሁን የምትገኝበት አቋም የተጠሩት 41ዱ ተጨዋች ውስጥ የሚስገባ ነው? በሚል ከሀትሪክ በማስከተል ጥያቄ የቀረበለት ፈቱዲን “ስለ ራሴ ምስክርነትን መስጠት አልፈልግም፤ነገር ግን እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ 41ዱ ውስጥ መመረጥ ብቻ አይደለም ተሰልፌ መጫወት የሚያስችል አቅም እንዳለኝ ጥርጣሬው የለኝም” ካለ በኋላ “ብዙዎቹ ሚዲያዎች፣የስፖርት ቤተሰቦችና አሰልጣኞች እንዴት አልተመረጥክም እያሉ በተደጋጋሚ መጠየቃቸው፣መቆርቆራቸውና ማዘናቸውን ስታይ መመረጥ እንደማይበዛብኝ የማጠቁም ነው፡፡” ብሏል፡፡
በርካታ ሰዎች፣የኢት.ቡና ደጋፊዎች እየደወሉ ሞራል እንደሚሰጡትና እንደሚያበረታቱት በተለይ ለሀትሪክ የገለፀው ፈቱዲን “በዚህ አጋጣሚ ተቆርቁረው አጋርነታቸውን ያሳዩኘ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች፣ጋዜጠኞች፣ አሰልጣኞችንና የስፖርት ቤተሰቦችን ከልብ አመሰግናለሁ” ካለ በኋላ “ሁሌም ሀገሬን ለማገልገል…ከ110 ሚሊዮን ህዝብ በላይን ወክዬ የራሴንም የሀገሬንም ስም ለማስጠራትና ህልሜን ስለማሳካት ነው የማስበው…ያ ቀን ደግሞ ሩቅ አይሆንም…አላህ ሲፈቅድ ይሁን ሲል ይሆናል” ብሏል፡፡

በቀጣይ ምን አስበሃል…?…በሚል ከሀትሪክ በመጨረሻ አስተያየቱን እንዲሰጥ የተጠየቀው ፈቱዲን “የአሰልጣኙን ምርጫ አከብራለሁ ያልተመረጥኩበትን ምክንያት ባውቀው እማርበት ነበር ነው ጥያቄዬ…ከዚህ ውጪ ለምን አልተመረጥኩም?ብዬ እንደ ሌሎች ተጨዋቾች የማይሆንና መጥፎ ውሳኔ ውስጥ አልገባም…ምክንያቱም ዛሬ ባልመረጥም ነገ ሀገሬን በብቃት ማገልገል እንደምችል የጠነከረ እምነት በውስጤ አለ” በማለት የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ኮከብ የአሁኑ የሲዳማ ቡና አዲሱ ፈራሚና በቅርቡ ጋብቻውን የፈፀመው አዲሱ ሙሽራ ለብ/ቡድን አለመጠራቱን ተከትሎ አስተያየቱን በተለይ ለሀትሪክ ሰጥቷል፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.