የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአቶ ሠለሞን አባተ ላይ ያለውን ቅሬታ ገለፀ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ሳምንት ለንባብ በበቃው ጋዜጣችን በቀን 23/2013 በቁጥር 655 The Big Interview በሚለው አምዳችን የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ እግር ኳስ አሰልጣኞች ማህበር ዋና ፀሐፊ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተሰማውን ቅሬታ በቀን 29/01/13 ዓ.ም በቁጥር 2/ኢ.እ.ፌ.አ.3/1806 በጽ/ቤት ኃላፊው በአቶ ባህሩ ጥላሁን ልመንህ ተፈርሞ በተፃፈ ደብዳቤ ገልፀውልናል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሌሎችም ምሣሌ በሚሆን መልኩ የፕሬስ ሕጉ የሚፈቅደውንና ሃሣብን በሃሣብ የመታገል የሰለጠነ መንገድ በጉዳዩ ዙሪያ የቀረበውን ቅሬታ በዝግጅት ክፍላችን አንዳችም የአርትኦት ስራ ሣይደረግበት እንዳለ ማቅረባችንን እየገለፅን ፌዴሬሽኑ ለመረጠው የሰለጠነ መንገድ ያለንን አድናቆት ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ፌዴሬሽኑ ለዝግጅት ክፍላችን የላከው የቅሬታ ደብዳቤ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡


ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- የጋዜጣ ቁጥር 655 ቅዳሜ መስከረም 23 2013 ዓ.ም ዕትም ይመለከታል

ከላይ በርዕሱ እንደተገለፀው ቅዳሜ መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም ለንባብ ባበቃችሁት ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ላይ አቶ ሰለሞን አባተ ከጋዜጣችሁ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በማስመልከት የሰጡት አስተያየት ከልብ አሳዝኖናል ብሎም አሳፍሮናል፡፡
በጋዜጣው ላይ ጠቅላላ ጉባኤ አምኖባቸው ወደ አመራርነት የመጡትን ሥራ አስፈፃሚዎቻኝን በተለይ የፕሬዚዳንታችንን ክብር የሚነኩ ከአንድ ሙያተኛ ነኝ ብሎ ከሚያምን ግለሰብ የማይጠበቅ አገላለጾችን በመጠቀም ተቋሙ ብሎም አመራሮቻችን በማህበረሰቡ ዘንድ የተዛባ እምነት እንዲያሳድር የሚያደርግ አሳሳች ተግባር ፈፅመዋል፡፡
ብሎም በአሁን ሰዓት በዝግጅት ያለው ሀገራችንን በመወከል የሚወዳደረው የብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አባላቶቻችንን ህልውናውን ጠብቀን ውጤት እንዲያመጣ የስነ-ልቦና ዝግጅትንም ጭምር በማድረግ ላይ እያለ የቡድኑን የስነ ልቦና ዝግጅቱን የሚያደፈርስ ውጤት በማምጣት ላይ ከባድ ተፅዕኖ ሊያመጣ የሚችል ስሜታቸውን የሚጎዳ የተጫዋቾቻችንን የቡድን መንፈስ የሚያፈርስ የስፖርቱን እድገት ወደ ኋላ የሚጎትት አገላለጾችን ተጠቅመዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህንን የስም ማጥፋት እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑን ስነ ልቦና የማናጋት ተግባር የፈፀሙትን ግለሰብ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በአፅንኦት የሚከታተለው መሆኑን እየገለፅን፣ በጋዜጣው ላይ ቃለ መጠይቅ የሰጡት ግለሰብ እየመጣ ያለው ለውጥን ወደ ኋላ ለመጎተት የተደረገ ስም ማጥፋት እንደሆነ ጋዜጣው እንዲያውቅልን እናሳስባለን፡፡

ከሠላምታ ጋር
ባህሩ ጥላሁን ልመንህ
የጽ/ቤት ኃላፊ
ከማይነበብ ፊርማ ጋር

 

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team