ፋሲል ተካልኝ በአዲሱ ሲዝን አዲስ ተስፋ ሰንቋል

 

በኮቪድ ምክንያት ለ7 ወራት ያህል ከልምምድና ከውድድር ስለራቀበት አጋጣሚ…

“…ያ…ወቅት በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ ጊዜ ነበር…ውድድርና ልምምድ ውስጥ ሆነህ ህይወትህም ከሙያህ ጋር ለአመታት ተቆራኝቶ እየቀጠለ ባለበት ሰዓት ከአንተ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት በድንገት አቁም ስትባል ለመቀበል ትቸገራለህ…እኛም ያለፉትን ሰባት ወራቶች በዚህ መልኩ ነው ያሳለፍነው…ከምትወደው፣ህይወትህ፣እንጀራህ ከሆነ ነገር ተለይተህ እንድትኖር ሲወሰንብህ በስነ-ልቦናም በአዕምሮም በኩል የራሱ የሆነ ጉዳት አለው…እንግዲህ በዚህ ይቀጥልልን በል እንጂ…አሁን ወደ ልምምድም ወደ ውድድርም ተመልሰናል…ሲጠቃለል ግን እጅግ በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ የሆነ ጊዜን ነው ያሳለፍነው…”

ባህር ዳር ከተማን ለአዲሱ የውድድር ዘመን እንዴት ገንብቶ እንደቀረበ

“…ካለፉት ድክመቶቻችንና ከጥንካሬዎቻችን በመነሳት፣በመፈተሽ የብቃት ችግር የታየባቸውን በማሰናበት በራሳቸው ጊዜም በመልቀቅ…እንዲሁም ሁሉንም አግኝተናል ለማለት ቢቸግረንም ክለባችንን ይበልጥ ያጠናክሩልናል ወደምንፈልገው ነገር ለመንደርደር ጉልበት ይሆኑናል ብለን ያመንባቸውን ወደ ስድስት የሚጠጉ ተጨዋቾችን በማምጣት ቡድናችን ለአዲሱ የውድድር ዘመን አቀናጅተን ቀርበናል… በአጠቃላይ ሜዳ ላይ ሲታይ ጥሩ የሆነና ውጤታማ ሊሆን የሚችል ቡድንን ይዘን እንቀርባል ብዬ አምናለሁ…”

ውድድሩ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ስለመባሉ በሱፐር ስፖርት ስለመተላለፉና እግር ኳሱ ገንዘብ ማምጣት ስለመጀመሩ…

“…ይሄ ለእግር ኳሱ ትልቅ ስኬት ነው…አንድ እርምጃ የመራመድ ያህልም ነው…ለሀገራችን እግር ኳስም መልካም የሚባል አጋጣሚም ነው…በሌላው አለም እግር ኳሱ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚፈስበት ትልቅ ኢንዱስትሪም ነው…በሀገራችን ክለቦች ደሞዝ ለመክፈል ሲቸገሩ አስተውለናል…እግር ኳስ ከፋይናንስ ጋር ቁርኝት ስላለው ገንዘብ የሚያገኘበት፣እግር ኳሱ የሚሸጥበት፣ገንዘብ የሚያወጣበት ጊዜ ላይ ደርሶ ማየታችን በጣም ትልቅ ነገር ነው…ሌላው ውድድሩ በሱፐር ስፖርት መተላለፉ ሀገራችንን በሩጫ ብቻ የሚያውቋት እግር ኳስም በሀገራችን እንዳለ ብቻ ሣይሆን ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች እንዳሉን የምናሳይበት ጥሩ ድልድይም ነው…እንደሚታወቀው የሁሉም ተጨዋች ህልም ፕሮፌሽናል ተጨዋች መሆን ከመሆኑ አንፃር አጋጣሚው ጥሩ ነው…በእኛ የጨዋታ ዘመን ይሄ ወርቃማ እድል አልነበረም… የአሁኑ ትውልድ ይሄን አግኝቷል…ወርቃማውን እድል በአግባቡ መጠቀም የተጨዋቾቻችንም ኃላፊነት ነው”

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅበህ ተጫውተሀል አሰልጥነሃልም ውድደሮች ያለ ደጋፊ መካሄዳቸው ምን ስሜት ፈጠረብህ…?

“እውነት ለመናገር ሙሉው የእግር ኳስ ህይወቴ በደጋፊዎች የታጀበ ነው፤ በርካታ እግር ኳስ ወዳድ የሆኑ ደጋፊዎች ባሉበት ክለብ ውስጥ ነው ተጫውቼም አሰልጣኜም ያሳለፍኩት… አሁንም ወደ ባህርዳር ስመጣ የገጠመኝ ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡
ተመልካቾች የእግር ኳስ ውበት መሆናቸው ጥያቄ የሚነሣበት ባለመሆኑ ያለ እነሱ የሚካሄድ እግር ኳስ…የሆነ ነገረ የጎደለው ያህል እንዲሰማህ ያደርጋል…ውድድሮች ያለ ተመልካች የሚካሄዱ መሆናቸውን ስታስብ በጣም ያስጨንቅሃል…የለመድንበት፣የመጣንበት መንገድ ይሄ ባለመሆኑም በጣም ግር ይልሃል…ምናልባት እንደ ውጪዎቹ ተመልካች ያለ በማስመሰል ነገሮችን ለመቀነስ የታሰበ ነገር ካለ አላውቅም እንጂ…እግር ኳስን ያለ ተመልካች ማሰብ በጣም ከድ ነው…እንግዲህ ከሩቅ ሆነን የሚሰማንን ነው የምነግርህ…ውስጡ ስንገባ ምን ምን ይለናል? የሚለውን ውስጡ ስንገባ ስሜቱን በደንብ የምናጣጥመው ነው የሚሆነው…፡፡”

ፋሲል እንደ አልጣኝ በፕሪሚየር ሊጉ ከየት ተነስቶ የት መድረስ ይፈልጋል? አላማና ግቡስ…?

“…የመጀመሪያው ያለፈውን አመት የተፎካካሪነት ስሜትና ደረጃችንን መጠበቅ ነው…ከዚህ ከፍ ሲልም ወደ ተሻለ ነገር መጓዝን ነው…የባለፈውን አመት የተፎካካሪነት ስሜት በማምጣት ወደ አዲስ ስኬት መንደርደር ነው ሃሣባችን…ይሄንን ለማሳካት ነው እንግዲህ እንደ ቡድን እየሠራን ያለነው…፡፡

ፋሲል የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳትስ አይፈልግም…?

“…እኔ ብቻ አይደለሁም…የሁሉም አሰልጣኞች ፍላጎትም ይሄው ነው…ሁሉም ዋንጫውን ማንሣት ይፈልጋል…ግን በመጨረሻ ይሄን ማሳካት የሚፈልገው እንደ ቡድን ብቻ ነው…ዋንጫ በጣም እፈልጋለሁ…ግን ዋንጫ ስለምፈልግ ብቻ…ልጆቼን ዋንጫ ካልወለዳችሁ ብዬ ጫና ውስጥ መክተት አልፈልግም…”

ፋሲል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሣት ምን ያህል አመት ይጠብቃል…?…ወይስ ስንት አመት ይወስድበታል…?

“…እንደዚህ አይነት ጥያቄ ይጠየቃል እንዴ…?…ዋንጫን የምታነሣው በቀጠሮ ሳይሆን በብቃትህ ነው… የጨዋታም፣የአሰልጣኘነት ዘመኔም በዋንጫ የታጀበ ነው…አሁንም ወደ አሰልጣኘነት ስመጣ ይሄን ለማስቀጠል ነው…ያም ሆን ግን በዚህ ሰዓት ወይም በዚህ ቀን ብዬ ከወዲሀ መናገር አልችልም… ምከንያቱም እኔ ተንባይ አይደለሁም…ደግምም የሊጉን ዋንጫ ማንሣት አለብኝ ብዬ ሳልሰራ በመጨነቅ የማሳልፍም ሰው አይደለሁም…ጠንክሬ ከሰራሁ በቀጠሮ ሳይሆን ራሱ ሥራዬ ከምፈልገው ነገር ጋር ያገናኘኛል…ሁሉም ነገር በሂደት ይመጣል…በእግር ኳስ ምን እንደሚያጋጥም እንደማይታወቅ ስለምረዳ መተንበይ አልወድም…እንዳልኩህ ሁሉም በሰዓቱ ይሆናል…”

ባለፈው አመት ከነበራቸው ጥንካሬና ከዘንድሮው ስብስባቸው በመነሣት እነማን የዋንጫው ተፎካካሪ ይሆናሉ ብሎ ያስባል…?

“…የቡድኖችን ስም መጥቀስ ከባድ ቢሆንም..ከያዘው የተጨዋቾች ስብስብ አንፃር ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዋንጫው ቅድመ ግምት የምትሰጠው ነው…ፋሲል ከነማም አሁን እንዳለው ስነ-ልቦናና በኢንተርናሽናል ተሳትፎአቸው ካገኙት ጨዋታዎችና ልምድና አንፃር እነሱም ለዋንጫ የተጠጉ ናቸው…
ኢት.ቡናም ለዋንጫው ጠንካራ ተፎካካሪ ከማይሆኑ ክለቦች ተርታ ውስጥ ይገኛል…ሲዳማ ቡናም ጋ ስትመጣ የዋንጫ ቡድን ሆኖ ይታይሃል…እዚህ ውስጥ የእኛን ክለብም ሳትዘነጋ በጠቀስኩልህ ክለቦች መካከል በተለይ የሚደረግ ጠንካራ የዋንጫ ፉክክር ይኖራል ብዬ ነው የማስበው…”

3ቱ የትግራይ ክለቦች ከውድድር መውጣታቸው ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ….

“…የሶስቱ የትግራይ ክለቦች አለመሳተፍ የተሳታፊዎችን ቁጥር ወደ 13 ስለሚያወርደው በተለይ ላለመውረድ የሚደረገውን ፉክክር የሚያከብደው ይመስለኛል…ከ13 ቡድን ሶስት የሚወርድ በመሆኑ እዛ ውስጥ ላለመገኘት ሁሉም ራሱን ለማዳን ስለሚጫወት በዚህ በኩልም ጠንካራ ፉክክር የሚታይ ይመስለኛል…ሁላችንም ከዋንጫው ባልተናነሰ እዚህ ውስጥ ላለመገኘት ጠንክረን እንሰራለን… ምክንያትም ከሊጉ መውረድ ማለትም ብዙ ነገር ያሳጣልናል…”

ከቡድኑ ጎልቶ ይወጣል ወይም ክስተት ይሆናል ብሎ የሢጠብቀው ተጫዋች…

“…እንግዲህ ፍፁም አለሙ ያለፈውን አመት ብቃቱን አስጠብቆ መጓዝ ከቻለ እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም ጎልቶ ይወጣል የሚል እምነት አለኝ…ግርማ ዲሳሳ፣ባዬ ገዛኸኝ፣ፍቅረማርያምም በውድድሩ የሚደምቁ ኮከቦች ይሆናሉ ብዬ ቅድመ ግምት ብሰጥም…ሁሉም የቡድኔ ተጫዋቾች የሊጉ ክስተቶች እንደሚሆኑ በማመን ነው…”

ውድድሩ በተመረጡ ስታዲየሞች ብቻ መካሄዳቸው ከሜዳ የሚገኝ እድልን ያሰጣ ይሆን? በተለይ የአዲስ አበባ ቡድኖችንችን ተጠቃሚ ያደርጋል በሚል ለቀረበለት ጥያቄ…?

“…በተለየ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ብዬ አላስብም…ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢት.ቡና በሜዳቸው ቢጫወቱም ጨዋታቸውን የሚያደረጉት በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው ሳይሆን ያለ ተመልካች በመሆኑ ለሁለቱም ቡድኖች ጨዋታዎች እኩል ናቸው ብዬ ነው የማምነው…በሜዳችን በከተማችን ነው የምንጫወተው የሚል ስነ ልቦና ካልሆነ በስቀተር ሌላ የሚያስገኘው ጥቅም አለብ ብዬ አላስብም…እንደ ቡድን ግን በሜዳዬ ስጫወት ብለህ የምታሰላቸው ወይም አገኛቸዋለሁ ብለህ የምታስባቸው ነጥቦች አሉ…እንደዚህ አይነት ሂሣብ ወይም ስሌት ዘንድሮ ያለ አይመስልም…”

ከሲዳማ ቡና ጋር ስለሚጠብቀው የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ…?

“…አንደ አጋጣሚ ሆኖ የመክፈቻ ጨዋታችን ከጠንካራው ሲዳማ ቡና ጋር ነው…በተቻለን አቅም በተሻለ ውጤት ለመጨረስ አስበን ነው የምንገባው…ምከንያቱም የመጀመሪያ ጨወታችንን ማሸነፍ ለእኔም ለልጆቼም በአጠቃላይ ለቡድኑ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል ብዬ ነው የማስበው…ለማሸነፍም ነው ወደ ሜዳ የምንገባው…አሁን ግን ከዘጠና ደቂቃው ጨዋታ በፊት እንዲህ ነው እንዲያ ነው ብዬ ብዙም ፉከራ ማብዛት አልፈልግም…የተሻለ ነገር ለማስመዝገብ እንጥራለን ነው መልሴ…”

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.