ከአወዛጋቢው የምኞት ደበበ የቀይ ካርድ ቅጣት በኋላ አፄዎቹ ይግባኝ ሊጠይቁ ቢሆንም ውሳኔው ግን ሊፀና ይችላል።
በአስረኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፋሲል ከነማ ተጋጣሚው ነገሌ አርሲን 1ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ 80ኛው ደቂቃ ላይ የነገሌው ጋናዊ የግብ ዘብ ኢድሪሱ አብዱላሂ በረጅሙ የለጋውን ኳስ አጥቂ ሐቢብ ከማል ኳስን ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ ምኞት ደበበ እንዳያገኛት ብቻ በመሸፈኑ የተነሳ ፌድራል ዋና ዳኛ ሔኖክ አበበ ምኞትን በቀይ ተማተሀል በሚል በቀይ ካርድ ማሰናበታቸው ይታወሳል። ከካርዱ በኋላ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቅጣት ዝርዝርን በዛሬው ዕለት ይፋ ሲያደርግ የፋሲሉ የመሐል ተከላካይ የአራት ጨዋታ ዕገዳ እና የሦስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ማስተላለፍ ችሏል።
ይህንንም ተከትሎ ፋሲል ከነማ በጉዳዩ ላይ ያለውን ቅሬታ በዝርዝር ጠቅሶ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን እና ለፌድሬሽኑ የዳኞችኮሚቴ ሊያቀርብ መሆኑ ታውቋል። ይሁን እንጂ ከቪዲዮ ምስሉ ተመልክተው ዳኛው ራሳቸውን ከማረም ይልቅ በፃፉት ሪፖርት የተቀጣው ተጫዋቹ የተወሰነበት ውሳኔ ሊፀና እንደሚችል ተሰምቷል።



