“ለኢትዮጵያ ቡና በቋሚነት ተሰልፌም ተቀይሬም በተጫወትኩባቸው ግጥሚያዎች ክለቡን በአንዴ ተላምጃለሁ” ሀብታሙ ታደሰ /ኢትዮጵያ ቡና/

“ከቡና ጋር የሊጉ ሻምፒዮና መሆን፤ ለኮከብ ግብ አግቢ መፎካከር፤ ለብሔራዊ ቡድን መመረጥና ወደ ውጪ መጥቶ መጫወትን አልሜያለሁ”
“ለኢትዮጵያ ቡና በቋሚነት ተሰልፌም ተቀይሬም በተጫወትኩባቸው ግጥሚያዎች ክለቡን በአንዴ ተላምጃለሁ”
ሀብታሙ ታደሰ /ኢትዮጵያ ቡና/

“ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ ተዘዋውሬ በመጣሁባቸው የአጭር ጊዜ ቆይታዎቼ ባልተለመደ ሁኔታ ክለቡን በፍጥነት እና በአንዴ ልላመድ ችያለሁ፤ ለቡድኑ ተቀይሬም ሆነ በቋሚ ተሰላፊነት በተጫወትኩባቸው ጨዋታዎችም ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየቴን ተከትሎም ቡና ምን አይነት ቡድን እንደሆነና ሌሎች ተጨዋቾችም ወደዚህ ቡድን ሲመጡም ራሳቸውን በማሳመን በምን መልኩ ክለቡን ቶሎ ተግባብተው ለመላመድ እንደሚችሉም በሚገባ ያወቅኩበት ሁኔታ አለና ይህን ያገኘሁትን ልምድ ወደፊት ወደ ቡድኑ ለሚመጡ ተጨዋቾች ለማካፈል ዝግጁ ነኝ” ሲል የኢትዮጵያ ቡናው የኮሪደር ስፍራ ተጨዋች ሀብታሙ ታደሰ ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽን ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በመቀላቀል ጥሩ ለመጫወት የቻለው እና ቡዙዎችም የእግር ኳስ አፍቃሪዎችና የቡና ደጋፊዎች አድናቆትን እየሰጡት ያለው ሀብታሙ ወደ አዲሱ ቡድን ከመጣ በኋላ ስላሳለፋቸው የውድድር ጊዜ፣ የዘንድሮ የፕሪምየር ሊግ ውድድር ከመጀመሩ በፊት እያደረጉት ስላለው የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት፣ ስለ ቀጣይ ጊዜ የኳስ ህልሙና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስተንለት የሰጠንን ምላሽ በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል፤ ቃለ-ምልልሱን እንዲያነቡትም እነሆ ብለናል፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳሱ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ለወራቶች ዕድሜ ከተራቀ በኋላ አሁን ላይ ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ ችሏል፤ ያለፉት ጊዜያቶች በአንተ በኩል እንዴት ታለፉ?

ሀብታሙ፡-መጀመሪያ ላይ ከኳሱ የተለየንበት ጊዜ በጣም ረጅም ወቅትን ያስቆጠረ ነበርና ቤተሰቦቼን በስራ በማገዝ ነበር ያሳለፍኩት፤ ሌላ ጊዜ የማላገኘውን የእረፍት ወቅትም በሚገባ አግኝቼም ነበርና ለቤተሰባችን የሚጠቅመውን ስራም ስሰራ ነበር፤ ከዛ ውጪ ደግሞ እንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋች አይደለም ለወራት ለአንድ ቀን እንኳን መቀመጥ በአንተ አቋም ላይ የሚያስከትለው የራሱ የሆነ ተፅህኖም ስላለ እኔ ምንም አይነት እረፍትን ሳላደርግም ነበር ለዘንድሮ የውድድር ዘመን ራሴን በግሌ ሳዘጋጅ የነበረው፡፡

ሀትሪክ፡- ከኮቪድ ወረርሽኝ የእግር ኳሱ መቆም በኋላ ልክ አሁን ወደነበርንበት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስንመለስ ምን ሁኔታዎችን ነው ያስተዋልከው?

ሀብታሙ፡- በመጀመሪያ ኮቪድ ወደ አገራችን ገብቶ ስፖርታዊ እንቅሰቃሴው ሲቆም ብዙ ተጨዋቾቻችን የድብርት ስሜት ውስጥ ገብተው ነበር፤ እንደውም ኳሱ ስራቸው መሆኑን የረሱ ተጨዋቾችም ነበሩ፤ አሁን ላይ ደግሞ ወደነበርንበት ሁኔታ ስንመለስ ብዙ ነገር ነው ደስ እያለን ዝግጅታችንን እየሰራን የምንገኘው፤ ምክንያቱም በእግር ኳስ ጨዋታም ሆነ በማንኛውም የስራ መስክ ገንዘብን ስታገኝ ደስ የሚልህ ስራህን ደክመህ ስትሰራ ነው፤ ያለ ስራ ቁጭ ብለህ ገንዘብ ስታገኝ የድብርት ስሜት ውስጥ ጭምር የምትገባበት ሁኔታ አለና ኳስን እየተጫወትክ ገንዘብን ስታገኝ አህምሮህም ደስ ይለዋልና ይሄን ነው ለማስተዋል የቻልኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና የፕሪ-ሲዝን ዝግጅቱን ጀምሯል፤ እስካሁን ያለው የልምምድ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ሀብታሙ፡- ወደ ዝግጅታችን የገባነው ለወራቶች ቆይተን በመምጣት ነው፤ ከዛም አንፃር ከበድ ወዳለ ልምምድ እና ስራም ፈፅሞ አልገባንም፤ እስካሁን ቀለል ባለ መልኩ ነው እንደ ግል ሳይሆን በቡድን ስራ ላይ አተኩረን በጥሩ መልኩ እየተለማመድን የሚገኘው፡፡ አሁን ወደሙዳችን ስንገባና ሰውነታችን በደንብ ሲላመድ ደግሞ ወደ ጠንካራ ልምምዳችን እንገባለን፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡናን የእዚህ ዓመት የተጨዋቾች ስብስብ በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?

ሀብታሙ፡- ስለ ቡድናችን የተጨዋቾች ስብስብ አሁን ላይ በዝግጅት ወቅት ላይ ስለሆንን ብዙ የምለው ነገር አይኖርም፤ እንደዛም ሆኖ ግን ቡና ብዙ ነባር ተጨዋቾቹን ያለቀቀ እና በወጡት ተጨዋቾች ምትክም ክለቡ እነሱን ሊተኩ የሚችሉ ልጆችን ስላስመጣ በስብስቡ ብዙ የሚቸገር አይመስለኝም፤ ስላለን የተጨዋቾች ስብስብም የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ሲጀመሩም በደምብ ብንናገርም ነው የሚሻለው፤ ቡና ደግሞ በቡድን ስራ ላይ እንዴት ማጥቃት እንዳለበት እንዴትም መከላከል እንዳለበት አተኩሮ የሚሰራ እንጂ እንደ ግል የሚንቀሳቀስ ቡድን ስላልሆነም በሊጉ ውድድር ላይ ጥሩ የምንሆንም ነው የሚመስለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮው የሊግ ተሳትፎው ምን ውጤትን ለማምጣት አልሟል?

ሀብታሙ፡- የእኛ እልም አሁንም እንደ ሁልጊዜው ተሳትፎአችን ሁሉ ለዋንጫው ባለቤትነት መጫወት ነው፤ ለዛ ደግሞ ጠንክረን መስራት አለብን፤ ያን ስራችንንም ከወዲሁ ጀምረነዋል፤ ለእያንዳንዱ የሊጉ ጨዋታዎቻችንም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እና አሳማኝ በሆነ መልኩም ተጋጣሚዎቻችንን ለማሸነፍም እቅድን እየነደፍን ይገኛል፤ ይሄን ለማሳካት ከቻልንም ድሉ ወደእኛ ቤት መምጣቱም አይቀሬ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከአምናው ዝግጅታችሁ አንፃር ዘንድሮ ለየት ባለ መልኩ ይዞት የመጣው ነገር አለ?

ሀብታሙ፡- የለም፤ ከዛ ውጪ ግን ምንአልባት ለየት ያለው እና የነገረን ነገር ቢኖር የኮቪድ ወረርሽኝን ታሳቢ በማድረግ ከእግር ኳሱ ርቀን ከመምጣታችን አኳያ በምን መልኩ ራሳችንን ለፕሪ-ሲዝንና ለውድድር ማዘጋጀት እንዳለብን ነው ጠቃሚ የሚባሉ ሀሳቦችን ለሁሉም የቡድኑ ተጨዋቾች ያስተላለፈልን፡፡

ሀትሪክ፡- እንደ አንድ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋችነትህ የእዚህ ዓመት ላይ ምን ምን ነገሮችን ለክለቡ ለመስራት እቅድን ይዘሃል?

ሀብታሙ፡- የኮቪድ ወረርሽኝ ምንም እንኳን እንደተቀሩት ዓለማት ወደ አገራችን ቢገባም ባሳለፍኳቸው ሰባት እና ስምንት ወራቶች ያለምንም ማቋረጥ ልምምዴን ጠንክሬ በግሌ ስሰራ ቆይቻለው፤ አሁን ላይ ደግሞ የክለባችን የፕሪ-ሲዝን ልምምድ ስለተጀመረ ከእነሱም ጋር በጋራ የፕሪ-ሲዝን ዝግጅቴን እየሰራው እገኛለው፤ ከዛ በመነሳት ዘንድሮ በእዚህ መልኩ እየተለማመድኩ ያለሁት ያለ ምክንያት አይደለምና ከእዚህ ቡድን ጋር የሊጉን ዋንጫ ማንሳት እፈልጋለው፤ ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ራሴን ከሌሎች ተጨዋቾች ጋርም ማነፃፀር፣ የፕሪምየር ሊጉ የኮከብ ግብ አግቢ ተፎካካሪ ለመሆን፣ ለቡድን ጓደኞቼ የተመቻቹ የግብ ኳሶች ለማቀበል፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥና ወደ ባህር ማዶ ሄዶም መጫወት ዋንኛ ግቦቼ ናቸውና ለዛም ነው ቡናን በእዚህ ዓመት ላይ በጣም መጥቀም እና ማገልገልም የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ አምና እንደመቀላቀልህ ክለቡን በአንዴ ለመላመድ ቻልክ? ጥሩ ጊዜንስ አሳለፍክ?

ሀብታሙ፡- አዎን፤ እንደ እኔ ምልከታ ጥሩ ጊዜን ነው ያሳለፍኩት፤ ተቀይሬና በቋሚነት ተሰልፌ በገባሁባቸው የተለያዩ ጨዋታዎች ላይም አበረታች እና ጥሩ የሚባል የጨዋታ ወቅቶችንም ለማሳለፍ ችያለሁ፤ ሊጉ በኮቪድ ተቋረጠ እንጂ በጥሩ ብቃት /ቴምቦ/ ደረጃም ላይ የምገኝበት ሁኔታም ላይ ነበርኩና እንዳካሄዴ ለቡና ሌላም ውጤታማ ጥቅምን እሰጠው ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ፕሪምየር ሊጋችን በዲ.ኤስ.ቲቪ ሊተላለፍ ነው፤ ምን አልክ?

ሀብታሙ፡- ያ ለመሆን መቻሉ ዓለም ያየናል፤ ተጨዋቾቻችንም በእዛ ላይ ታይተው በውጪ ሀገር ክለቦች የመጠራት እድሉ ይኖራቸዋል፤ ከእዚህ ቀደም የእኛ ተጨዋቾች በሰዎች አማካኝነት በመጠራት ነበር የሙከራን እድል እንዲያገኙ የሚደረጉት አሁን ግን ጨዋታዎቹ በቀጥታ ስለሚታዩ በአሰልጣኞች እና በኤጀንቶች በቀጥታ የሚመለመሉበት ሁኔታ ስለሚኖር ይሄ ወጥቶ ለመጫወት ጥሩ አማራጭ ነው የሚሆነው፤ ከዛ ውጪም ጨዋታዎቹ የመተላለፍ እድሎቹ መፈጠር መቻላቸውም ሁላችንንም ተጨዋቾች ሁሌም ጠንክረን እንድንመጣም ያደርገናል፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ አሁን ላይ ለየት ያለ ነገርን ተመልክተሃል?

ሀብታሙ፡- አዎን፤ ለየት ያለውም ነገር ከእዚህ ቀደም ልምምድ ስንሰራ የነበረው በሰርቪስ ራቅ ወዳለ ቦታ እና ስፍራ ላይ በመሄድ ነበር፤ አሁን ላይ ግን እዛው ካምፓችን አጠገብ ነው ቡድናችን ሁሉንም ነገሮች በጥሩ ሁኔታ አሟልቶልን በመለማመድ ላይ የምንገኘው፤ ይሄ እና የቡድናችን ተጨዋቾች በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ራሳቸውን ለመጠበቅ እንዲችሉ በካምፕ ውስጥ ተገድበው እና ወደሌላ ቦታ ሳይሄዱም ተቀምጠው መገኘታቸው ሌላው ለየት ያለ ነገር ነውና በጊዜ ሂደት ሁሉም የቡድናችን ተጨዋቾች በካምፕ ውስጥ መኖርን መላመዳችን የማይቀር ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ያለ ደጋፊው ሲጫወት ለማየት መዘጋጀት ምን ሊመስል ይችላል?

ሀብታሙ፡- የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች በዲ.ኤስ.ቲቪ የሚተላለፍበት ሁኔታ መፈጠሩ በፊት በሜዳ ገብቶ ከሚመለከትን ደጋፊ በላይ እንደሚያየን እርግጠኛ ነኝ፤ ቡና ምንም እንኳን ጊዜው ባመጣው ወረርሽኝ ያለ ደጋፊው የሚጫወት ቢሆንም እኛ ግን ውድድሮቹን የምናደርገው ምንም እንኳን ያ ድባብ አለመኖሩ ሊከብድ ቢችልም እነሱ ሜዳ ላይ እንዳሉ አድርገን እና ግጥሚያዎቹንም ለማሸነፍ በሚያስችለንም መልኩ ነው የምንጫወተው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተፎካካሪዎቻችሁ እነማን ይሆናሉ?

ሀብታሙ፡- የሊግ ተፎካካሪዎቻችንን በተመለከተ ከወዲሁ ስም ጠቅሶ እንዲህ ብሎ ለመናገር አይቻልም፤ ሁሉም ቡድን ወደ ሜዳ የሚገባው ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ነው፤ ራሱን ብቁ አድርጎ የሚቀርብ ቡድንም የእዚያ ተጠቃሚ ይሆናል፤ በተለይ ደግሞ ከእዚህ ቀደም የሊጉን ዋንጫ ያነሱት ክለቦች የእኛ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ለመሆን በጣም ቅርቦቹ ይመስሉኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና የተጨዋችነት ቆይታህ ላይ የካምፕ የቅርብ ጓደኛህ ማን ነው?

ሀብታሙ፡- በኢትዮጵያ ቡና ካምፕ ውስጥ የቅርብ ጓደኛዬ ሰይፈ ዛኪር ነው፤ ከእሱ ጋርም ነው በአንድ ዶርም ውስጥ አብረን እየኖርን ያለነው፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ከመጫወት ውጪ በተለየ መልኩ ጊዜህን የምታሳልፍበት ሁኔታ አለ?

ሀብታሙ፡- አዎን፤ ሙዚቃ ማድመጥን በተለይ ደግሞ የሚያስጨፍሩ /ቢት/ ያላቸውን የሀገር ውስጥ እና የባህር ማዶ ዘፈኖችን መስማት በጣም እወዳለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ልዩ ባህሪዬ እና መታወቂያዬ የምትለው?

ሀብታሙ፡- ከሰዎች ጋር በፍጥነት እግባባለው፤ ከተግባባዋቸው እና ከአገኘዋቸው አካላቶችም ጋር ጥሩ ግንኙነት እና ገጠመኞችም አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ባሳለፍካቸው ህይወት ደስተኛ ነህ?

ሀብታሙ፡- አዎን፤ ሁሌም ደስተኛ ነኝ፤ በኳሱ እዚህ ደረጃ ላይ ላደረሰኝም ፈጣሪዬ አምላኬም ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በወልቂጤ ከተማ ክለብ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ ሁሌም ፈፅሞ የማትረሳው የተለየው ነገር ምንድን ነው?
ሀብታሙ፡- አንደኛው ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመቀላቀል በነበረን የከፍተኛው ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ በጥቂት ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ እድልን አግኝቼ የውድድሩ ሁለተኛው ኮከብ ግብ አግቢ የሆንኩበትን ሁኔታ እና ከዛ በመቀጠል ደግሞ በአንድ ጨዋታ ላይ እምብዛም በአገራችን ባልተለመደ ሁኔታ 6 ግቦችን ያስቆጠርኩበትን ሁኔታ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና መዝሙሮች ውስጥ ለአንተ ልዩ ስሜትን የሚሰጥህ ዜማ የቱ ነው?

ሀብታሙ፡- ሳዜም ነው ያደግኩት የሚለው፤ እሱን ስሰማ አንዳች ነገር ይነዝረኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች መካከል ሲጨፍሩ ለአንተ ልዩ የድባብ ስሜትን የሚፈጥሩብህ በየት በኩል ያሉት ናቸው?

ሀብታሙ፡- በሚስማር ተራ በኩል፤ ከእረፍት በኋላ ብዙ ጊዜ እነሱን ነበር የማገኛቸውና አጨፋፈራቸው በጣም ይማርካል፡፡

ሀትሪክ፡- የአገራችንን ሰላም እና ሉዓላዊነታችንን በሚያስጠብቁልን የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የህወአት የጥፋት ቡድን ሰሞኑን ጦርነት በመክፈት አደጋ አድርሷል፤ ይሄን እንዳደመጥክ ምን አልክ?

ሀብታሙ፡- ድርጊቱን ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት፤ ሰላም ሲኖርም ነው ሁሉም ነገርም ሊኖር የሚችለው፤ ይሄ የጥፋት ሀይል በራሱ ሀገር ሰራዊት ላይ፤ እንደዚሁም ደግሞ ወንድሞቹ ላይ ያደረሰው አደጋ ከወገን የሚጠበቅ ባለመሆኑ የተፈጠረው ሁኔታ በሁሉም አካል ዘንድ ሊወገዝ ይገባዋል፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሁሌም የእኛን ሰላም ለማስጠበቅ ተግቶ የሚሰራ ነው፤ በየበረሃው እና በየሸለቆ ውስጥም ራሱን መስዋህት በማድረግ ጭምር ሀገራችንን ከክፉ አደጋ ለመጠበቅም ሁሌም ዝግጁ በሆነበት ሁኔታ ባልተጠበቀ መልኩ ለደረሰበት አደጋ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅኩ ሁሌም ግን ይሄ ሰራዊታችን እኔም የማውቃቸው አባላቶች አሉና የአገሩን ባንዲራ ከፊት በማስቀደም ውዲቷን አገራችንን እየጠበቀ ላለበት እንቅስቃሴው ከፍተኛ አድናቆቴን ለመግለፅ እፈልጋለው፤ ፈጣሪ አገራችንንም ይጠብቅ ነው የምለው፡፡

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ የምታስተላልፈው መልህክት ካለ?

ሀብታሙ፡- የእግር ኳሳችን በኮቪድ ወረርሽኝ ተቋርጦ ነበር፤ አሁን ላይ ዝግጅት ተጀምሯል፤ ወደ ኳሱ በመመለሳችንም ሁላችንም ደስ ብሎናል፤ ከእዚህ በኋላ እንደ ክለብ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ልናስብ የሚገባን ወደ ጠንካራ የውድድር ተፎካካሪነት ስለመመለስ ነው፤ የአሁን ሰዓት ላይ የብሔራዊ ቡድናችንን ውጤት በሚገባ እየተመለከትን ነው፤ በኮቪድ ከውድድር ርቀን እንደመምጣታችን በነበርንበት ብቃት ላይ አልተገኘንም ነበርና በአቋም መለኪያው ጨዋታ ላይ ድካም ይታይብን ነበር፤ ይሄ የሚፈጠረው በእረፍቱ ወቅቱ አብዛኛው ተጨዋች ልምምዱን በተገቢው መልኩ ለውድድር በሚያዘጋጀው ደረጃ አሟልቶ ስላልሰራ ስለሚሆን ከእዚህ በኋላ ግን እያንዳንዱ ተጨዋች ስራውን ሁሌም በማክበር እና ጠንክሮም እየሰራ በመሄድ የሚፈለገውን ውጤት እንድናመጣ ከወዲሁ መዘጋጀት ነው የሚኖርብን፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website