ሀብታሙ ታደሰ የኢትዮጵያ ቡና የውጤታማነት ምስጢር
የኢትዮጵያ ቡና የውጤታማነት ሚስጥር
ሀብታሙ ታደሰ /ኢትዮጵያ ቡና/
በመሸሻ ወልዴ
ለኢትዮጵያ ቡና ከወዲሁ የድል ግቦችን ማስቆጠር ጀምሯል፤ ይሄን ተንተርሶም በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ውድድር ላይ በኮከብ ግብ አግቢነት የቅድሚያ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት የቡድን አጋሩ አቡበከር ናስር እና ከሌላኛው የወልቂጤ ከተማው ተጨዋች ያሬድ ታደሰ እና የባህር ዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ ጋር ስሙን ሊያሰፍርም ችሏል፤ ኢትዮጵያ ቡናን ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ከወልቂጤ ከተማ ክለብ በመምጣት የተቀላቀለው ሀብታሙ ታደሰ ከፋሲል ከነማ እና ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ለቡና ውጤታማነት ጎል ከማስቆጠር ባሻገር ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን ይህን ተጨዋች ስለ ቡድኑ የሊግ አጀማመር፣ እያስመዘገቡት ስላለው የውጤታማነት ሚስጥር፣ የድል ጎሎችን ስለማስቆጠሩ፣ ስለ ቡድኑ ቀጣይ ጉዞ ከሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ቆይታን አድርጎ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሾችን ሰጥቷል፤ ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናን ስኬታማ የውድድር አጀማመር አስመልክቶ
“ባለፉት ሶስት ጨዋታዎቻችን በእንቅስቃሴም ሆነ ከውጤት አንፃር ከጨዋታ ወደ ጨዋታ በተጓዝንበት ሰዓት ጥሩ ለውጦችንና መሻሻሎችን በቡድናችን ላይ ልንመለከት የቻልነው በአሰልጣችን የተሰጠንን ታክቲክ በሜዳ ላይ ልንተገብር ስለቻልን ነው፤ ለውጤታማነታችንም ሚስጥር ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደ ሜዳ ስንገባ የማሸነፍ መንፈሳችን በጣም ከፍ ያለ መሆኑ ሊጠቅመንም ችሏል፤ ይሄን ስናይ ቡድናችን ከአምናው በብዙ መልኩም መለወጡንም ያሳየ ሆኗል”፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን በምን መልኩ ከአምናው አንፃር እንጠብቀው
“ዘንድሮ በብዙ መልኩ እየተሻሻልንና ችግራችንንም በመቅረፍ መጥተናል፤ በተለይ ደግሞ የምንከተለው የጨዋታ ታክቲክ ላይ ወደ ሜዳ ስንገባ ያሉብን ክፍተቶች በጣም ከባድ ያልሆኑ ስለሆኑ በቀጣይ ግጥሚያዎቻችን ላይ ምርጡን እና የተሻለ የሚባለውን ቡናን የምናስመለክት ይሆናል”፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ስላሸነፉበት መንገድ
“ጨዋታዎቹን ያሸነፍነው በእያንዳንዱ የቡድኑ ተጨዋቾች ውስጥ ከፍተኛ የጨዋታ ፍላጎት፣ መነሳሳት እና ወደ ሜዳ ከገባንበት ሰዓት አንስቶም ያለንን አቅም ሁሉ ሰጥተን ስለምንጫወት ነው፤ በተለይ ደግሞ ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረን ጨዋታ በጎዶሎ ልጅ ሆነን ያሸነፍነው ግጥሚያ ድሬዳዋ ከተማንም ድል እንድናደርግ ጨዋታው ትልቅ የሞራል ስንቅም ሆኖናልና ይሄ ጉዞአችን ቀጣይነትም ይኖረዋል”፡፡
ከሰበታ ከተማ ጋር ስለሚኖራቸው ቀጣይ ጨዋታ
“ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ላይ በሚያደርገው ጨዋታው የሚያከብደውም ሆኖ አውርዶ የሚያየው ቡድን አንድም የለም፤ ከማንም ቡድን ጋር ለመጫወት ወደ ሜዳ ሲገባም ቀጣይነት እና ዓላማ ያለውን የአሰልጣኙን ካሳዬ አራጌን የጨዋታ ታክቲክ በመከተል ከግጥሚያው 3 ነጥብን ይዞ ለመውጣት ተዘጋጅቷል”፡፡
ለኢትዮጵያ ቡና የድል ጎልን ማስቆጠር ስለመጀመሩ
“በእዚህ መልኩ የውድድር ዘመኑን መጀመሬ ለእኔ ጥሩ የሚባል ነው፤ ከእዚህ በመነሳትም በቀጣዩ ጊዜ በርካታ ግቦችን ለክለቤ የማስቆጥር ይሆናል”፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ቆይታው ላይ ዘንድሮ ያለመው
“የመጀመሪያው ከቡድን አጋር ጓደኞቼ ጋር የሊጉን ዋንጫ ማንሳት መቻል ነው፤ በመቀጠል ደግሞ በሊጉ ጅማሬዬ ሶስት ግቦችን ከወዲሁ ማስቆጠር ችያለሁና ይሄን በማስቀጠል ዘንድሮ ኮከብ ግብ አግቢ መባልን እፈልጋለሁ”፡፡
ለኢትዮጵያ ቡና የሚያሰጋው እና የሚያስፈራው ቡድን
“አሁን ላይ ከሊጉ ጅማሬ አንፃር እንዲህ ማለት ባይቻልም ቡናን የሚያሰጋውም ሆነ የሚያስፈራው ቡድን ማንም የለም፤ ምክንያቱም ቡና ሁሌም ወደ ሜዳ የሚገባው ሁሉንም ቡድኖች በእኩል መልኩ አይቶ እና ከተጋጣሚዎቹ ላይም 3 ነጥቦችን ለመውሰድ የሚጫወት ቡድን ስለሆነ ነው”፡፡
ከኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ ምን ይጠበቅ?
“ሻምፒዮንነት ነዋ! ምክንያቱም ቡድኑ ሁሌም የሚጫወተው ለዛ ስለሆነና ከዛ ያነሰ ውጤት ማስመዝገብም በክለቡ ዘንድ የሚታሰብ አይደለምና፤ ስለዚህም ይህን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ከፍ አድርገን በማንሳት የመጪው የውድድር ዘመን ላይ ደግሞ በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ መካፈልን እንፈልጋለን”፡፡

እናጠቃል…
“ኢትዮጵያ ቡና አሁን ላይ የያዘው የጨዋታ እንቅስቃሴ ዓላማ ያለው፣ ቀጣይነት ያለው ከዛ ባሻገር ደግሞ ግምታዊ ያልሆነ እና ብዙ ቡድኖች ቢከተሉት ለሀገር እግር ኳስም እድገት መሻሻል ጠቃሚ ስለሆነ በእዛ መልኩ ቢጓዙ እና ከአየር ላይና የጥለዛ መልክ ካለው አጨዋወት ቢወጡ ጥሩ ነው፤ ይሄን ካልኩ በቡና ቡድን የተጨዋችነት ቆይታዬ አሁን ላይ ወደ እግር ኳሱ ከመጣሁበት መንገድ እና ለእግር ኳሱም ከከፈልኩት መስዋህትነት አኳያ ለቡድኑ በመጫወቴ ደስተኛ ብሆንም ቡድኑን ግን ገና በምፈልገው መልኩ አላገለገልኩም፤ ከዛ ውጪ አሁን ላይ ለቡና ግብ ማስቆጠር ብጀምርም ራሴን አዘናግጄ በሚያስኮፍሰኝ ደረጃም ላይ አልቀመጥምና ቡናን በብዙ መልኩ ለመጥቀም ዝግጁ ነኝ”፡፡
አስተያየት ይስጡ