በይስሐቅ በላይ
የሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳል? አልኩት…. ከመልሱ ሣቁን አስቀደመ… ወዲያው አስከተለና “መጠርጠርህ…! ከፋሲል ውጪ ማን ዋንጫውን ሊያነሣ?….” ለዋንጫ የሚፎካከሩ ክለቦችስ?… ጥያቄዬን አስከተልኩ… “እሱን በሂደት የምናየው ነው የሚሆነው፤ እኔ እስከማውቀው ግን የዘንድሮ የሊጉ ሻምፒዮን ከፋሲልና ከፋሲል ውጪ ማንም የለም” በማለት አስገራሚ ምላሹን ሰጥቶኛል…በዚህም ሳላበቃ እሺ የሊጉ ክስተትና ኮከብስ ማን ይሆናል? አልኩት… አሁንም “ሱራፌል ነዋ” ብሎ ፍርጥም ያለ ምላሽ ሰጠኝ፤ የዛሬው እንግዳዬ የፋሲል ከነማና የኢትዮጵያ ብ/ቡድን የመሀል ሜዳ ሞተር የሆነው አመለሸጋው ሱራፌል ዳኛቸው፡፡
“ያለፉት ሁለት አመታት ለዋንጫ ደርሰን ተመልሰናል… ዘንድሮ ግን ያንን ቁጭታችንን የምናብስበት… በታሪካችን አይተን የማናውቀውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ከፍ አድርገን የምናነሳበት አመት ነው” …በማለት ለሀትሪክ ኤክስክዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ሃሳቡን ያካፈለው ሱራፌል ዳኛቸው በዚህም ሣያበቃ አቋምህ ወርዷል የሚለውን ሃሣብ ትቀበለዋለህ በሚል ለቀረበለት ጥያቄና በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ስለተቀዳጁት ድል፣ በኢትዮጵያ ቡና ስለደረሰባቸው ሽንፈት፣ ስለ ኢትዮጵያ ብ/ቡድን፣ ስለ ኒጀሩ ሽንፈትና የ3ለ0 ድላቸው፣ ስለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ… የእረፍት ጊዜውን ሰዉቶ ከዚህ በታች ባለው መልኩ አጫውቶታልና አብራችሁን ሁኑ…
ሀትሪክ፡- የቴሌግራም ቻናልህን ፕሮፋይል ስመለከት በተደጋጋሚ የልጅህን ፎቶ ነው ፕሮፋይል ፒክቸር የምታደርገው…ለእሷ ያለህን ፍቅር የምትገልፅበት አንደኛው መንገድ ነው ልበል…?
ሱራፌል፡-…(እየሳቀ)…እናንት ጋዜጠኞች የማትጎረጉሩት…የማታዩት ነገር የለም…ማማዬን በጣም ነው የምወዳት…ለእሷ ያለኝን ፍቅር በቃላት መግለፅ ይከብደኛል…የእኔነቴ ምልክትም መገለጫም ስለሆነች ነው… በአገኘሁት አጋጣሚ ስሟን ከፍ የማደርገው ምስሏንም የምጠቀመው…፡፡

ሀትሪክ፡- …አሁን አሁንማ…ጊዜ ስታገኝ ሩጫህ ሁሉ ወደ ቤት እንዲሆን አስገድዳሃለች…?ለመሆኑ ልጅህ ስንት አመት ሞላት?
ሱራፌል፡- …(እየሳቀ)…በፊትም ወደ ቤቴ መሮጥን ነበር የምወደው…..ማማዬ ከመጣች ግን ፍቅርዋ እያሯሯጠ ይወስደኛል…ጊዜ አግኝቼ ከእሷ ጋር ለመጫወት…እሷን ለማቀፍ በጣም ነው የምጓጓው….አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ማማዬ አድጋልኛለች…አንድ አመት ከአንድ ወር አካባቢ ሆኗታል…በእሷ በጣም ደስተኛ ነኝ…ይህቺን የመሰለች ቆንጆ ልጅ አባት ያደረገችኝ ባለቤቴም የዚህ ደስታ ምክንያት ናትና እሷንም በዚህ አጋጣሚ አመሰግናታለሁ…

ሀትሪክ፡- …ትዳር የተመቸህ እንደሆነ ንግግርህም…ስሜትህም ያሳብቃል…እስከዛሬ ትዳርና ስፖርተኛ አብሮ አይሄድም የሚለው አባባል አንተ ጋር ቦታ ያገኘ አይመስልም…?
ሱራፌል፡- …ትክክል ነህ…ትዳር ብዙ ፀጋዎች…ብዙ በረከቶች እንዳሉት እኔ ህያው ምስክር ነኝ…በእኛ ሀገር እግር ኳስ ተጨዋችነትና ትዳር አብሮ አይሄድም ሲባል እሠማለሁ…እንደውም ይሄ ነገር ተገልብጦ ትዳርና እግር ኳስ ተጨዋችነት አብሮ መሄድ ያለበት በእኛ ሀገር ነው ባይ ነኝ…በትዳር ስትታሰር ነው በፕሮግራም የምትመራ ጥሩ ስፖርተኛ የምትሆነው…ከዚህ በፊት በዚህ አመለካከት ብዙ ተጨዋቾች ተሸውደዋል…አሁን ግን ያ አባባል አሮጌ የሆነ…በዚህ ዘመን ላይ የማይሰራ ይመስለኛል…በጥሩ ብቃት ለመጫወት፣ፕሮፌሽናል ለመሆን፣የምትፈልገው ደረጃ ላይ ለመድረስ በትዳር መታሰር መልካም ይመሰለኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- …ስለዚህ ያላገባችሁ አግቡ እያልክ ተጨዋቾችን እየመከርክ ነው…?
ሱራፌል፡- …እኔ ሌሎችን የመምከር አቅሙ ያለኝ ሰው አይደለሁም…ግን ካገኘሁት ትርፍ፣ካየሁት ነገር በመነሣት ነው ምክሬን ነው ለማካፈል እየሞከርኩ ያለሁት…ተጨዋቾች በትዳር ቢታሰሩ እንደ እኔ ተጠቃሚ…ደስተኛ ይሆናሉ በማለት ነው ያገኘሁትን ነገር የማጋራቸው…በአጭሩ የእኔን መንገድ ይከተሉ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ሱራፌል ባለፈው አመት ወደ ትዳር ዓለም ሲገባ አቋሙ ጥሩ ነበር…ዘንድሮ ግን አቋሙ እንደባለፈው አመት አይደለም…የመውረድ ነገር ይታይበታል…ብለው ጥያቄ ለሚያነሱብህ መልስ አለህ…?
ሱራፌል፡- …(እየሳቀ)…የሐሙሱን ጨዋታ ጀምሮ ገና ሶስት ጨወታ ነው ያደረግነው…ገና ብዙ ጨዋታዎችም ይቀሩናል…“ሱራፌል አቋሙ ወርዷል” የሚል ድምዴሜ ላይ ለመድረስ ገና ጠዋት ይመስለኛል…በደንብ ከታየን በኋላ ቢባል አስተያየት ቢሰጥ ሰዎችን አያስገምትም…ግን ይሄንን መሰሉን አስተያየት ስሰማ አንድ የምረዳው ነገር አለ…
ሀትሪክ፡- …ምን…?
ሱራፌል፡- …ምናልባት ለደጋፊዎቼና ለተመልካቾች ካስለመድኩት ነገር ያጎደልኩት ነገር ቢኖር ነው ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል… ደጋፊዎቼ ከእኔ በጣም ብዙ ጠብቀው ይሆናል…ያንን የጠበኩትን ነገር ሲያጡ አቋምህ የወረደ ያህል ሊሰማቸው ይችላል…ደግሞም ሁሉም እንዲረዳን የምፈልገው አንድ ነገር በየቀኑ ልምምድና ውድድር ማድረግ የለመደው ሰውነታችን ከሰባት ወር በላይ ከዚህ ሲስተም ወጥቶ ቆይቶ ነው አሁን የተመለሰው…ይሄ በራሱ ይፈትናል…ወደ ቀደመ…ወደ ሪትሙ እስክትመለስ የራሱን ጊዜ ይፈልጋል…እነዚህ ችግሮች ተዳምረው ተመልካቹ ብቻ ሣይሆን እኔም ወደምፈልገው ሱራፌል ለመምጣት የተቸገርክበት ሁኔታ ተከስቶ ይሆናል…አሁን ግን ሁሉም ማየት ወደሚፈልገው ሱራፌል ለመምጣት እየጣርኩ ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ፋሲል ከኮንፌዴሬሽን ካፕ ውጪ ሆነ፣በኢት.ቡና በ10 ተጫዋቾች 3ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ተሸንፈ፣ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም ከባለፈው አንፃር ትንሽ የመውረድ ነገር ይታይበታል…በሚል የሚሰነዘረውን አስተያየትስ ትቀበላለህ…?
ሱራፌል፡- …አሁንም እንደዚህ አይነት አስተያት ለመጠት ገና ጠዋት ነው ባይ ነኝ…እንዳልኩህ ከሰባት ወር በላይ ተቀምጠን ነው ሁላችንም ወደ ውድድር የመጣነው…ያ ትኩረታችንን፣የጨዋታ ስሜታችንንም ነጥቆን ቆይቷል… በጣም ጥሩ፣እንከን አይወጣልንም ብዬ ለመከራከር ባልደፋርም ለክፉ በሚሰጥ ደረጃ ላይ ነን ግን ማለት ይቸግረኛል… ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻልን መምጣታችንን…የበለጠ እየተሻሻልን እንደምንሄድ ግን እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ…ደግሞም እኮ በሊጉ ጀማሬ ለሻምፒዮንነት ትልቅ ግምት የተሰጠውን ቅ/ጊዮርጊስን የሚያክል ቡድን ማሸነፋችንንም አትረሣ…፡፡
ሀትሪክ፡- …እንዳልከው በሊጉ ጀማሬ ቅ/ጊዮርጊስን አሸንፋችኋል…ድሉ የተለየ ስሜት ይፈጥራል…?
ሱራፌል፡- …ቅ/ጊዮርጊስ በሀገሪቱ እግር ኳስ የገዘፈ ታሪክና ውጤት ያለው፣በተደጋጋሚ የሊጉን ዋንጫ ያነሣ ክለብ መሆኑን ስታይ በዚህ ደረጃ ያለን ቡድን ማሸነፍ ድሉ በውስጥህ የተለየ ስሜት እንዲፈጠር ያደርጋል… ቅዱስ ጊዮርጊሶችም እኛም ላለፉት ሁለት አመታት በጠንካራ ፉክክር ውስጥ ሆነን ነን ነው ያሳለፍነው… ጊዮርጊሶችም ላለፉት ሁለት አመታት ከዋንጫ ርቀው…እኛም ላለፉት ሁለት አመታት አይተን የማናውቀውን ዋንጫ ለማሳካት ቆርጠን የገባንበት ውድድር በመሆኑ ክብደት ያለው ጨዋታ ነበር ያደረግነው…በሁለታችንም በኩል ጥሩ የመሸነፍ ፉክክር አድርገናል…ትልቅ ስም፣ትልቅ ውጤት ያለውን፣ለዋንጫም ከፍተኛ ግምት የተሰጠውን ቡድን ያውም በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ማሸነፍ ድሉ ድርብ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን እኮ በሁለተኛው ሣምንት ጨዋታ በ10 ተጨዋቾች በተጫወተው ኢት.ቡና የ3ለ1 አስከፊ ሽንፈትን ተጎንጭታችኋል…ሽንፈቱስ ምን መልዕክት አስተላልፈልህ…?…
ሱራፌል፡- …እውነት ለመናገር ለማመን የሚከብድ ነበር…ሽንፈቱንም ያልጠበቅነው ነው…በጨወታው ጥሩ ጀማሬ አድርገን ነበር…ቀደመው ቢያገቡብንም እኛም ወዲያው አስቆጥረን አቻ ሆነን ነበረን…ግን አንድ ተጨዋች ከወጣባቸው በኋላ መዘናጋታችንም ለሽንፈት የዳረገን ይመስለኛል…የአንድ ተጨዋች ብልጫችንን እንዲሁም ያገኘናቸውን እድሎች አለመጠቀማችን የእነሱን በራስ የመተማመን ስሜት የጨመረው ይመስለኛል…ሌላው በጠዋት ልምምድ እንጂ የነጥብ ጨዋታ አድርገን አናውቅም…ያ በራሱ ግራ የመጋባት የመቀዛቀዝ ስሜት ፈጥሮብናል…አንደኛው ተፅዕኖም ነበር…ይሄን የምለው ሽንፈትን ላመቀበልና ምክንያት ለመደርደር አይደለም…በእነዚህ ችግሮቻችንን ተሸንፈናል…እኔ እንደውም አሁን ላይ በኢት.ቡና እንኳን ተሸንፈን ነው የምለው…
ሀትሪክ፡- …እንኳን…ተሸንፍን…?…ምን ማለት ነው አልገባኝም…?
ሱራፌል፡- …እንኳን ተሸነፍን ያልኩህ…ሽንፈትን የምወድ ሰው ሆኜ አይደለም…ግን በኢት.ቡና የደረሰብን ሽንፈት የተማርንበትና ራሳችንን በደንብ እንድንፈትሽ ያደረገ ሽንፈት ስለሆነ ነው…እንኳን ተሸነፍን ያልኩህ…መዘናጋት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል በደንብ ያየንበት ሽንፈት ነው….ያ ሽንፈትም ነው በቀጣይ ከጅማ አባጅፋር ጋር በነበረው ጨወታ በትኩረት እንድጫወትና በሰፊ ውጤትም እንድናሸንፍ የረዳን ብዬ ነው የማምነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከእስከዛሬዎቹ የተለየ የሚያደርገውን ነገር አይተህበታል…?
ሱራፌል፡- …በብዙ መልኩ የተለየ ነገር አለው…የመጀመሪያው የተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር ከ16 ወደ 13 ዝቅ ብሏል…የውድድሩ ፎርማትም እስከዛሬ ከነበረው የተለየም ነው…ውድድሩ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌቪዥን ስርጭት በDSTV አማካኝነት ያገኘበት…በሱፐር ስፖርት ለመላው አለም የመተላለፍ እድል ያገኘበት ነው…ከዚህ በተጨማሪም የተሻለ መሆን የተሻለ ገንዘብ የሚገኝበት መሆኑ፣ከ13 ቡድኖች ሶስት ቡድኖች የመውረድ እድል ስለሚያጋጥማቸው ሁሉም በጥንካሬ የቀረቡበት መሆኑ የዘንድሮው የተለየ ነው ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- …ፋሲል ዘንድሮ ወደ ውድድር የመጣው በዋናነት ለምንድነው ብልህ ምን ትመልስልኛለህ…?
ሱራፌል፡- …ምንም ጥያቄ የለውም…አለማችን አንድና አንድ ብቻ ነው…እሱም የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ማንሣት…ላለፉት ሁለት አመታት ዋንጫው ጋ ደርሰን የተመለስንበት የቁጭት ታሪክ አለን…ዘንድሮ ዋንጫውን በማንሣት ሻምፒዮን በመሆን ያንን ቁጭታችንን በደስታ ለመቀየር ነው ወደ ውድድር የገባነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …ሱራፌል በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ለዋንጫው ከፍተኛውን ግምት የሚሰጠው ለማነው…?…ለቅዱስ ጊዮርጊስ…?…ለኢትዮጵያ ቡና…?…ለሀድያ ሆሳዕና ወይስ…
ሱራፌል፡- …አረ በቃህ…!…የብዙ ክለቦችን ስም በመጥራት አትድከም…ለዋንጫው ከፍ ያለውን ግመት የምሰጠው ለፋሲል ከነማ ብቻ ነው…ከፋሲል ውጪ ለማንም አልሰጥም…(በጣም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ከፋሲል ውጪ ለዋንጫ የሚፎካከሩ ሌሎች ክለቦች የሉም እያልክ ነው…?
ሱራፌል፡- …እሱን በሂደት የምናየው ነው የሚሆነው…አሁን ባለው ሁኔታ ጠንካሮች ናቸው…ያልተገመቱ ቡድናች ጠንካራ ፉክክር እያሳዩ እያየን ነው…ለእኔ ግን በአሁን ሰዓት ለዋንጫው የሚወጫወተው ብቸኛ ቡድን ፋሲልና ፋሲል ብቻ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …ከዋንጫው ባልተናነሰ ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር ዘንድሮ ጠንካራ የሚሆን አይመስልህም…?
ሱራፌል፡- …እውነት ለመናገር ሁሉም ነገር በብዙ መልኩ ከባድ ነው…ላለመውረድ የሚታገል ይኖራል…ለዋንጫ የሚፎካከርም እንደዛው…የተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር ከ16 ወደ 13 መውረድ ዋንጫውን ለማንሣት ላለመውረድ የሚደረገውን ትንቅንቅ የከበደ ያደርገዋል…ከ13 ሶስት ቡድን መውረድ ግን የበለጠ ከባድ ይመስለኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- …ዘንድሮ ከፋሲል ከነማ የውድድሩ ክስተት ወይም ጎልቶ የሚወጣ ተጨዋች ማን ይሆናል ትላለህ…?
ሱራፌል፡- …ጠንክሮ የሰራ…ጎልቶ ይወጣል ብዬ አስባለሁ…

ሀትሪክ፡- …ክስተት ሊሆን ይችላል ብለህ በስም የምትጠቅሰው ተጨዋች ፈልገህ አጥተኻል ማለት ነው…?
ሱራፌል፡- …(ሣቅ)…ራሱን በራሱ አሞገስ ካላስባልከኝ በስተቀር…እኔው ራሴ ጠንክሬ ሠርቼ ራሴው የውድድሩ ክስተት ልሆን እችላለሁ ብዬ አስባለሁ…ከአምናው የተሻለውን ሱራፌል ለማሳየት ክስተት ለመሆን ተጨማሪ ትሬይኒንግ ሣይቀር እየሠራሁ…ይሄንን አጠንክሬ ከቀጠልኩ ክስተት ከመሆን የሚያግደኝ ይኖራል ብለህ ነው…?…(በጣም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ባለፈው አመት የሊጉ የኮከብ ተጨዋችነት ክብርን አግኝተሃል…ዘንድሮ ይሄንን ክብር ታስጠብቃለህ…?…ወይስ ለሌላ ተጨዋች አሳልፈህ ትሰጣለህ…?
ሱራፌል፡- …አንዴ የገባ ነገር አይወጣም…(በጣም ሳቅ)…የክለቤ ጉዳይ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ቢሆንም…የአምናውን የኮከብነት ክብሬን ማስጠበቅ ነው አላማዬ…የኮከብነት ክብሩ ዝም ብሎ በመመኘት ብቻ እንደማይመጣ ስለማውቅ ጠንክሬ ሠርቼ ክብሬን አስጠብቃለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ውድድሮቹ በDSTV መተላለፋቸው በእግር ኳሱ ላይ የሚጨምረው ነገር አለ ትላለህ…?
ሱራፌል፡- …በጣም ብዙ ነገር ይጨምራል…አሁን እግር ኳሳችን፣የእያንዳንዳችን እንቅስቃሴም ለአለም እየታየ ነው…ያለህን ነገር በሙሉ ለአለም እግር ኳስ የምታሳይበትን መድረክን ነው DSTV የፈጠረልን…ከዚህ ውጪ ደካማና ጠንካራ ጎናችንን በድጋሚ የምናይበት ራስህን ለማሻሻልም ሆነ ያለህን ጠንካራ ጎን ይበልጥ ለማጎልበት በድጋሚ የምታይበት እድልንም የሚፈጥር ጥሩ አጋጣሚ ነው…ሌላው ጨዋታው በመላው ሀገሪቱ የሚታይ በመሆኑ ወጣቶች እንደ እኛ ለመሆን ልምድም ተሞክሮም እንዲያገኙም የሚሰጠው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም… በአጠቃላይ ከተጠቀምንበት DSTV ይዞልን የመጣው ወርቃማ የሚባል እድል ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …በካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አምናም ዘንድሮም ከአንድ ዙር ማለፍ አልቻላችሁም…በጊዜ ነው ከውድድር የወጣችሁት…ከዚህ አንፃር ለዚህ ውድድር ገና አልበቃችሁም፣አልደረሳችሁም ማለት ነው…?
ሱራፌል፡- …እንደዛ እንኳን ብሎ ማሰብስ ህተት ነው…የአምናውን ውድድር ካየኸው የልምድ ችግር እንደጎዳን በግልፅ ይታይብን ነበር…ዘንድሮ ግን ብዙ ነገሮችን አሻሽለን፣በስለን የተገኘንበት ውድድር ነበር…ጥቃቅን ነገሮች ዋጋ አስከፈሉን…እንጂ ጨዋታው ኢንተርናሽናል ሁሉ አልመስል እስኪለን…የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የምናደርግ ያህል ተሰምቶን በጣም ተጨነን ነበር፡፡ የተጫወትነው…በጣም ብዙ ሙከራዎችንም አድርገናል…የቱኒዚያው ሞንስቴር በጣም ጠንካራ ቡድን ነው…በጣም ሀብታም…ጥሩ ፋሲሊቲ ያለው…ብዙ ነገር የተሟላለት ትልቅ ቡድን ነው…ያም ቢሆን ግን ብዙ አልበለጡንም…ብዙ ሞክረን…ሁለት ግብም አስቆጥረን ነበር…ግን አጨራረሳችንን ማሰመር ባለመቻላችን…ወደ ቀጣዩ ዙር አላለፍንም እንጂ ካለፈው አመት ብዙ ልምድ ወስደን፣ብዙ ተሽለን የታየንበት፣ብዙ የተማርንበት ውድድር ነበር ማለት እችላለሁ…

ሀትሪክ፡- …2ለ0 እየመራችሁ ለማለፍ የተሻለ እድል በእጃችሁ ይዛችሁ ያንን ማስጠበቅ አለመቻላችሁ ከውድድሩ ትምህርትን ሳይሆን ትልቅ ቁጭትን አትርፋችሁ እንድትወጡ ያደረጋችሁ አይስልህም…?
ሱራፌል፡- …እውነት ለመናገር ከውድድሩ ያገኘነው ትምህርት የበዛውን ቦታ ቢይዝም…መቆጨታችን ግን አልቀረም…ምክንያቱም በቱኒዚያ የደረሰብንን ሽንፈት በአዲስ አበባ ቀልብሰን የማለፍ እድላችንን ብናሰፋም ያንን አስጠብቀን ባለመውጣታችን ትልቅ ቁጭት በውስጣችን እንዲፈጠር አድርጓል…
ሀትሪክ፡- …የ2ለ0 ውጤታችሁን ያላስጠበቃችሁበትን ምክንያት ምን እንበለው…?
ሱራፌል፡- …ያው እንደ ተመለከታችሁት…ቱኒዚያዎች ጎል ያስቆጠሩብን ባለቀ ሰዓት ነው…ረዥም ሰዓት 2ለ0 ስለመራን ያለቀ ያህል ቆጥረን ተዘናግተናል…ከዚህ ውጪ በወቅቱ ሜዳ ላይ የተፈጠረው የከፋ ጉዳት የሁላችንንም ትኩረት ሰርቆት ነበር…በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ጨዋታው ለ15 ደቂቃ ያህል መቋረጡ…ከአሸናፊነት መንፈስ (Wining Sprit) ውጪ እንዳገኘውን ትኩረታችን ወደ ጉዳቱ እንዲያዘነብል የራሱን ተፅዕኖ አድርጎብናል ማለት እችላለሁ…ጉዳቱ ከፈጠረብን የትኩረት መሰረቅ በተጨማሪ በወቅቱ የነበረው አየር በጣም ቀዝቃዛ መሆኑ ተዳምሮበት ከመጀመሪያው የሞቀ ስሜታችን የወጣንበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል…ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፍ ታሪክ መስራት የምንችልበት እድል ባለቀ ሰዓት አንድ ጎል አግብተውብን መሸነፋችን ትልቅ ቁጭትና ፀፀትን በውስጣችን ፈጥሮብናል…መዘናጋታችን ግብ እንድናስተናግድ አድርጎናል…በጨረሻም ከውድድሩ ውጩ አድርጎናል…አሁን ሁሉም አልፏል…ለበጎ ነው ብለን መውሰድና ለቀጣይ ከዚህ ተምረን መዘጋጀት ነው ቀጣዩ ሥራችን ሊሆን የሚገባው…፡፡
ሀትሪክ- …ሱራፌል በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱም…በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ብ/ቡደን ውስጥ ነበር…ምን ልዩነትና አንድነት አየበት…?
ሱራፌል፡- …ኢንስትራክተር አብርሃም በነበረበት ሰዓት የነበሩ ተጨዋቾች ላይ ጥቂት ተጨምረው ነው የውበቱ ስብስብ ውስጥ የተካተቱት…አብርሃም በነበረበት ሰዓት ለማሸነፍ የነበረው ጥረት፣ለሀገር የመልፋት፣አንድ ነገር የመስራት ስሜቱ በጣም ደስ ይል ነበር…በአብርሃም ጊዜ የነበረው ፍቅርና ስሜት ነው በውበቱ ስብስብ ውስጥም የተደገመው…ከዚህ አንፃር በሁለቱም ጊዜ ያለው ነገር ተመሳሳይነት ያለው ነው…አሁንም በውበቱ ጊዜ ተጫዋቹ ገብቶት ነው በደንብ እየሠራ ያለው…አንድነት፣ፍቅር ሲኖር ነው ማሸነፍ የሚመጣው…ይሄ ነገር ሜዳ ላይ ታይቷል…
ሀትሪክ፡- …ኒጀርን አዲስ አበባ ላይ 3ለ0 ማሸነፋችሁን የተመለከቱ በኒጀር ላይ መሸነፍ ሣይሆን ማሸነፍ ነበረባችሁ በማለት በቀጭት ይናገራሉ…ሽንፈቱ ይገባችሁ ነበር…?
ሱራፌል፡- …በፍፁም አይገባንም…እኛንም የሚገልፅ አይደለም…ግን እግር ኳስ አንዳንዴ እንዲህ ነው…ማሸነፍ ሲገባህ ትሸነፋለህ…ትሸነፋለህ ሲባል ታሸንፋለህ…እግር ኳስ እንዳይተነበይ የሚያደርገውም ይሄ ነው…ኒጀር ላይ የነበረው እንቅስቃሴያችንና የማሸነፍ መንፈሳችን ከፍተኛ ነበር…በጣምም ተጭኗቸው ነበር የተጫወትነው… ያገኘናቸውን እድሎችም አምክነናል…ወደ አዲስ አበባ የተመለስነው በከፍተኛ የቁጭት ስሜት ውስጥ ሆነን ነው… በብዙ ጎል ሁሉ ማሸነፍ አለብን ብለን ነበር የመጣነው…እንዳሰብነውም ተሳክቶልን 3ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፈናቸው ተበቅለናቸዋል…
ሀትሪክ፡- …አዲስ አበባ ላይ 3ለ0 ብታሸንፉም…ድሉ ሊካበድ አይገባም…ያሸነፉት ደካማዎቹና ከዚህ በላይም በሆነ ውጤት መሸነፍ የሚገባውን ኒጀርን ነው…ብዙዎች ውጤቱን አጣጥለውታል…በዚህ ደረጃ ድሉን ማሳነሳቸው ቅር ያሰኝሃል…?
ሱራፌል፡- …እስቲ መጀመሪያ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ…ደካማ ማነው…?…ጠንካራውስ ማነው…?…የሚለው በደንብ የተለየ አይመስለኝም…አፍሪካ ዋንጫ ላይ ስትካፈል ቡድን እየመረጥክ አይደለም…ተደልድለህ ነው… ኒጀርን ደካማ እኛን ደግሞ የበለጥን አድርገን የምናየው ከምን አንፃር እንደሆነ አይገባኝም…ኒጀሮች ወደ ውድድሩ የገቡት እኮ ማሸነፍ መወዳደር እንችላለን ብለው ነው…ከሁለት አመት በፊት እኮ እኛ የአፍሪካ ዋንጫ ሳንገባ እነሰ ገብተው ነር.. ከዚያምማ ውጪ በፊፋ የደጃ ሰንጠረዠ ኒጀሮች እኮ እኛን ይበልጡናል…እኔ ሁሌም ግራ የሚገባኝ አንድ ነገር አለ… l
ሀትሪክ፡- …ምን ምንድነው ግራ የሚያጋባህ…?
ሱራፌል፡- …እዚህ ሀገር ምን ስትሠራ እንደምትሞገስ አይገባኝም…ምክንያቱም ስታሸንፍም ትተቻለህ… ስትሸነፍም ትተቻለህ…ኒጀሮች ሲያሸንፉን ተተቸተናል…በሰፊ ውጤት ስናሸንፋቸውም በተመሳሳይ ተተችተናል… ውጤቱም ተጣጥሏል…ታዲያ ምን ማድረግ ነው የሚፈልገው…?…እንደውም በዚህ አጋጣሚ…እንደዚህ አይነቱ ነገር ቢስተካከል ማለት እፈልጋለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡- …ኒጀርን በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ፉክክር ተመልሳችኋል…ከዚህ አንፃር ከወዲሁ የካሜሩኑን የአፍሪካ ዋንጫ አሻግረህ መመልከት ጀምረሃል…?
ሱራፌል፡- …እያለፉን እየሠራን ያለነው…ይሄንን የአፍሪካ ዋንጫ ህልማችንን ለማሳካት ነው…የሰውነት ልጆች የሠሩትን ታሪክ በእኛ ጊዜ በመድገም ወደ ካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ነው አለማችን…ነገሮች ጠባብ ወይም ከባድ ቢመስሉም ይሄንን ህልማችንን ለማሳካት እንጥራለን…ጠንክረን ሰርተን ካሜሩን ላይ መገኘት ነው ህልማችን…
ሀትሪክ፡- …የውደድር አመቱ ሲጠናቀቅ…ፋሲል ከነማንና ሱራፌል ዳኛቸውን የት ነው የምናገኛቸው…የሚለው የመጨረሻ ጥያቄዬ ቢሆንስ…?
ሱራፌል፡- …(በጣም እያሳቀ)…ፋሲል ከነማን የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን…ሱራፌል ዳኛቸው ደግሞ የኮከብነት ክብርን ደርበው ነው የምታገኛቸው…(ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …እርግጠኛ ነህ…?
ሱራፌል፡-…አትጠራጠር…!…(በጣም ሳቅ)…አባባሉም…Dream Big…(ትልቅ አልም)…አይደለም የሚለው…?…እኔም በትልቁ ነው የማልመው…(በጣም ሳቅ)…በጣም አመሰግናለሁ ቻው…፡፡
አስተያየት ይስጡ