የሊግ ካምፓኒው 2000 ደጋፊ እንዲገባ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሆነ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በሊጉ መርሃ ግብር ወደ 2000 የሚጠጉ ተመልካቾች እንዲገቡ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ተነገረ፡፡

ሀትሪክ ከታማኝ ምንጯ ባገኘችው መረጃ የጤና ሚኒስቴር የሊግ ካምፓኒውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ማስጠንቀቂያ መስጠቱም ተሰምቷል፡፡ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተይይዞ ቫይረሱን የመከላከል የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን ሊግ ካምፓኒው እንዲያከብርና እንዲያስከብር ትዕዛዝ መስጠቱ ታውቋል፡፡

በተለይ በ1ኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ባህርዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር በነበራቸው ጨዋታ የገባው የደጋፊው ቁጥር ከፕሮቶኮሉ ተቃራኒ በመሆኑ እንደማይቀበለውና ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይደግም ማሳሰቢያ መስጠቱ ታውቋል፡፡

ውድድሩ አሁን ባለው ሂደት የሚቀጥል ከሆነም ርምጃ እወስዳለሁ ማለቱም ተሰምቷል፤ ሊግ ካምፓኒው ሁሉም ቡድን ጨዋታ ሲኖረው አስር አስር ደጋፊዎች እንዲያስገባ ፍቃድ ቢሰጥም በጨዋታ ላይ የሚታየው አንዳንዱ 4 ሌላው 40 ያስገባ እስኪመስል ድረስ የታየው የደጋፊ ቁጥር አለመመጣጠን ሊግ ካምፓኒውን አስተችቷል፤ ያም ሆኖ አንዳንድ ክለቦች ቅሬታ ገብቷቸው ጥያቄ ማንሳት መጀመራቸው ለሀትሪክ የደረሳት መረጃ ያስረዳል፡፡

በተቃራኒ ደግሞ 30 ሺ ህዝብ የሚይዝ ስተዲየም ውስጥ እስከ 2ሺ ደጋፊ ቢገባ ምን ችግር አለው? ጤና ሚኒስቴር እግር ኳሱ ላይ ከሌላው በተለየ ጠንከር ማለቱ ለምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስቷል፤ የተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች እና የትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ላይ ያለውን መዘናጋት ተመልክቶ የማስተካከያ ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ስታዲየሙ ላይ ያውም የታፈነ ነገር በሌለበት ጫናውን ሊቀንስና ውሳኔውን እንደገና ሊመረምር ይገባል ሲሉ የጤና ሚኒስቴርን ጠይቀዋል፡፡

በወጣው መረጃ ዙሪያ የፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ክፍሌ ሰይፈ በበኩላቸው ለሀትሪክ በሰጡት ምላሽ “የ1ኛ ሣምንት 6 ጨዋታዎችን ገምግመናል መስተካከል ያለበት ጉዳይ እንዳለበትም ተማምነናል የሚገቡ ደጋፊዎች ቁጥር 10 ይሁን ተብሎ ከዚያ በላይ እየቡ ያሉ ደጋፊዎች በመኖራቸው የፀጥታ ኃይሉ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ መግባባት ላይ ደርሰናል” ሲሉ የክለቦች የደጋፊ ቁጥር መለያየት የፈጠረው ቅሬታ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡ አቶ ክፍሌ ”ጤና ሚኒስትር በላከው ደብዳቤ በ1ኛ ሳምንት የታየው ሁኔታ ቅር እንዳሰኘው ገልጾልናል፡፡

ማክስ የማያደርጉ ደጋፊዎች ነበሩ፤ ከበሮ ይዘው ተጠጋጋተው ሲጨፍሩ ታይቷል፤ ይሄ ደግሞ የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን የጣሰ በመሆኑ መስተካከል እንዳለበት የወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ ሁሉ ጠቅሰው ማሳሰቢያ ሰጥተውናል” በማለት ያለውን እውነታ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport