ዲኤስ ቲቪ ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር መከረ

ሊግ ካምፓኒው የዲኤስ ቲቪ ምላሽን እየጠበቀ ነው
የኢትዮጵያ ፕሪማየር ሊግን ለቀጣዮቹ 5 አመታት ስፖንሰር ያደረገው ትልቁ የሚዲያ ተቋም ዲ.ኤስ.ቲቪ 16ቱም የሊጉ ክለቦች የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሊቀጥሩ እንደሚገባ አሳሰበ፡፡

የዲ.ኤስ.ቲቪ ባለሙያዎች ከሊግ ካምፓኒና ከክለቦች አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት የተሟላ መረጃ ለመገናኛ ብዙኃን የሚገልፅ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያና የተጠናከረ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሊኖራቸው እንደሚገባ ለክለቦቹ ተነግሯቸዋል፡፡ ተቋሙ ይፋ ባደረገው መመሪያ የሊጉን ማንኛውንም ጨዋታ የትኛውም የመገናኛ ብዙኃን የመቅረፅ መብት እንደሌለው ለክለቦቹ የገለፀ ሲሆን የሊግ ካምፓኒው ይህንን ኃላፊነት የሚሰራና የሚከታል ባለሙያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለመቀጠር እየተዘጋጀ መሆኑን መግለፁ ይታወቃል፡፡

በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከሀትሪክ ጥያቄ የቀረበላቸው የሊግ ካምፓኒው ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ እንደገለፁት “ከዲ.ኤስ.ቲቪ ጋር በተያያዘ በረቂቅ ሰነዱ ላይ ምላሽ ሰጥተን ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳል፡፡ የነርሱን ምላሽ እየጠበቅን ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከስታዲየም ፓውዛ ጋር ተያይዞ የሚናፈሰው ወሬ መስተካከል እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ክፍሌ የኛ የውድድር መርሃ ግብር በቀን የሚካሄድ በመሆኑ የስታዲየሙን ፓውዛ የግድ አያስፈልግም ግን መሰራት ካለበት ጉዳዮን በኃላፊነት የያዘው አካል የሚያየው ይሆናል የአዲስ አበባ ስታዲየምን ለሚጠቀሙት ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የቤት ስራው ተሰጥቷቸው የሚመለከተውን አካል እያነጋገሩ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በ3ቱ የትግራይ ክልል ክለቦች መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራትና ስዑል ሽረን በተመለከተ ዋና ስራ አስከያጁ እንደገለፁት “ከ3ቱ ክለቦች አመራሮች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለንም መገናኘትም አልቻልንም በቀጣይ ካለው ችግር አንፃር ምን መደረግ አለበት የሚለው የሼር ካምፓኒው ቦርድ ውሣኔ የሚሰጥበት ይሆናል” በማለት ለሀትሪክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport