በውዝግብ የተቋረጠው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ነገ ይካሄዳል


በ2012 ሊካሄድ የነበረውና በተገቢነትና ሌሎች ጥያቄዎች በቀረበው ቅሬታ ሳይካሄድ የቀረውና አዲስ አስመራጭ ኮሚቴ መርጦ የተበተነው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ነገ ጠዋት በጁፒተር ሆቴል ይካሄዳል፡፡


ባለፉት አመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ኢንጂነር ኃ/ኢየሱስ ፍሰሃ እንዲሁም በውድድርና ስነ-ሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢነት የሠሩት ኢንስፔክተር የኔነህ በቀለ ለፕሬዚዳንትነት በሚወዳደሩበት በዚህ ምርጫ 18 ዕጩዎች ለ9 የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቦታ ይወዳደራሉ፡፡

📸 official AAFF


በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ሊፈታ የተዋቀረው 5 አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚቴ ለስራ አስፈፃሚና ለፕሬዚዳንትነት ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ውክልና የተሰጣቸውን ኢንስፔክተር የኔነህ በቀለን መቀበሉ ለሌላ ውዝግብ በር እንዳይከፍት ስጋት ፈጥሯል ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማህበራት ማደራጃና ማልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ገ/ህይወት ግን “ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደረ ሰው ከተሸነፈ ለስራ አስፈፃሚነት መወዳደር ይችላል የሚል ደንብ ወደ 21 የሚጠጉ ፌዴሬሽኖች መተዳደሪያቸው ላይ አስገብተዋል ነገር ግን በሁለት ቦታ መወከል አይቻልም ህጉ ይከለክላል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የአጣሪ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ዮሐንስ ስለሺ በበኩላቸው “ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመጣው መመዘኛ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማህተም ተመቶበት ተሰጥቶናል ስንመለከተው የሚከለክልም ሆነ የሚፈቅድ ደንብ አላገኘንም በሁለት ቦታ መወከል ይቻላል ወይም አይቻልም የሚልም ሕግ አላየንም ለምን ታዲያ በፖዘቲቭ አይተነው አንፈቅድም ብለን ልንወስን ችለናል” ሲሉ የኮሚቴው ውሣኔ አሳውቀዋል፡፡


በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ የአመቱ ሪፖርትና የ2013 እቅድ የሚቀርብ ሲሆን የኦዲት ሪፖርቱም ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚሁ ምርጫ ላይ ፌዴሬሽኑን ላለፉት አመታት ሲመሩ የነበሩት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ በለጠ ዘውዴ፣ ወ/ሮ ሰርካለም ከበደና የህዝብ ግንኙነቱን ሲመሩ የነበሩት አቶ ዮናስ ሀጎስ እንደማይወዳደሩ ለሀትሪክ የደረሰው መረጃ ያስረዳል፡፡

 

 

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport