ነገ በስድስተኛ ሳምንቱ የሚመለሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የሚመሩ ዳኞች የጥቅማጥቅም ጥያቄያችን መልስ ሊያገኝ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።
የ2018 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለአምስት ሳምንታት ሲደረግ ቆይቶ በኢትዮጵያ ዋንጫ እና ክለቦች የከተማ ለውጥን ስለሚያደርጉ ለአስር ቀናት ያህል ከነበረው ዕረፍት መልስ ነገ በአዲስ አበባ እና በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየሞች ላይ በተመሳሳይ በሚደረጉ የስድስተኛ ሳምንት አንድ አንድ መርሀግብሮች በድጋሚ ይመለሳል። ፕሪምየር ሊጉን የሚመሩ ዳኞች ነገ በሚመለሰው ውድድር ላይ ግን ጥያቄያችን ሊመለስ ይገባል ይህ መሆን ካልቻለ ደግሞ ውድድር ለመምራት እንቸገራለን በማለት ቅሬታቸውን ለሀትሪክ ስፖርት ያደረሱ ዳኞች አሳውቀዋል።
በቅሬታቸው መሠረት “የቀን የውሎ አበላችን 2 ሺህ ብር ነው የሙያ አበላችን ደግሞ 3 ሺህ ብር ነው ከአራት አመት በፊት ማሻሻያ እንዲደረግልን በተደጋጋሚ ጥያቄን ብናነሳም መልስ ማግኘት አልቻልንም በዚህም አመት ጥያቄውን አንስተን እየሰራቹ ጠይቁ ተብለን ነበር ነገር ግን እስከ አሁን በተደጋጋሚ ለምናነሳው ጥያቄ መልስ አላገኘንበትም ሲሉ ተናግረዋል። ድረገፃችን ዳኞች ስታንዳርድ ያለውን ሆቴል ያዙ እንደሚባሉ ሊጉ በየአመቱ ከፍተኛ ገንዘብን ለክለቦች እያከፋፈለ የነሱ መብት ሰሚ ማጣቱ እንዳሳዘናቸው አብዛኞቹ ዳኞችም ቤተሰብን ጭምር በዚህ ስራ እንደሚያስተዳድሩ ጭምር መገንዘብ ችለናል።
ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ የዳኞቹን ጥያቄ ለመመለስ ሀገር ውስጥ እንደማይገኙ የሰማን ሲሆን የፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሸዋንግዛው ተባበልን በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን በስልክ ብንጠይቅም “በስልክ ምንም አይነት መረጃ አንሰጠም” ሲሉ ቁንስል ሀሳባቸውን ሰጥተውናል።
- ማሰታውቂያ -
ይህንንም ተከትሎ ዳኞች ነገ በሚጀምረው የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን ላይ እንመለከታቸው ይሆን ወይስ ሌላ መፍትሄ ይገኝለት ይሆን ? አዳዲስ መረጃዎች ካሉም በቀጣይ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።


