የፌዴሬሽኑና የቴክኒክ ኮሚቴው አለመግባባት ተጠናክሮ ቀጥሏል በኢንስ. ሰውነት ቢሻው የሚመራው ኮሚቴ ባለ 16 ነጥብ ደብዳቤ አስገብቷል

የፌዴሬሽኑና የቴክኒክ ኮሚቴው አለመግባባት ተጠናክሮ ቀጥሏል

በኢንስ. ሰውነት ቢሻው የሚመራው ኮሚቴ ባለ 16 ነጥብ ደብዳቤ አስገብቷል


የብሔራዊ የቴክኒክ ልማት ኮሚቴና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግንኙነት ከመሻሻል ይልቅ ወደ ለየለት ውዝግብና አለመግባባት እያመራ ነው፡፡
በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት የሚመራው የቴክኒክ የልማት ኮሚቴ የብ/ቡድን ዋና አሰልጣኝ ቅጥርን አስመልክቶ ያቀረበውን ባለ 9 ነጥብ ምክረ ሃሣብ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ “ከቴክኒክ ይልቅ አስተዳደራዊ ነገር ይበዛዋል” በሚል ውድቅ ካደረጉ በኋላ ውስጥ ለውስጥ ሲብሰለሰል የነበረው ልዩነት ወደለየለትና ወደ ሰፋ አለመግባባት እንዲያመራ አድርጎታል፡፡

በቴክኒክ ልማት ኮሚቴው የቀረበው ባለ 9 ነጥብ ምክረ ሃሣብ ሙያተኛ ባልሆነ ሰው ውድቅ ተደርጓል በሚል የከረረ ተቃውሞ ውስጥ የገቡት የኮሚቴው አባላት በዚህ ድርጊት የደረሰባቸው ቁጭት ሳያባራ የፌደሬሽኑ አመራሮች “ቴክኒክ ኮሚቴው ምንም የሠራው ስራ የለም” በሚል በሚዲያ አስተያየት መስጠታቸው ቁጣቸው ዳግም እንዲቀሰቀስ፣ ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ እስከማስገባትና አቋማቸውን እስከማሳወቅ እንዳደረሳቸው ሀትሪክ በተለይ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ባለ 9 ነጥቡ ምክረ ሃሣብ ውድቅ ከመደረጉ ባልተናነሰ “የቴክኒክ ኮሚቴው ወደ ኃላፊነት ከመጣ ጀምሮ የሰራው ሥራ የለም” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱ ለከፋ ቁጣ የዳረጋቸው የቴክኒክ ኮሚቴው አባላት ባለፈው ሰኞ በጉዳዩ ዙሪያ ከመከሩ በኋላ ማክሰኞ ባለ 16 ነጥብ የያዘ የቅሬታና የተቋውሞ ደብዳቤ በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ስም ተፈርሞ ለፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት አስገብተዋል፡፡
በቀን 17/02/2013 በቁጥር 004/03/2013 በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ስምና ፊርማ ተፈርሞ ለፌዴሬሽኑ ከገባው ደብደቤ መረዳት እንደተቻለው በተለይ ቴክኒክ ኮሚቴው “ምንም አልሠራም” በሚል የተደረሰው ድምዳሜ ልብን የሚነካና የቋሚ ኮሚቴውን የስራ ሞራልና ተነሳሽነት የሚያጠፋ ድካምና ልፋታችንን ከንቱ ያስቀረ ድርጊት ነው” በማለት በፃፉት ደብደቤ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ተፈርሞ ከገባው ደብደቤ ለመረዳት እንደተቻለው “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሽንና በሥሩ በሚገኘው የብሔራዊ የቴክኒክ ልማት ኮሚቴ መካከል በተፈጠረው መጠነኛ የሥራ አለመግባባት ጭራሹንም ቴክኒክና ልማት ኮሚቴው ከተቋቋመ ጀምሮ ምንም የሠራው ሥራ የለም” በማለት በሚዲያ ሳይቀር የፌዴሬሽኑ አመራርና የጽ/ቤት ኃላፊው ሳይቀር እስከዛሬ ድረስ የለፋንበትን ስራ ከንቱ ለማስቀረት ሲሞክር ታይቷል፤ ሁኔታውም በጣም ልብ የሚነካ፣ የግለሰቦችን የኋላ ታሪክና የሠሩትን ታላላቅ ተግባራት ለማጥፋት ታስቦ ይሆን ወይም ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ስም ማጥፋቱ በተደጋጋሚ በሚዲያ ሲነገር ተደምጧል” በማለት ድርጊቱ እንዳሳዘነው የሚተነትነው ደብደቤው “ይህ ድርጊት በእጅጉ የቋሚ ኮሚቲያችንን የስራ ሞራልና ተነሳሽነት የሚጎዳም ነው” ብለዋል በደብዳቤ፡፡
የብሔራዊ የቴክኒክ ልማት ኮሚቴው ከፌዴሬሽኑ በተሰጠው የስራ ዝርዝር መሠረት ለመስራት ብንሞክርም የፌዴሬሽኑ አመራር ሊያሠራን አልቻለም፤ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ተጠሪነት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ እጅ ወጥቶ ወደ ኮሚቴው ከመጣበት ከሌሴቶው ጨዋታ አንስቶ በሴቶችም በወንዶችም አስፈላጊው ሥራ ሠርተናል፤ በርካታ ሥራዎችን ለመስራት ለፌዳሬሽኑ ያቀረብናቸው እቅዶችም ምላሸ ባለማግኘታቸው በምንፈልገው ልክ እንዳንሠራ አድርጎን አልሰራችሁም፤ የሚለን ፌዴሬሽን ራሱ እንቅፋት ሆኖብን ቆይቷል” በማለት አምርረውም ይወቅሳሉ፡፡
በዚህ በኩል በተለይ ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አስገብተን ምላሽ ያላገኘንባቸው በሚል የቴክኒክ ኮሚቴው 16 ነጥቦችን በቅሬታ መልክ በደብዳቤው ውስጥ አካቶ አቅርቧል፡፡

በብሔራዊ የቴክኒክ ልማት ኮሚቴ ውስጥ ከፋብሪካ ቡድን ጀምሮ እስከ ብ/ቡድን በማሰልጠን ውጤታማ መሆን የቻልን በትምህርትና በእውቀት የታጠቅን እስከማስትሬት ድግሪ ድረስ የደረሰን የምሁራንና የሙያተኞች ስብስብ ሆነን የሠራነው ሥራ አልሠሩም ብሎ ማጣጣልና በዚህ መልኩ መፈረጁ አግባብ አይደለም፤ እኛ እንስራ ብለን አላሠራ ብሎ ደብዳቤዎቻችንን አንቆ የያዘው ተገቢውን እቅድና ስትራቴጂ በመንደፍ ወደ ሥራ ብንገባም ፌዴሬሽኑ ሥራችንን በአግባቡ እንድንሠራ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ባይችልም በሙያችን ግን ያቀድነውን ያህል በአግባቡ ለመፈፀም የበኩላችንን ጥረት ስናደርግ ቆይተናል ብለዋል፡፡

የቴክኒክ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በፅሁፍ የተሰጠንን በተግባር እንድንወጣና አገራችን እንደናግዝ ጥያቄ ያቀረብንባቸውን ደብዳቤዎች ለአብነት ያህል 2 ገፅ ከዚህ ደብደቤ ጋር አባሪ አድርገን አቅርበናል” የሚለው በኢንስትራከትር ሰውነት ቢሻው የሚመራው የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው በፃፈው ደብዳቤ “ፌዴሬሽኑ በቴክኒክ ኮሚቴው ላይ ያለውን አመለካከት እንዲያስተካክል” በሚል ከገለፁ በኋላ “በሀሰት ለተነገሩብን ስም ማጥፋቶች ትክክለኛ ምላሽ የምንሰጥ መሆኑን እንገልፃለን” ይላል የቴክኒክ ኮሚቴው በፃፈው ደብዳቤ ማሳረጊያ፡፡

የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው አባሪ አድርጎ ያያዘው ደብዳቤ ላይ ከሠፈረው ፅሁፉ ለመረዳት እንደተቻለው “የቴክኒክ ልማት ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በፅሁፉ የሰጠንን ኃላፊነት በተግባር እንድንወጣና ሀገራችንን እንድናግዝ ያቀረብናቸውን ደብዳቤዎች የሚመለከተው ሁሉ እንዲያውቀው በዝርዝር እናቀርባለን” በማለት ባለ16 ነጥብ ቅሬታን አቀርበዋል፡፡
የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው ለፌዴሬሽኑ የቅሬታ ደብዳቤ ካስገባ ቀናቶች ቢቆጠሩም እስከ አሁን ከፌዴሬሽኑ የተሰጠ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምላሽ ባይኖርም የቴክኒክ ኮሚቴው አባላት ከፌዴሬሽኑ ምላሽ የማያገኙ ከሆኑ መገናኛ ብዙኃንና በመጥራት ጉዳዩን ይፋ በማድረግ ህዝብና መንግሥት እንዲያውቀው የማድረግ እቅድ የያዙ ሲሆን ከዚህ ከፍ ሲልም እስከ ካፍና ፊፋ ድረስ በመሄድ ለሙያተኞች ክብር የሚታገሉ መሆናቸውን ስማችን አይጠቀስ ያሉ የቴክኒክ ኮሚቴው አባላት በተለይ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡

ከዚሁ ከፌዴሬሽኑና የብሔራዊ የቴክኒክ ልማት ኮሚቴው ውዝግብ ሣንወጣ የቴክኒክ ኮሚቴው ሙሉ በሙሉ አፍርሶ በሌሎች የመተካት ሃሣብ ቢኖርም ይሄ ሃሣብ በሥራ አስፈፃሚው መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር እንዳደረገ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፤ በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት የሚመራው የቴክኒክ ኮሚቴው ተበትኖ ተደራጅቶ ስልጣን ተከፋፍሎ የተቀመጠን አንድ ቡድን የመተካት ሥራ መሠራቱ የተሰማ ሲሆን ይሄን ማድረግ ወደ ሌላ የአልተፈለገ ችግር ሊያስገባ አንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ ስሜ ለጊዜው ይቆይ ያሉ አንድ የቴክኒክ ኮሚቴው አባል “ሁሉን ነገር ሰምተነዋል፤ እነማንን ማምጣት እንደተፈለገ ማን ምን እየሠራ እንደሆነም እናውቃለን፤ ፌዴሬሽኑ እኛን ሲፈልግ የሚያፈርሰን ሲፈልገን የሚገነባን አይደለንም፤ ሀሉም ነገር የሚፈርሰውና የሚገነባው ሕግን ተከትሎ ነው፤ የእኛን ኮሚቴ ለማፍረስ ድፍረቱ የመጣው ከምን መነሻ ነው? ይሄን ማድረግ አይደለም ማሰብ በራሱ ከባድ ነው” በማለት የሚወራውንና የተጠነሰሰውን ማሳካት እንደማይቻል እርጠኝነት በተሞላበት ስሜት ተናግረዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን በቴክኒክ ኮሚቴው መበተን ዙሪያ ባለፈው ሳምንት በስልክ አነጋግረናቸው “ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴውን የመበተን ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን የማንሣት ሃሣብም እንቅስቃሴም አለመኖሩን መናገራቸው የሚታወስ ነው

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.