ሊግ ካምፓኒውና ዲ.ኤስ.ቲቪ በሊጉ ጅማሮ ዙሪያ እየመከሩ ነው

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የቀጣዮቹ 5 አመታት ስፖንሰር መሆኑ የታወቀው የዲ.ኤስ ቲቪ የብሮድካስቲንግ ቡድን አዲስ አበባ መግባቱ ታውቋል፡፡ ቡድኑ ከሊግ ካምፓኒው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ትላንት ከቀትር በኋላ 4 ሰዓታት የፈጀ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን በሊጉ ጅማሮ በስታዲየሞች መረጣና በዕጣ አወጣጥ ስነ-ሥርዓት ዙሪያ ከዲ ኤሲ ቲቪ ተወካዮች ጋር መምከራቸው ተሰምቷል፡፡

የዲ.ኤስ.ቲቪ የማሸነፊያ ገንዘብ መጠን 68 ሚሊዮን ዶላር ነው? ወይስ 22.5 ሚሊዮን ዶላር የሚለው የሁለት ወገኖች ክርክር እስካሁን ትክክለኛ ምላሽ ያላገኘ ሲሆን የአራት ቀኑ የዲ.ኤስ ቲቪ የብሮድካስቲንግ ቡድንና የሊግ ካምፓኒ አመራሮች ስብሰባ ላይ ስምምነቱ ይፋ የሚደረግበት ቀን እንደሚወስን ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል ታህሳስ 3/2013 የሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያዎቹ 5 ሳምንታት 40 ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ መወሰኑን የሊግ ካምፓኒው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፉ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡ ስራ አስኪያጁ ለውድድር ስፍራው 7 ከተሞችና ስታየሞች የተያዙ ሲሆን ከሰባቱ አንዱ እንደሚቀነስ እስካሁን ግን ተቀናሹ ስታዲየም አለመታወቁን ገልፀዋል፡፡

ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ ግን የአዲስ አበባ ስታዲየም፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም፣ የመቐለ ስታዲየም፣ የባህርዳር ስታዲየም፣ የድሬደዋ ስታዲየምና የሀዋሳ ስታዲየም ሳይመረጡ እንዳልቀረና የአዳማ ስታዲየም ግን ከኮቪድ 19 የመከላከያ ፕሮቶኮል አንፃር ሳይሰረዝ እንዳልቀረ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ ሊግ ካምፓኒው ከዲ.ኤስ.ቲቪ የስርጭት ባለሙያዎች ጋር እስከ ሰኞ ድረስ ከተወያዩ በኋላ ያሉት ሁኔታዎች ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚሁ የሊግ ካምፓኒው ዜና ሳንወጣ ለታህሳስ 3/2013 የሊጉ ጅማሮ የዕጣ ማውጣት ስነ-ሥርዓት በይፋ በቴሌቪዥን ለማስተላለፍ እቅድ ተይዟል፡፡ አለም አቀፍ ይዘት ባለው መልኩ የዕጣ ማውጣት ስነ-ሥርዓቱን ከተለመደው ውጪ በማድረግ ለማዘመን መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡ 16ቱ የሊጉ ክለቦች ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኙበት በመሆኑ የ2013 መርሃ ግብር ከፍተኛ ጉጉት የጫረ ሆኗል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport