የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ላይ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ የፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ደካማና የዘገየ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

የፍትህ አካላት የሚባሉት የዲሲፕሊን ኮሚቴና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ውሣኔዎቻቸው የዘገየና ተአማኒነት ያጣ መሆኑ በርካታ ተጨዋቾችና ክለቦችን አስቆጥቷል፡፡
የኮሚቴው አባላት አማተርና በሳምንት አንዴ የሚሰበሰቡ ሲሆን ምንም አይነት ወጪ የመተካት ወይም ክፍያ የሌላቸው መሆኑ በታማኝነት ጉዳዮችን እንዳያዩ እንዳደረጋቸው ይነገራል፡፡ በዚህ ምክንያት በርካታ ውሣኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች እንዲበረከቱ፣ ፍትህ የሚጠይቁ ክለቦችና ተጨዋቾች በተለይ በፌዴሬሽን ላይ ያላቸው ተአማኒነት እየዘቀዘ ለመምጣቱ በኮሚቴዎቹ የስራ ሂደት ላይ ጣታቸውን የሚቀስሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ዋንኛ የፍትህ ባለድርሻ እንደመሆኑ እንደሌሎቹ ኮሚቴዎች ፈጣንና ተአማኒነት ያለው ውሣኔ ከተከታታይ ርምጃዎችን የማስፈፀም አቅም ጋር ሊጠናከር ሲገባ አባላቱ ጉዳይ ገጠመኝ አልቻልኩም በሚል የተለያዩ ሰበቦች እየቀሩ መሆናቸው የፍትህ ፈላጊዎችን ቁጣ ቀስቅሷል፡፡

የፍትህ አካላቱ ነፃና ገለልተኛ የመሆናቸው ነገር የተረጋገጠ ሲሆን ተጠሪነታቸው ለጠቅላላ ጉባኤ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አባላቱ በበጎ ፈቃድ የሚሰሩ መሆናቸውና ምንም የአበል ክፍያ የማያገኙ መሆኑ በሙሉ ልባቸውና በተጠያቂነት አንዳይሰሩ አድርጓቸዋል ተብሎ ይታማል፤ የመኪና ነዳጅ ክፍያን ያለመቻል፣ ወይም ሌላ ጥቅማ ጥቅም አለመኖሩ ደግሞ በፍትህ አሰጣጡ ላይ ሌላ አይነት የሙስና በርም እንዳይከፍት ተሰግቷል፡፡ የሚከፈል ክፍያ ከሌለ በውሣኔው ተጠቃሚ የሚሆን አካል ጋር ላለመሞዳሞዳቸው ምንም አይነት ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻልም የሚሉ ወገኖች የሁለቱ ኮሚቴ አባላት ዋነኛ የፍትህ ስርዓቱ ማስተማመኛ እንደመሆናቸው ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥቅማቸው ሊከበር ይገባል ይላሉ፡፡

የተለያዩ የፌዴሬሽኑ ኮሚቴዎች በአንድም በሌላም አበልና ጥቅማ ጥቅሞች የሚያገኙ መሆኑ ደግሞ የፍትህ አካላቱን ቅሬታ ውስጥ የከተተ ሆኗል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ በኮሚቴው ዋና ፀሐፊ ተዘጋጅቶ የሚጠብቋቸው የክስ ሰነዶች መበራከት፣ የተጨዋቾች የይገባኛል ልዩነት ከዝውውር መስኮቱ የጊዜ ገደብ ጋር የሚታይ ቢሆንም የፍትህ አካላቱ መቅረትና መዘግየት ተጨዋቾችና ክለቦች ላይ ጉዳት ማስከተሉ ጥያቄ የሚያስገሳ ክፍተት መሆኑን የፌዴሬሽኑ የውስጥ አዋቂ ለሀትሪክ ገልጿል፡፡ በዚህ የኮሚቴዎቹ ክፍተት ዙሪያ ሰሞኑን ከተካሄደ ምክክር በኋላ ሂደቱን ገምግሞ የማስተካከያ አቅጣጫ እንዲዘጋጅ በያዝነው ወር አጋማሽ በኃላ ላይ ለሚካሄደው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲቀርብ መወሰኑ ቢነገርም ዋና ፀሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ግን አስተባብለዋል፡፡ ዋና ፀሐፊው እንደገለፁት “ጠቅላላ ጉባኤው ላይ የሚላከው አጀንዳ ተልኮ አልቋል፤ አዲስ አጀንዳ ሊኖር አይችልም ነገር ግን ከፍትህ አካላት አንፃር እየቀረቡ ያሉ ችግሮች በመኖራቸው መፍትሔ ሊሰጣቸው የግድ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ለኮሚቴውም እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ለማስተካከል እንጥራለን የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈጠር አንሻም ከፍትህ አካላት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ክፍተቶች የግድ የሚዘጉ መሆን ስላለባቸው በዚህ ላይ ጠንክረን እንሰራለን” በማለት ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን በአፅንኦት መያዙን በተለይ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport