ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ባደረገው የአካል ብቃት ምዘና 6 ዋና ዳኞች መውደቃቸው ተሰማ።
ከ24 ዋና ዳኞች ሠሃል 18ቱ የአካል ብቃት ፈተናውን ያለፉ ሲሆን ኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩን ጨምሮ አምስቱ ፌዴራሎች ተፈሪ አለባቸው ፣ ተሳልኝ ለማ፣ ሄኖክ አክሊሉ ፣ አዳነ ወርቁና ሀብታሙ መንግስቴ ማሟላት ያለባቸውን 18.2 የሚለውን ሚኒማ ባለማሟላታቸው ከሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዳኝነት ምደባ ውጪ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያስረዳል።
ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሙሉ መረጃውን በቅርብ ኚዜ ውሰጥ እንደሚያወጣና ለፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ውድድር ኮሚቴ ዝርዝሩን እንደሚልክ ይጠበቃል።
ፕሪሚየር ሊጉ በአዳማና ሀዋሳ በሚቀጥለው ሁለተኛ ዙር ውድድር ለዋንጫ እና ላለመውረድ የሚደረግ በመሆኑ ከዳኝነት ጥራት ጋር ተያይዞ ጠንካራ አቋም በመያዝ ውድድሩ ያማረ እንዲሆን ከፌዴሬሽኑ ጋር በጥምረት በመሰራት የበኩሉን ጥረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።


