*…ካፍ የሚያውቃቸው አምስቱ
ኢንስትራክተሮች ቦታ አጥተዋል….
*… የአምስቱም ኢንስትራክተሮች ዝምታም ጥያቄ አስነስቷል…
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ በተሰጠው የኢንስትራክተሮች ኮታ ተገቢውን ባለሙያ መጠቀም አለመፈለጉ አነጋጋሪ ሆኗል።
- ማሰታውቂያ -
ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ ካፍና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዕውቅና የሰጧቸው የአካል ብቃት ኢንስትራክተሮች አምስት ሲሆኑ እነሱም ሃይለመላክ ተሰማ፣ ቸርነት አሰፋ ፣ ሳራ ሰኢድ፣ ፍቃዱ ጥላሁንና ኤፍሬም መንግስቱ መሆናቸው ታውቋል።
በየውድድሩ ስፍራ ዳኞችን ስልጠና የሚሰጥ የሚያበቃ የአካል ብቃትና የተግባር አሰልጣኞችን መመደብ እንዳለበት በኮሚሽነር ሸረፋ ደሌቾ የሚመራው የቀድሞ የዳኞች ኮሚቴ ከፕሪሚየር ሊጉ ጋር በመነጋገር በየውድድሩ አንድ ዳኛ የሚመድብ ሌላኛው ስልጠና የሚሰጥ የፊዚካል ፊትነስ ኢንስትራክተር እንዲመደብ ቢስማማም አሁን እየሰራ ያለው ኮሚቴ አየተጠቀመበት አለመሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል።
አምስቱ የአካል ብቃት አሰልጣኞች ካፍ የሚያውቃቸው ሲሆን አሁን ኮሚቴውን እየመሩ ያሉ አመራሮችን ጨምሮ አብዛኛው በሚባል የኩፐርቴስት ፈተና በነዚህ ኮሚሽነሮች ስር ያለፈና የባለሙያዎቹ አሻራ ያረፈባቸው መሆኑ ሲታይ በነሱ አለመጠቀሙ ሊግ ኪባንያም ለባለሙያው የመደበው በጀት ለተገቢው ሰው እየዋለ ነው ብሎ አለመቆጣጠሩ ግርምትን ፈጥሯል።
የዳኞቹ ኮሚቴ ከሊግ ኩባንያው የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ጋር በጋራ በመሆን ዳኞችን የሚመድብ አንድ አባል በቋሚነት እየመደበ ሲሆን በፊዚካል ኢንስትራክተርነት ኮታው የኮሚቴው አባል የሆኑት ሁለቱ
አመራሮች ክንዴ ሙሴና ለማ ንጉሴ እየተፈራረቁ መመደባቸው ጥያቄ አስነስቷል። ሁለቱም ስራውን በኮሚቴው አባልነታቸው ይስሩ አንጂ ኢንስትራክተር አለመሆናቸው ሲታይ አርቢትሮቹ ውስጥ ጉርጉምታ ማስነሳቱ አልቀረም።
ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ የዘንድሮ የውድድር አመት ከተጀመረ ጀምሮ ያልተጠቀመባቸውን አምስቱ ኢንስትራክተሮች ፌዴሬሽኑም ይሁን ካፍ ዋጋ የሰጣቸው መሆኑን በማመን በባለሙያዎቹ የመጠበም ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ይታመናል።
የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤትም የኮሚቴው ውሳኔና ተግባር ዙሪያ ማጣሪያ በማድረግ የማስተካከያ የእርምት ርምጃ ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።


