አሰልጣኝ ውበቱ በሁለት አመት ውስጥ
6ሚሊዮን ብር ይከፈላቸዋል…..
“ሃላፊነቱ ላይ የቆየሁት ለክለቦች የጠየኩትን ያህል ተከፍሎኝ ሳይሆን ዛሬን ስለማይጎዳኝና ነገ በደንብ ስለማገኘው ነው”
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
የዋሊያዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ በተራዘመው የሁለት አመት ኮንትራታቸው 250 ሺህ ብር የተጣራ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ፌዴሬሽኑ በተስማሙት ውል ዙሪያ የተናገሩት ዋና ጸሃፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን “ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሶስት ጊዜ ከተሰበሰበ በኋላ የተመዘገበው ውጤት፣ የሌሎች ሀገራት የክፍያ ተሞክሮ፣ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ደመወዝና የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ጥቅም ምን መሆን ይችላል ምን ይሟላ በሚለው ጉዳይ መረጃዎች ከቀረቡ በኋላ ስምምነቱ ተፈጽሟል” ሲሉ ተናግረዋል።
- ማሰታውቂያ -
አቶ ባህሩ አክለውም “ውሉ እንዲከበር አሰልጣኙ ለ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ብሄራዊ ቡድኑን ማሳለፍና የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። ፌዴሬሽኑ ወደ ውጪ ተጉዘው የመሰልጠን ዕድል ቢያገኙ ሙሉ ወጪ ፌዴሬሽኑ የሚችል ሲሆን በሚያደርጉትም የውጪ ጉዞ በፊት ከነበረው የኢኮኖሚ ክላስ በቢዝነስ ክላስ ቲኬት ይቆረጣል”ሲሉ አቶ ባህሩ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ” ከተለያዩ ክለቦች የቀረበልኝ ፍላጎት ቢኖርም በብሄራዊ ቡድን ሀላፊነት መቆየት ለቀጣዩ የአሰልጣኝነት ህይወቴ ትልቅ ጥቅም ስለሚኖረው ለሁለት አመት ለመቀጠል ተስማምቻለሁ በተሰጠኝ ዕድል ደስተኛ ነኝ አብረውኝ ከሚሰሩ ጋር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እጥራለሁ ” ሲል ተናግረዋል።
አሰልጣኙ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት “የተቀመጠውን ግዴታ የማስፈጸም ሀላፊነት አለብኝ ነገር ይህን ካላደረክ ርምጃ ይወሰዳል የሚል የተቀመጠ ነገር ነገር የለም። ቡድኑን የማላሳልፍ ከሆነ ቁጭ ብለን እንወያይና የሚሆነውን እንወስናለን ከክፍያ ጋር ተያይዞ ብሄራዊ ቡድኑን ማሰልጠን የማይተካ ነገር አለው ነገር ግን ሃላፊነቱ ላይ የቆየሁት ለክለቦች የጠየኩትን ያህል ተከፍሎኝ ሳይሆን ዛሬን ስለማይጎዳኝና ነገን በደንብ ስለማገኘው ነው” ሲሉ
መልሰዋል።
በምክትል አሰልጣኞቹ ደስተኛ እንደሆኑ የተጠየቁት አሰልጣኙ “ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በምክትል አሰልጣኞቼ ደስተኛ ነኝ የነርሱም ጥቅም እንዲከበር ጠይቄ ተመልሶልኛል ተጨዋቾች ወደ ቡድኑ ሲመለሱ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ መፈጸም ስላለብን ነገሮች ሀሳብ ሰጥቼ ተቀብለውኛል በኔ ዕድገት ብቻ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም በሙሉ ስታፌ ግን ደስተኛ ነኝ” ሲሉ መልሰዋል።
“ከሊቢያ ብለሄራዊ ቡድን ጋር ለመጫወት በቃል ደረጃ ብንስማማም ሳይሳካ ቀርቷል ነገር ግን ከሱዳንና ጋር በመጪው አርብና ሰኞ በምናደርገው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ እንድትመለከቱን እጋብዛለሁ” ያሉት አሰልጣኝ ውበቱ ” ያለፉትን ሁለት አመታት ያለእናንተ አልተጓዝንም በቀጣዩ አመታትም ያለናንተ አይሆንምና ለብሄራዊ ቡድኑ ገንቢ ሀይል እንድትሆኑን እጠይቃለሁ አበረታቱን ክፍተት ካለ እየነገራችሁን እንደሀገር ስራው የጋራ በመሆኑ አብረን እንስራ ለእስከዛሬው ድጋፋችሁ አመሰግናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
በውሉ ዙሪያ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ጸሃፊው በበኩላቸው” ከክፍያ ጋር ተያይዞ ከከፍተኛ ተከፋዩ የሞሮኮ አሰልጣኝ አንስቶ ትንሽ ክፍያ እስከሚከፈላቸው አሰልጣኞች ድረስ ገምግመናል የነ ሚቾን ደመወዝንም አይተናል የፕሪሚየር ሊጋችን ክፍያንም አይተናል ከዚያ በኋላ ነው የተስማማንበትን ስምምነት ያጸደቅነው ክፍያውን ከሌሎች ሀገራት አንጻር ካየነው አነስተኛ ነው እንደ ሀገራችን ካየን ግን ትልቅ ደመወዝ ነው በዚህም ደስተኛ ነን ” ሲሉ መልሰዋል። አቶ ባህሩ ” ብራንድን ከመጠበቅ አንጻር የተሻለ ለመሆን እየሰራን ነው እንደ ምሳሌ የጋና የስነምግብ ባለሙያ የኛን ሀገር የስነምግብ ባለሙያ ምክር ስትጠይቅ ማየቴ ገርሞኛል ይሄም ለካ ጥሩ ደረጃ ላይ ነን ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል” ሲሉ ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ በውሉ መሠረት ከደመወዝ ክፍያው ውጪ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ለአሰልጣኙ እንደሚፈጽም ታውቋል።