*… ሰባተኛ የሪከርድ ድላቸው ሆኗል
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ለሰባተኛ ጊዜ መውሰዱን አረጋገጠ።
ፈረሰኞቹ ለ16 ጊዜ የተካሄደውን ሻምፒዮና አሸናፊ መሆናቸውን ያረጋገጡት በቀድሞ ኮከባቸው ፋሲል ተካልኝ የሚሰለጥነውን መቻልን በሀብቶም …ብቸኛ ግብ 1ለ0 መርታት በመቻላቸው ነው። ከፍጻሜ ጨዋታው አስቀድሞ በተካሄደ የደረጃ ኢትዮጵያ ቡናም ለገጣፎ ለገዳዲን 1ለ0 በማሸነፍ ሶስተኛ ሆኖ ጨርሷል።
የፈረሰኞቹ ወጣቶች በነገሱበት 16ኛው የከተማው ዋንጫ ላይ በግማሽ ፍጻሜው በመለያ የፍጹም ቅጣት ምት ኢትዮጵያ ቡናን በዋንጫው መቻልን በማሸነፍ ለነገው ክለባቸው ተስፋ መሆናቸውን ለኢትዮጵያ እግርኳስ የታዳጊዎቾ ችሎታ አለመምከኑን ያሳዩበት ሆኗል። ከዚሁ ጎን የበርካቶች ጥያቄ የሆነው ፈረሰኞቹ ከነዚህ ወጣቶች በቋሚነት እነማንን አሳድገው የወጣቶቹን ተስፋ ያለመልማሉ የሚለው ሆኗል።
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኝ ሳምሶን ሙሉጌታ / ፍሌክስ/ ባለልምዶቹ አሰልጣኞች ገ/መድህን ሃይሌ፣ ተመስገን ዳናና ፋሲል ተካልኝን በመብለጥ ታዳጊ መስራትና ውጤቱን ማየት ትልቅ ደስታ እንደሚፈጥር ያሳየ ህኗል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮውን ጨምሮ በ2002፣ በ2003፣በ2004፣
በ2006፣በ2010፣ በ2012 የውድድሩ ሻምፒዮን በመሆናቸው የከተማውን ዋንጫ ሰባት ጊዜ በመርታት ሪከርድ መያዝ ችለዋል።
በእስካሁኑ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ቡና በ4 ድል፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ3 ድል እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ባህርዳር ከተማ በእኩል አንድ አንድ የዋንጫ ድል የዋንጫ አሸናፊ ክለቦች ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል። በውድድሩ ታሪክ ከከተማው ክለቦች ውጪ ሻምፒዮን የሆነው የአምናው አሸናፊ ባህርዳር ከተማ ብቻ መሆኑ ይታወቃል። ውድድሩ በ1998 ሲጀመር ሻምፒዮን የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲሆን ሻምፒዮናው በ2000 እና በ2013 ሳይካሄድ መቅረቱም ይታወቃል። በዘንድሮ ሻምፒዮና ከዚህ ቀደም የዋንጫ ባለቤት ከሆኑ አምስት ክለቦች መሃል ሁለቱ ባህርዳር ከተማና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሳይካፈሉ ቀርተዋል።
ሻምፒዮናው በስኬትና በሰላም በመጠናቀቁ መደሰታቸውን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ አረጋ እንደተናገሩት
“በከተማችን ፍጹም በሆነ ሰላም ሲካሄድ የነበረው ሻምፒዮና በመጠናቀቁ ተደስተናል እንደ አዘጋጅ ድግሳችንን በሰላም በማጠናቀቃችን ኩራት ተሰምቶናል በተለይ አምና በነበረው የሲቲ ካፑ ውድድር የተፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች በክለቦች ላይ የደረሰው አላስፈላጊ ጉዳትና ውድድሩ ላይ ያጠላው መጥፎ ስሜትን የምንረሳበት ሆኖ በመጠናቀቁ ተደስተናል። በከተማችን ላይ የታየውን እግርኳሳዊ መነቃቃትን ለማስቀጠል ጠንክረን የምንሰራ ይሆናል የፌዴሬሽናችን መሪ ቃል በሆነው ‘ዕውቀታችን ለእግርኳሳችን’ ለሀገራችን በቀጣይ የተሻለ ስራ የምንሰራበት የከተማችን ወጣቶች የተሻለ እግርኳሳዊ ስኬት እንዲኖራቸው የምናግዝ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ውድድሩ በሰላም እንዲፈጸም ትልቅ ድጋፍ ላደረጉት ለስፖርት ቤተሰቡ፣ ለክለቦች፣ ለከተማችን የጸጥታ ሃይሎችና ደፋ ቀና ሲሉ ለነበሩ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና አጠቃላይ ሰራተኞች ውድድሩን በቀጥታ ስርጭት ሲያስተላልፍ ለነበረው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክና ለሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ” ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።