ኢትዮጵያ በሴካፋ እንደምትሳተፍ ተገለፀ !

 

የዘንድሮው የውድድር ዓመት የሴካፋ ከ 17 ዓመት እና 20 ዓመት በታች ውድድር በሩዋንዳ እና ታንዛኒያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ እንደምትሳተፍ ሀትሪክ ስፖርት ያገኘችው መረጃ ያሳያል ።

ከመጪው ህዳር 13 እስከ 27 በታንዛኒያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ 20 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በምድብ ሶስት ከ ኬንያ እና ሱዳን ጋር መደልደላቸው ይፋ ተደርጓል ።

ኢትዮጵያ ከዓመት በፊት ዩጋንዳ ባዘጋጀችው ውድድር ላይ በአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ እየተመሩ ሁሉንም የምድብ ጨዋታቸውን ተሸንፈው አስር ግብ አስተናግደው በዛንዚባር አቻቸው ላይ አንድ ግብ አስቆጥረው መመለሳቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ።

በተያያዘ ዜና ከ 17 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር በሩዋንዳ ከ ታህሳስ 4 እስከ 19 ሲካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ ዩጋንዳ እና ኬንያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ምድብ ሁለት መደልደላቸው ለማወቅ ተችሏል ።

ሀትሪክ ስፖርት ከ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባገኘው መረጃ ከ 20 ዓመት በታች ቡድኑን አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እንደሚመራው ለማወቅ ሲቻል ከ 17 ዓመት ብሔራዊ ቡድን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ መድህን አልያም ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኞች መካከል አንዳቸው ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚረከቡ ለማረጋገጥ ችለናል ።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ዋናው ብሔራዊ ቡድን በዘንድሮው የውድድር ዓመት የሴካፋ ውድድር ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት የማይሳተፍ ይሆናል ።

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor