የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን አዲስ ታሪክ ለመፃፍ የሰዓታት እድሜ ብቻ ቀርቷቸዋል !!

በግብፅ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒየንስ ሊግ ለመሳተፍ የሴካፋ ዞን ማጣርያውን እያካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ በዛሬዉ ዕለት ከቀኑ 10:00 ላይ ከኬንያው ቪጋ ኪዉንስ ጋር በካሳራኒ ስታዲየም የዉድድሩን ዋንጫ ከፍ አድርገው ለማንሳት የሚጫወቱ ይሆናል።

ሁለቱም ቡድኖች ከዚህ ቀደም በአንድ ምድብ ይገኙ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድቡ የመክፈቻ ጨዋታ 4ለ2 ቪጋ ኪዉንስን መርታታቸው የሚታወስ ነው። አሁን ደግሞ በ2014 አዲስ አመት ዋዜማ አዲስ ድል አዲስ ብስራት ሊያበስሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ከዋንጫዉ ደጃፍ ቆመዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኬንያ ቆይታው እስካሁን አራት ጨዋታ አከናውኖ ሁሉንም አሸንፏል፤ 25 ጎሎችን አስቆጥሮ 3 ጎል ብቻ ገብቶበት ለዛሬው ፍፃሜ ደርሷል፤ የቡድኑ ፊውታራሪዎቹ ሎዛ አበራና መዲና አወልም የውድድሩ ክስተት ሆነዋል፤ ቡድኑ ካስቆጠራቸው 25 ጎሎች ሀያ አንዱን ሎዛና አበራ እና መዲና አወል ከመረብ ማሳረፍ ሲችሉ፤ ሎዛ 13 መዲና ደግሞ 8 ግቦችን በማስቆጠር የዉድድሩን ከፍተኛ ግብ አግቢነት በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጋጣሚውን በዛሬዉ ዕለት የሚያሸንፍ ከሆነም ምስራቅ አፍሪካን በብቸኝነት በመወከል በግብፅ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ማለፋቸውን የሚያረጋግጡ ይሆናል።

የዋንጫ ጨዋታ አሸናፊው ከዋንጫ በተጨማሪም 30,000 የአሜሪካ ዶላር ፣ ሁለተኛ ደረጃ 20,000$ እንዲሁም ሶስተኛ ደረጃ 10,000$ ዶላር እንደሚያገኙ ይፋ ሆኗል።

Writer at Hatricksport

Facebook

Ermias Misganaw

Writer at Hatricksport