የተወለደው ሰሜን ሸዋ ዞን ከሸኖ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው መኑሻ የገጠር መንደር ውስጥ ነው፤ ለቤተሰቡ ደግሞ የመጀመሪያ የበኩር ልጅ….የትውልድ አመቱ 1972
ከዛ…..
ገና በስድስት አመቱ እናትና አባቱ በመለያየታቸው ከአያቶቹ ጋር ለመኖር ተገደደ፤ ወላጆቹ ወደ አዲስ አበባ ሄደው ለየብቻ አዲስ ኑሮ ሲመሰርቱ እሱ ከአያቶቹ እርሻ፥ አያቶቹ ቀዬ ውስጥ ቀረ
ከዛ…..
በአስራ አንድ አመቱ የእናትና የአባቱ ናፍቆት ሲበረታበት ወላጆቹን ፍለጋ ከቤት ጠፍቶ በክፍት መኪና ተደብቆ ወደ ሸገር አዱገነት መጣ
የመኪናው መዳረሻ መሀል መርካቶ ነበር። እንዳሰበው ወላጆቹን በቀላሉ ማግኘት ባለመቻሉ ጎዳና መውደቅ እጣፈንታው ሆነ፤ ሰው ከሞላው የገበያ ሰፈር የሰው ናፍቆቱን ይዞ ትንሹ ብላቴና መንገድ ላይ ዋለ፤ በረንዳ ላይ ተኛ
ከዛ…..
ከሁለት ቀን በኋላ አዲስ አበባ የሚኖረው ነጋዴው አጎቱ ያመጣውን ሸጦ ሲመለስ እሱ ደግሞ ጎጃም በረንዳ አካባቢ ምግብ ፍለጋ ሲዞር ድንገት ተገናኙ፤ ለሁለቱም የእድልና የገድ ቀን ሆነ። አጎቱ የገበያ ገድ ሞላለት፤ እሱ ደግሞ እድለኛ ሆኖ በአጋጣሚ የስጋ ዘመድ አጉራሽ አልባሹን አገኘ፤ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ፤ አብረው መኖር ጀመሩ
ከዛ….
ትምህርት እየተማረ ጎን ለጎን አጎቱን ያግዛል፤ ቅቤና እንቁላል ይሸጣል
በአንዱ ቀን የተሰጠውን እንቁላልና ቅቤ ሸጦ ጨርሶ 140 ብር ይዞ ወደቤቱ ሊመለስ ሲል አንድ ሰው አስቆመው። “ጋዝ ግዛልኝ” ብሎ 11 ብርና ጄሪካን ሰጠው፤ ለሚላክበት ደግሞ አምስት ብር ጉርሻ ሸጎጠለት፤ ሰውየው መያዣ እንዲሆን ግን 140 ብሩ እኔ ጋር ይቀመጥ ብሎ ወሰደበት፤ ታዳጊው በአምስት ብሩ የሚበላውን ቀይ ወጥ እያሰበ ጄሪካኑን ይዞ ሄደ
ከዛ…..
ከማደያ ጋዙን ገዝቶ ሲመለስ ሰውየው የለም፤ ብሩን ይዞበት ጠፍቷል፤ የአጎቱን ቁጣና ዱላ ፈርቶ ምን ይዤ ልመለስ ወደ አጎቴ ቤት ብሎ ድጋሚ ጎዳና ወጣ፤ አስር ቀን ውሎና አዳሩ ጎዳና ላይ ሆነ፤ በአስራ አንደኛው ቀን በፍለጋ ተገኘ፤ ተመክሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ አጎቱን በስራ እያገዘ ትምህርቱን ቀጠለ
ከዛ…..
ከልጅነቱ ጀምሮ ያደረበትን የኳስ ፍቅር ለመወጣት ጃንሜዳ መዋል አዘወተረ፤ ግብ ጠባቂ ለመሆን ወሰነ። በአንድ ክለብ የሲ ቡድን በረኛ ምልመላ ላይ ከብዙዎች አንዱ ሆኖ ተወዳደረ፤ ከመጨረሻዎቹ አምስት እጩ በረኞች መካከል አንዱ እሱ ነበር። መልማዩ አሰልጣኝ ግን “እጅ ውርወራ”አትችልም አለው፤ እሱን ለማስተካከል ጃንሜዳ ላይ በርትቶ ሰራ፤ መጨረሻ ላይ ግን “እጅ ውርወራ” የተባለው ገንዘብ አምጣና ወደ ክለቡ ላስገባህ መሆኑን ተረዳ፤ ሳይመረጥ ቀረ….1987 ዓ.ም

ከዛ….
እግርኳስ ተጫዋችነቱ አልሳካ ሲለው ለተሻለ ህይወት ስደትን መረጠ፤ ከአስር ጓደኞቹ ጋር ሆኖ በሱዳን በኩል ግብፅን አልፈው እስራኤል ድንበር ደረሱ። አራቱ ጓደኞቹ ግን የሲና በረሀ ሲሳይ ሆነው ህይወታቸው አለፈ። አንዱ የበረሀ ወዳጁ እጁ ላይ ነው የሞተበት፤ እሱን ጨምሮ በህይወት የተረፉት ስድስቱ እስራኤል ድንበር ላይ ተይዘው አንድ አመት ከስድስት ወር ታስረው ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ….1989 ዓ.ም
ከዛ……
አዲስ ህይወት ልጀምር ብሎ የሰፈር ወጣቶችን እኩዮቹን ሰብስቦ በተለይ በግሩፕ ፀብ አካባቢውን ያሰለቹ ጎረምሶችን ይዞ ጃንሜዳ ላይ ማሰልጠን ጀመረ፤ ይህንን ያየው የወረዳው አስተዳዳሪ የወረዳውን ቡድን እንዲያሰለጥን እድል ሰጠው፤ ከተጫዋቾቹ ጋር ሆኖ ዋንጫ አመጣ፤ ጃንሜዳን ይበልጥ ወደደው፤ አሰልጣኝነትም ጣፈጠው….1990 ዓ.ም
ከዛ……
ብዙ ትኩረት የማይሰጣቸውን ሴቶችን ማሰልጠን ጀመረ፤ ቀዳሚዎቹ የምኒልክ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ ጃንሜዳ የሚሰሩ ሌሎች ሴት ተጫዋቾችም ተቀላቀሉት….1992 ዓ.ም
የቡድኑን ገቢ ለማጠናከር መላ ዘየደ፤ ተጫዋቾቹ እንደ ወንድ ለብሰው ሆያሆዬ እየጨፈሩ ለአዲስ አመት ደግሞ ቀሚስና ሻሽ ለውጠው አበባዮሽ እያሉ ፍራንካ ይሰበስቡና ኳስ ይገዙበታል፤ ለውድድር ምዝገባ ይከፍሉበታል። ለገና እና ለፋሲካ ደግሞ ዶሮ እያጫረቱ እየሸጡ ማሊያ ይገዙበታል

ከዛ……
የቡድኑ ጅማሬ ጥሩ ባይሆንም ብዙ ጎል እየገባበት ቢሸነፍም ተስፋ አልቆረጠም፤ ሴቶችን ከማጀት ወደ ሜዳ እያስወጣ የወቅቱ የአስተሳሰብ ትችትና መገፋትን ችሎ ሙሉ ትኩረቱን እንስት ኳስ ተጫዋቾች ላይ አደረገ፤ ነገ የብርሀን ቀን እንደሚሆን ያምናል
ከዛ….
ሙሉ ቡድኑን የሚወስድ ተገኘ። የካ ክፍለ ከተማ ለአምስት አመት ተረከበው፤ ሁለት ዋንጫዎችን ሳመ። ቀጥሎ ይህንኑ ቡድን ለሴቶች እግርኳስ ታላቅ አስተዋፅኦ ያደረገው አቶ አብነት ግርማይ በባለቤት የሚመሩት ሴንትራል ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በተሻለ ክፍያ ወሰደው። የመጀመሪያ ደሞዙ 100 ብር ነበር፤ ቡድኑ በአምስት አመት ውስጥ ሶስት ዋንጫዎችን አሸነፈ ፤ ደሞዙም 1ሺህ 200 ብር ደረሰ
ከዛ…..
በአንድ አጋጣሚ ምግብ ቤት ውስጥ የተመለከታት ቆንጆ ልቡን ወሰደችው፤ ተዋደዱ፤ ተጋቡ፤ የእሱ ገቢ ብቁ ባለመሆኑ ባለቤቱ ወደ አረብ ሀገር ሄዳ ለሁለት አመት ሰርታ ተመለሰች፤ እሱም በአሰልጣኝነቱ ቀጠለበት
ከዛ……
ከጃንሜዳ ወደ የካ ክፍለከተማ፥ ከየካ ወደ ሴንትራል ኮሌጅ የተሸጋገረው ቡድኑ ከአምስት አመት የሴንትራል ቆይታ በኋላ ንግድ ባንክ ገዛው። ልጆቹን ይዞ እድሜና ልምዱን አካብቶ እስካሁን ለ10 አመት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሰልጥኖ 11 ዋንጫዎችን በባንክ ሼልፍ ላይ አስቀመጠ

ከዛ……
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝነት ከሰሞኑ ለሁለት አመት ውሉን አራዘመ። ለፊርማ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ተቀበለ፤ በ100 ብር ደሞዝ የተጀመረው የብርሀን ጉዞ አሁን ከ50ሺህ ብር በላይ የወር ተከፋይነትን አልፏል
እሱ ሴቶችን በ1992 ማሰልጠን ሲጀምር ብሄራዊ ቡድኑ ግን በ1994 ነበር የተቋቋመው፤ ሉሲዎችን ከአራት ጊዜ በላይ እየተመላለሰ አሰልጥኗል፤ አሁንም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እሱ ነው
ከዛ……
እስካሁን 22 ዋንጫዎችን ወስዷል፤ በሀገር ውስጥና በውጪ ስልጠናዎችን ተከታትሎ ኤ ላይሰንስ ላይ ደርሷል፤ በስደት የረገጣትን ግብፅ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ ተመላልሶባታል፤ አንድ ክለብን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ብቻ ለአስር አመት በማሰልጠን በሀገራችን ረዥም አመት የቆየ አሰልጣኝ የሚል ክብረወሰንን ይዟል፤ አሁንም እዛው ነው፤ በግሉ ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ከስኬት ጫፍ ደርሷል፤ አብራው ኑሮን ከታገለችው ባለቤቱ ጋር በፍቅር የታጀቡ አመታትን አሳልፎ ሶስት ልጆችን አፍርቷል

ከዛ…..
አሁን ደግሞ በ2014 አዲስ አመት ዋዜማ አዲስ ድል አዲስ ብስራት ሊያበስረን ወርቃማ ልጆቹን ይዞ ኬንያ ተገኝቷል፤ ዋንጫ ደጃፍ ቆሟል። በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ማጣሪያ እሱ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ሀሙስ ጳጉሜ 4/2013 ከቀኑ 10:00 ሰዓት ጀምሮ ዋንጫ ለመውሰድ ይጫወታል። የኬንያው ቪሂጋ ኪዊንስ ተጋጣሚው ነው፤ አሸናፊው ምስራቅ አፍሪካን ወክሎ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኬንያ ቆይታው እስካሁን አራት ጨዋታ አከናውኖ ሁሉንም አሸንፏል፤ 25 ጎሎችን አስቆጥሮ 3 ጎል ብቻ ገብቶበት ለዛሬው ፍፃሜ ደርሷል፤ የቡድኑ ፊውታራሪዎቹ ሎዛ አበራና መዲና አወል የውድድሩ ክስተት ሆነዋል፤ ቡድኑ ካስቆጠራቸው 25 ጎሎች ሀያ አንዱን ሎዛና መዲና ናቸው ከመረብ ያሳረፉት፤ ሎዛ 13 መዲና 8፤ አሰልጣኙ ደግሞ የማይሰበረው የብርሀን ተጓዡ እሱ ነው

ከዛ…….
ይህ ሰው ለጨለማው እጁን አልሰጠም፤ መንጋትን እያሰበ ብርሀን እንደሚተካ እያመነ አመታትን በፈተና አሳልፏል። ከመኑሻ እስከ እስራኤል ድንበር፥ ከጎዳና እስከ ተንጣለለ ቪላ፥ ከስደት እስከ አለምን እስከመዞር፥ ከእስር ቤት እስከ ቤተመንግስት፥ ከመቶ ብር ደሞዝ እስከ ሚሊየን ብር የፊርማ ተከፋይ፥ ከእንቁላልና ቅቤ ነጋዴ እስከ ዘመናዊ እርሻ ባለቤት፥ ከጃንሜዳ እስከ ብሄራዊ ቡድን የደረሰ የብርሀን ጉዞ ተምሳሌት ነው
ብርሀኑ ግዛው‼️
ከዛ…….
የብርሀን ተጓዡ የብርሀኑ ግዛው ጉዞ ይቀጥላል!!!
ከዛ……
…………….. ይህ ነጠብጣብ ደግሞ ከዛሬው ጨዋታ ውጤት በኋላ ሙሉ ሆኖ ይፃፋል፤ መልካም እድል ለብርሀን ተጓዡና ለመላው የቡድኑ አባላት!!!
(ታምሩ ዓለሙ)
#ይቺን ለቅምሻ
አስተያየት ይስጡ