ሶስት ኢትዮጵያያን ባለሙያዎች ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ መመረጣቸውን የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል።
በሶስት ሀገራት የጥምር አስተናጋጅነት የሚካሄደው የ2025 የቻን የአፍሪካ ዋንጫ በቀጣይ ነሀሴ የሚጀመር ሲሆን በዚህ ሻምፒዮና በካፍ ቴክኒክ የጥናት ቡድን ውስጥ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በዳኝነቱ ኢንተርናሽናል ረዳት አርቢትር ፋሲካ የኋላሸትና በቫር ዳኝነት ኢንተርናሽናል አርቢትር በዓምላክ ተሰማ መመረጣቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል በሁለቱ ኢትዮጵያዊያን የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተሮች ላይቤሪያ ውስጥ የተሰጠው የኤ ላይሰንስ ስልጠና ተጠናቀቀ።
ላይቤሪያ አዲሱን የካፍ ኮንቬሽን ከፈረመችበት 2020 በኋላ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የኤ ላይሰንስ ስልጠናውን ከተጋባዥ ኢንስትራክተሮች ጋር በመሆን የሰጡት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና ኢንስትራክተር ሰላም ዘርዓይ መሆናቸው ታውቋል።
- ማሰታውቂያ -
አንድ አመት በፈጀውና በአራት ሞጁል ተከፋፍሎ የተሰጠውን ስልጠና 11 የላይቤሪያ 3 የጋምቢያ 1 የዛምቢያ በአጠቃላይ 15 አሰልጣኞች መውሰዳቸው ታውቋል። ከ15ቱ የዛምቢያዋ ብቸኛ ሴት አሰልጣኝ መሆኗ ታውቋል።
የስልጠናው መሪ ሆና የሰራችው የላይቤሪያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ መሆኗ ታውቋል።


