የፋሲል ከነማ ዋንጫ ዱባይ ላይ እየተሰራ ነው ተባለ

የፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒ ለ2013 የሊጉ አሸናፊ ሊሰጥ የነበረው ዋንጫ ለአቡበከር ናስር መሠጠቱ ታውቋል።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ቢሰነብትም ከሊግ ካምፓኒው በተሰጠ መረጃ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ዋንጫውን ለማሰራት ቃል ገብቶ ስራው ቢጀመርም ከደቡብ አፍሪካ ይመጣል ተብሎ ተሰርቶ የመጣው ዋንጫ የሊጉን ደረጃና ኢትዮጵያዊነትን የማይገልጽ ሆኖ በመገኘቱ ሊግ ካምፓኒው ሳይቀበለው መቅረቱ ታውቋል።

የሊግ ኩባንያው ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞና ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ዋንጫው ከደቡብ አፍሪካ እንደሚመጣና ርዝመቱ 80 ሴንቲ ሜትር ኪሎው ከ15 -20 ኪሎግራም እንደሚመዝን ቢገልጹም የመጣው ዋንጫ ተቀባይነት ማጣቱ ታውቋል። ያም ሆኖ ቤትኪንግ የመጣው ዋንጫ ተቀባይነት ቢያጣም “ቤትኪንግ አዋርድ” በሚል የተሻለ አቋም ላሳየ ለመስጠት በመወሰኑ በሶስት የሽልማት ዘርፎች ላይ አሸናፊ ለሆነው የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር መሰጠቱ ታውቋል።

ሊግ ኩባንያው ዋንጫ የሚሰጥበት ቀን በመቃረቡ የተሻለ መፍትሄ ሲያፈላልግ ዋንጫውን ለማሰራት ከጠየቀው
“ሎሚ ኢንተርቴይመንት” ጋር በመስማማቱ የአርቲስት ሳያት ደምሴ ድርጅት የሆነው ሎሚ ኢንተርቴይመንት ዋንጫው ለካፒታል ሆቴል ጠቅላላ ጉባኤም ይሁን ለሸራተኑ የሽልማት መርሃግብር መድረስ ባይችልም እየተሰራ ካለበት ዱባይ ሲመጣ ለፋሲል ከነማ እንደሚበረከት ሊግ ኮሚቴው አስረድቷል።

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport