ኢትዮጵያ ቡናና ቤቲካ የስፖርት ውርርድ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራረሙ

“ቢዝነስ ባልሆነ እግርኳስ ተደራድረን 6 ሚሊየን መፈራረማችን ያኮራናል”
አቶ ገዛኸኝ ወልዴ
/ የኢት.ቡና ዋና ስራ አስኪያጅ/

“የኛ ልዩ መለያችን ለስፖንሰራችን ታማኝ መሆናችን ነው ላማችንን አርደን አንበላም”
አቶ ይስማሸዋ ስዩም
/ የኢት.ቡና የቦርድ አባል/

“ሁለታችንም ተቋማት የተገናኘነው ተፈላልገን ነው”
አቶ አብርሃም ተ/ማርያም
የቤቲካ ኢትዮጵያ ዋና ስራአስኪያጅ

በ8 ሀገራት እየሰራ የሚገኘው ቤቲካ የስፖርት ውርርድ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የ5 አመት የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራረሙ።

ተቋማቱ ባደረጉት ስምምነት ነሀሴ 30/2014 ድረስ 6 ሚሊየን ብር ሊከፈል ተስማምቶ የመጀመርያውን 3 ሚሊየን ብር ቤቲካ ከስምምነቱ ይፋ መደረግ ጋር ተከትሎ የከፈለ ሲሆን ቀሪው በቀጣዮቹ 5 ወራት የሚከፈል ይሆናል ተብሏል። ከነሃሴ 30 በኋላ ተጨማሪ ክፍያው በድርድር የሚካሄድ ይሆናል በማለት የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ተናግረዋል።

አቶ ገዛኸኝ ጨምረው እንደገለጹት “ከቤትኪንግ ኢትዮጵያ ጋር ተነጋግረን ከቤቲካ ጋር እንድንደራደር ፈቅዶልን ስምምነቱን ፈጽመናል ነገር ግን የተከለከለ ነገር በመኖሩ ከተቋሙ ጋር ሰፊ ድርድር አድርገን የሚስተካከለው ተስተካክሎ በመስማማታችን ውሉ ጸድቋል።

አቶ ገዛኸኝ “ቢዝነስ ባልሆነ እግርኳስ ተደራድረን 6 ሚሊየን መፈራረማችን ያኮራናል ሀበሻ ቢራ 70 ሚሊየን ብር የደረሰው ከ1 ሚሊየን ተነስተን ነው ጉዟችን ሲጨምር ክፍያችን እንደሚጨምር ርግጠኞች ነን የተጨዋች ደሞዝ በየአመቱ 75 በመቶ እየጨመረ በሚሄድበት እግር ኳሳችን የፋይናንስ አቅማችንን ማጠናከር ይኖርብናል” በማለት ገልጸዋል።

የክለቡ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ይስማሸዋ ስዩም “ህግ ካላገደን በስተቀር ማሊያችን በስፖንሰሮች ይሞላል በቅርብ ቀን ውስጥ ሌላ ተጨማሪ ስፖንሰርን ይፋ እናደርጋለን የኛ ልዩ መለያችን ለስፖንሰራችን ታማኝ ነን ደጋፊውም ለስፖንሰራችን ደሙን ሰጥቷል ሟች ነው ላማችንን አርደን አንበላም ወተት አይብ ቀስ እያልን እናገኛለን እንጂ…ውላችን 5 አመት ቢልም ሳይቋረጥ ይቀጥላል ብለን እናምናለን ከስፖንሰራችን ጋር በጋራ ለማደግ ነው የተነሳነው..”ሲሉ ተናግረዋል።

የቤቲካ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ተ/ማርያም ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ለተነሱት ቅሬታዎች በሰጡት ምላሽ ” ከ18 አመት በላይ የነበረው ውርርድ ማድረግ የሚቻልበት ዕድሜ ከ21 አመት በላይ ሆኗል ይህን ህግ እናከብራለን ከት/ቤቶች፣ ከሃይማኖት ቦታዎችና ሌሎች የሚከለከሉ ስፍራዎች በስንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ቅርንጫፍ ሊኖረው የሚችለው የሚለው መመርያ ተቀምጧል በአዲሱ ህግ መሠረት ማህበረሰቡን ሊከላከሉ በሚችሉ ደረጃ ተስተካክሏል።

በስራ ላይ ላሉ 42 ተቋማት ውል የሚታደሰው በዚህ ወር መጨረሻ ሲሆን ሊያሟሉ የሚገባቸውን ካላሟሉ በቀጣይ መስራት አይችሉም ስለዚህ ከሀገር ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ችግር አይኖርም ብሄራዊ ሎተሪ በዚህ ደረጃ ሂደቱን እየተቆጣጠረ ነው” ሲሉ ተናግዋል።

አቶ አብርሃም አጽንኦት በሰጡት አስተያየታቸው”ሁለታችንም ተቋማት የተገናኘነው ተፈላልገን ነው የምናገኘው አለ የሚያገኙት አሉ በውላችን ደስተኞች ነን” ሲሉ የኢት.ቡናና የተቋማቸውን ግንኙነት አወድሰዋል።

ቤቲካ የስፖርት ውርርድ በኢትዮጵያ ካለው ከ70 በላይ ቅርንጫፎች ውጪ በኬንያ፣ ሞዛምፒክ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ታንዛኒያ፣ዛምቢያና ኮንጎ የሚሰራ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *