” ካሜሩን በሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሀገሬን ወክዬ መሳተፍ እፈልጋለሁ ” አለልኝ አዘነ /ባህርዳር ከተማ/

ካሜሩን በሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሀገሬን ወክዬ መሳተፍ እፈልጋለሁ “

” ቅጣቱ የተላለፈብኝ በመማታት ሳይሆን ለመማታት በመሞከር በሚል ነበር “

በ15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በሚጫወትበት የአማካይ ቦታ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን በማሳየት ከብዙዎች አድናቆትን አግኝቷል ። ባህርዳር ላይ በተካሄደው የሲቲ ካፑ የፍፃሜ ጨዋታም የጨዋታው ኮከብ ነበር ። ከዚህ ቀደም ለአርባምንጭ ከተማ እና ለሀዋሳ ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል ባሳለፍነው ክረምት ደግሞ ባህር ዳር ከተማን ተቀላቅሏል ። 

አለልኝ አዘነ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረገጽ ጋር ባደረገው ቆይታ ስለ ሲቲ ካፑ ፤ ስለዘንድሮው እቅዱ እንዲሁም ለሀዋሳ ከተማ እየተጫወተ አጋጥሞት ስለነበረው የአንድ አመት ቅጣት እና ሌሎች ጉዳዮች አስተያየቱን ሰጥቷል ።


ሀትሪክ : በቅድሚያ ለ15ኛ ጊዜ በተዘጋጀው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ላይ ሻምፕዮን በመሆናቹ እንኳን ደስ አለክ

አለልኝ : በጣም አመሰግናለሁ

ሀትሪክ : አለልኝ እስኪ ስለ እግር ኳስ ህይወት አጀማመርክ አጫውተኝ

አለልኝ : ኳስን በጨርቅ ኳስ ሰፈር ውስጥ በመጫወት ነበር የጀመርኩት ። ከዛም በትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ እየተጫወትኩ በ2007 በአሰልጣኝ ገረመው የሚሰለጥን ፕሮጀክት ውስጥ መግባት ቻልኩ በመቀጠልም በ2008 የአርባ ምንጭ ከተማን የተስፋ ቡድን ተቀላቀለኩ በዛው አመት ወደ መጨረሻ ላይ በውሰት ለጋሞ ጬንቻ ተጫውቻለሁ ክለቡ ብሄራዊ ሊግ ሲገባ የቡድኑ አባል ነበርኩ ። በ2009 ዓመተ ምህረትም ከአርባምንጭ ከተማ የተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ቻልኩ ። ከዛም በአርባምንጭ ከተማ የሶስት አመት ቆይታ አድርጌ ውሌ እንደተጠናቀቀ ወደ ሀዋሳ ከተማ አመራሁ በሀዋሳም የሁለት አመት ቆይታ ካደረግኩ በኋላ በክረምቱ አሁን ወዳለሁበት ባህርዳር ከተማ ልገባ ችያለሁ ።

ሀትሪክ : ባህርዳር ከተማን እንዴት ልትቀላቀል ቻልክ ከሌሎች ክለቦች የቀረቡልክ ጥያቄዎችስ አልነበሩም ?

አለልኝ : አዎ ሌሎች አማራጮች ነበሩኝ ግን ባህርዳርን የመረጥኩበት ምክንያት ምንድነው ቡድኑ በሊጉ ጥሩ ቡድን ነው ምርጥ ደጋፊ ያለውም ክለብ ነው እና ከኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋር ለመስራት ያለኝ ፍላጎት ወደ ባህርዳር ከተማ እንዳመራ አድርጎኛል ።

ሀትሪክ : በባህርዳር ከተማ የመጀመሪያ የውድድር አመትክን በዋንጫ ጀምረካል ። ከዚህ በፊት በዋንጫ ደረጃ ያሳካሀቸው ድሎች ነበሩ ?

አለልኝ : አዎ አሉ ። ከዚህ በፊት በነበርኩባቸው የአርባ ምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጋር የሲቲ ካፖችን ማሸነፍ ችያለሁ ።

ሀትሪክ : ሲቲ ካፑ በአንተ እይታ ምን መልክ ነበረው ? እንደ ተጫወችም ሆነ እንደ ክለብ ምን አይነት ጥቅም አስገኝቶላቹሀል ?

አለልኝ : በጣም ጠቅሞናል ። ዝግጅት ቶሎ አልጀመርንም ነበር የወዳጅነት ጨዋታዎችንም ማግኘት አልቻልንም ነበር እና በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነው ወደ ሲቲ ካፑ የመጣነው ። እና በጣም ጥሩ ነበር ቡድናችን ያየንበት ነው እንዳየከው ባህርዳር ከተማ ኳስን መስርቶ የሚጫወት ቡድን ነው እየተሰራ ያለው ። ወደ ውድድሩ ስንመጣ አቅደን የመጣነው እስከ ሶስተኛ ባለው ደረጃ ለማጠናቀቅ ነበር ከዕቅዳችንም በላይ አሳክተን ዋንጫውን መብላት ችለናል በዚህም በጣም ደስ ብሎናል ።

ሀትሪክ : በሲቲ ካፑ ባሳየኸው አቋም ከበርካታ ጨዋታህን ከተመለከቱ ተመልካቾች እና የእግር ኳስ ባለሙያዎች ከፍተኛ አድናቆትን አግኝተካል በተጨማሪም በፍፃሜው ጨዋታ የጨዋታው ኮከብ ተብለህም ተሸልመሀል እነዚህ ነገሮች ምን አይነት ስሜት ፈጠሩብክ ?

አለልኝ : በመጀመሪያ የድንግል ማርያም ልጅ እየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይሁን ። አዲስ ቡድን ተቀላቅዬ በመጀመሪያ አመት እንደዚህ አይነት ዕድል በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል ። በቀጣይም በርትቼ እንድሰራ ያደርገኛል ። አሁን ያለውን ነገር እንደጅማሬ ይዤ ወደፊት ማስቀጠል ነው የምፈልገው ።

ሀትሪክ : በሲቲ ካፑ ሻምፕዮን የሆነውን የባህርዳር ከተማ ክለብ በዘንድሮው አመት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከምን እንጠብቀው ?

አለልኝ : እንዳልኩህ በሲቲ ካፑ እስከ ሶስት ባለው ደረጃ ለማጠናቀቅ ነበር ዕቅዳችን ከዕቅዳችን በላይ አሳክተነዋል ። በፕሪሚየር ሊጉም ዕቅዳችን እስከ ሶስት ባለው ደረጃ ለማጠናቀቅ ነው ከፈጣሪ ጋር እናሳካዋለን የሚል ተስፋ አለኝ ።

ሀትሪክ : ከሀገር ውስጥ በልጅነትክ አርአያ የሆነክ እያየከው ያደከው ተጫዋች አለ ?

አለልኝ : አዎ አለ በአርባምንጭ ከተማ ይጫወት የነበረው አመለ ሚልኪያስ የሰፈሬ ልጅ በአቅራቢያዬም የነበረ ስለነበር እሱን እያየው ነበር ያደኩት ።

ሀትሪክ : ከውጪስ ?

አለልኝ : ከውጪ ማይክል ካሪክ እና ፖል ስኮልስ

ሀትሪክ : በአሁን ሰአት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚጫወቱ ተጨዋቾች ላንተ ምርጡ ተጫዋች ማነው ?

አለልኝ : በሊጉ ባለፈው አመትም ጥሩ ነገር እያሳየ ያለው አቡበከር ናስር ነው ። ቀዳሚው ተጫዋች እሱ ነው ለኔ ።

ሀትሪክ : ከውጪስ ?

አለልኝ : ፖል ፖግባ

ሀትሪክ : ትርፍ ጊዜክን በምን ማሳለፍ ያስደስትሀል ?

አለልኝ : ትርፍ ጊዜዬን በአብዛኛው የማሳልፈው በመተኛት እና ፊልም በማየት ነው

ሀትሪክ : እስካሁን ባሳለፍከው የእግር ኳስ ህይወትክ የተደሰትክበት እና ያዘንክባቸው አጋጣሚዎችን ጥቀስልኝ ?

አለልኝ : በጣም ያዘንኩበት አጋጣሚ የመጀመሪያው አርባ ምንጭ ከፕሪሚየር ሊጉ ሲወርድ የቡድኑ አባል ነበርኩኝ እና በጣም ነበር ያዘንኩት በጣም እና በዛው አመት ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማን ገጥመን 1 ለ 0 እየመራን ባለቀ ሰአት ጎል ተቆጥሮብን አቻ የወጣንበት ጨዋታ በጣም የተናደድኩበት ነበር ።
የተደሰትኩበት ደግሞ በ2009 ለአርባ ምንጭ ከተማ የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዬን ያደረኩ ቀን ነበር ።

ሀትሪክ : ከማን ነበር ጨዋታው

አለልኝ : ሀዋሳ ላይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነበር

ሀትሪክ : አለለኝ ከዚህ ቀደም በአንድ አጋጣሚ ከፍተኛ የሚባል ቅጣት ተቀጠክ ነበር በወቅቱ ምን ነበር የተፈጠረው ?

አለልኝ : ሀዋሳ እያለሁ ከመቀሌ 70 እንደርታ ስንጫወት ነበር ያው ከዳኛው ጋር ነበር ከቅጣቱ በኋላም ከእሱ ጋር ያለውን ነገር አውርተናል ። በቴስታ መቶኛል ብሎ ነበር ግን በኋላ ላይ ልክ እንዳልነበር ነግሮኛል ቅጣቱ ሲተላለፍብኝም በመማታት ሳይሆን ለመማታት በመሞከር በሚል ነበር ። እናም ከዛ በኋላ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት ።

ሀትሪክ : ምን ያህል ነበር የተቀጣኸው ?

አለልኝ : አንድ አመት ነበር የተቀጣውት ። በመሃል ኮቪድም ስለነበር በጣም ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት ለመግለጽ በጣም ይከብዳል ። በተቀጣው ሰአት ዮሐንስ ፀበል ሄጄ ነበር እዛም ሆኜ ነው መረጋጋት የቻልኩት ። በወቅቱ የሀዋሳ ከተማ የአሰልጣኞች ስታፍ ፤ ተጨዋቾች የቡድን አጋሮቼ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ከጎኔ ነበሩ እነሱን በዚህ አጋጣሚ በደንብ ማመስገን እፈልጋለሁ ።

ሀትሪክ : የዚህ አመት የግል ዕቅድክ ወይም ማሳካት የምትፈልገው ምንድነው ?

አለልኝ : የመጀመሪያው ዘንድሮ ጥሩ አመትን በማሳለፍ ከክለቤ ጋር በሊጉ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ማሳካት እፈልጋለሁ ። በግሌም ካሜሩን ላይ በሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሀገሬን ወክዬ መሳተፍ እፈልጋለሁ ። ለዛም የቡድኑ አባል ለመሆን የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ ።

 

ሀትሪክ : በመጨረሻም ማመስገን የምትፈልገው አካላት ካሉ ዕድሉን ልስጥህ

አለልኝ : በመጀመሪያ የድንግል ማርያም ልጅ እየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይሁን እላለሁ ። እናቴን ፤ ቤተሰቦቼን ፤ ፍቅረኛዬን እና ጓደኞቼን ማመስገን እፈልጋለሁ በአርባ ምንጭ ተስፋ ቡድን እያለሁ ያሰለጠነኝን አሰልጣኝ ታሪኬ ወደ ዋናው ቡድን ከገባሁም በኋላ አሰልጣኝ በረከት ደሙ ( ፈየራ ) ሀዋሳ ከተማን ስቀላቀል የነበረውን አሰልጣኝ አዲሴን ባጠቃላይ እስከዛሬ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ ። ቅድም እንደጠቀስኩትም መጥፎ ጊዜ ላይ በነበርኩበት ጊዜ ከጎኔ ላልተለዩኝ የሀዋሳ ከተማ ክለብ የአሰልጣኞች ስታፍ እና ተጨዋቾች አመሰግናለሁ ። በመጨረሻም አሁን ያለሁበትን የባህር ዳር ከተማ ክለብ አመራሮች የአሰልጣኞች ስታፍን እንዲሁም የቡድን አጋሮቼን ማመስገን እፈልጋለሁ ።

 

Writer at Hatricksport

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *