የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፓይለት ከአስራ አምስት ዓመት በታች ፕሮጀክት የመክፈቻ ፕሮግራም ተካሂዷል።

ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ተጫዉተዉ ዉጤት የሚያመጡበት እንጅ ስልጠናን መማሪያ መሆን የለበትም” የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ

”መንግስት አምና ብቻ ለእግርኳሱ 2.2 ቢሊዮን ብር ወጭ አድርጓል” ኢንስትራክተር ሰዉነት ቢሻው

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለክልሎችና ለከተማ መስተዳድሮች ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ወንድና ሴት ታዳጊ ወጣቶች የስልጠና ኘሮጀክቶች የመክፈቻና ኘሮግራም የፌዴሬሽኑ አመራሮች እና አሰልጣኞች በተገኙበት በኢሊሊ ሆቴል ዛሬ ረፋድ ተካሂዷል።

ለአራት አመታት በሚቆየው በዚህ ፕሮጀክትም እሰከ 27 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግ ሲሆን ዋና አላማውም ታዳጊዎችን በየክልሉ በማሰልጠን እና ብቁ አድርጎ በማቅረብ ለብሔራዊ ቡድን ግብዓት እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ሲሆን በተጨማሪም እግርኳስ ተጫዋቾች ከልጅነታቸው አንስቶ በስልጠናው ታግዘዉ እንዲያድጉ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነዉ።

ይሄንን አስመልክቶ ዛሬ ረፋድ 4:00 ላይ በኤሊሊ ሆቴል በተካሄደው የመክፈቻ ፕሮግራምም ዝርዝር ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን ከነዚህ መካከልም:-

ከ4 አመት በኋላ በሚደረጉ ከ20 በታች ዉድድሮች ላይ እንደሀገር በሴቶችም በወንዶችም ጠንካራና ተፎካካሪ የሆነ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት በዋናነት አላማ ባደረገዉ ፕሮጀክትም በአጠቃላይ በክልሎች እና ከተማ መስተዳደሮች 760 የሚሆኑ ልጆች ታቅፈዉ ስልጠናው እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

ብሔራዊ ቡድኑ ስልጠናን መማሪያ ሳይሆን ተጫዋቾች ተጫዉተዉ ለሀገራቸው ዉጤት የሚያስመዘግቡበት መሆን አለበት ያሉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸዉ ታዳጊዎችን ከታች በሚገባ አሰልጥነን ከአመታት ቆይታ በኋላ ደረጃውን የጠበቀ ዉጤታማ ብሔራዊ ቡድን መገንባት እንጅ ከታች ሳንሰራ ከዋናዉ ብሔራዊ ቡድን ዉጤት መጠበቅ የለብንም።

በተጨማሪም ይሄ ፕሮጀክት ዉጤታማ እንዲሆን ሁላችሁም የክልል አመራሮች እና ፌደሬሽን ፕሬዝዳቶች እንዲሁም አሰልጣኞች የድርሻችሁን ልትወጡ ይገባል ያሉ ሲሆን ፤ በተለይ በሴቶች ስልጠና ላይ የሚሰማሩ አሰልጣኞም ሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ የስነ ምግባር ጥንቃቄ ማድረግ አንዳለባቸዉ አሳስበዋል።

በመጨረሻም ይሄ ፕሮጀክት ፌዴሬሽኑ ተገዶ የገባበት ስለመሆኑ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ቀደም በታዳጊዎች ላይ በትኩረት ሲሰራ እና ታዳጊዎችን እያሳደገ ለሊጉ ግብዓት ሲያደርግ የነበረዉን የሙገር ሲሚንቶ እግርኳስ ክለብ የጠቀሱ ሲሆን ሙገርም ቢሆን በአሁኑ ሰዓት ከታዳጊዎች አልፎ ዋናዉ ቡድንም መፍረሱ እንደሚያሳዝናቸዉም አያይዘዉ ገልፀዋል።

በፕሮጀክቱም ሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳደሮች አንድ አንድ የወንድ እና የሴት ክለቦችን የሚያቋቁሙ ሲሆን፤ ክለቦቹ የሚቋቋሙትም ክልሎቹ በመረጧቸው ከተሞች ሲሆን ለአብነት በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ እና ወሎ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ ፕሮጀክቶቹ የሚቋቋሙ ይሆናል።

በፕሮጀክቱ ዉስጥ ታቅፈዉ ለዉጥ የማያሳዩ ታዳጊዎችም በሌሎች አቅም ባላቸዉ ልጆች እንደሚተኩ የተገለፀ ሲሆን ፤ ታዳጊዎቹም 18 አመት እስከሚሞላቸዉ ድረስ ስልጠናውን እንደሚወስዱ ተነግሯል።

በመጨረሻም ኢንስትራክተር ሰዉነት ቢሻዉ ታዳጊዎቹን ከእድሜያቸዉ ጋር የሚሄድ ስልጠና ሊሰጣቸዉ እንደሚገባ እንዲሁም የስልጠና መንገዳቸዉ ተለዋዋጭ እንዲሆን በስፍራው ለነበሩት አካላት የገለፁ ሲሆን ፤ መንግስት ለእግርኳሱ እያደረገ ከሚገኘዉ ድጋፍ አንፃርም እግርኳሱ በምላሹ እየሰጠ እንደማይገኝ ሲናገሩ ለአብነትም አምና መንግስት ለእግርኳሱ 2.2 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ገልፀዋል።

አጠቃላይ ለአራት አመታት በሚቆየዉ ፕሮጀክትም የክልል ኮሚሽነሮች እና አሰልጣኞች ታዳጊዎቹን በተገቢው መንገድ ስልጠናቸውን እንዲወስዱ እና በሀገር ፍቅር ስሜት እንዲያሳድጓቸዉ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ አሳስበዋል።

Writer at Hatricksport

Facebook

Ermias Misganaw

Writer at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *