“ከሳሾች በውሸት ቃለመሀላ ፍርድ ቤቱን ያሳሳቱ በመሆናቸው ራሳቸው በህግ የሚጠየቁበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም”
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ
“የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ታገደ ለሚባለው የደረሰን ነገር ባይኖርም በውሸት ቃለመሀላቸው የተሳሳተ ዳኛ ካለ በህግ አግባብ እናስቀለብሳለን” ሲል የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዛተ።
ኦሎምፒክ ኮሚቴውን የከሰሱ ጠበቆች የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ ኦሎምፒክ ኮሚቴው በሰጠው ባለ 6 አቋም የምላሽ መግለጫ “ከሁሉም በላይ እነዚህ ከሳሾች በውሸት ቃለመሀላ ፍርድ ቤት ያሳሳቱ በመሆናቸው ራሳቸው በህግ የሚጠየቁበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እንረዳለን ከዚህ ቀደም በኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ የስፖርት ትጥቆችን መርካቶ ድረስ ሄደው በመቸብቸብ በፈፀሙት ህገ ወጥ ተግባር በኮሚቴው የታገዱ አካላት ስልጣን በሌለው መደበኛ ፍርድ ቤት ከሳሽ ሆነው መቅረባቸውም እጅግ አሳፋሪ ነው ” ሲል የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገልጿል።
- ማሰታውቂያ -
ኦሎምፒክ ኮሚቴውን የከሰሱ ጠበቆች የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ ኦሎምፒክ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ ” የስፖርት ነክ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደማይታዩ እና መደበኛ ፍርድ ቤት ስልጣን እንደሌላቸው እየታወቀ ህግና ስርአትን ተከትሎ ጥያቄ ማንሳት ሲገባ የውሸት ቃለመሀላ በማቅረብ እና ተረኛ ችሎቱን በማሳሳት እግድ ያወጡበት መንገድ ከሳሽ ነን የሚሉት ግለሰቦች ተከራክረው ማሸነፍ የሚችሉበት የእውነተኛ የህግ መሰረት የሌላቸው መሆኑን ያሳያል። በተጨማሪም በውሸት ቃለመሀላ ያገኙትን እግድ ልክ ተከራክረው እንዳሸነፉ መግለጫ መስጠታቸው የቱን ያህል በሀላፊነት እና በተጠያቂነት ስሜት እንደማይሰሩ በግልፅ የሚያሳይ ነው። ሀገርን ለማስቀጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል” ሲል የትድረስ እንደሚሄድ አስጠንቅቋል።
በአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (IOC) ሙሉ በሙሉ የታገደውና እውቅና በግልፅ የተከለከለው እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ያልሆነው በአቶ እያሱ ወሰን የሚመራው የቀድሞው የቦክስ ፌዴሬሽን ከሳሽ ሆኖ መምጣቱ ” እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ” እንዳለችው እንስሳ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ይዤ ልውደቅ ከሚል ክፉ መንፈስ የመነጨ በመሆኑ ይህንን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገነዘበው ለመግለፅ እንወዳለን” ያለው ኦሎምፒክ ኮሚቴው አንዳንድ የሚዲያ ባለሙያዎች ከግለሰቦች ጋር በግልፅ በገንዘብ በመደለል እና በጥቅም በመተሳሰር (ለዚህም በቂ ማስረጃዎች አሉ ) ለህብረተሰቡ የተዛቡ እና ሚዛናዊ ያልሆኑ የአንድ ወገንን መረጃ ብቻ በማቅረብ የስፖርት ቤተሰቡን እያሳሳቱት ይገኛሉ ከህገ ወጥ ድርጊታቸውም እንዲቆጠቡ እናሳስባለን” ብሏል።
“ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ የባለፉትን አራት አመታት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዝደንት ሆኖ ቆይቷል ነገር ግን ራሱን ከደሙ ንፁህ ነኝ በሚል እና ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በነበረበት ወቅት ለማናጀሮች እና ለስፖርት ትጥቅ አምራች ካምፓኒዎች አሳልፎ በመስጠት ብሄራዊ ቡድን ያፈረሰው ራሱ ሆኖ እያለ የስፖርቱ ተቆርቋሪ ሆኖ መምጣቱ እጅግ አሳዝኖናል ለመሆኑ ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ የባለፉትን አመታት የት ነበር ? ” ሲል የጠየቀው የኦሎምፒክ ኮሚቴ መግለጫ ጀግናው አትሌት ገዛኸኝ አበራ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት እንደሆነ ይታወቃል። በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያለበትን የማኔጅመንት ክፍተት ወደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይዞ መምጣቱ ” ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ” የሚባለው ብሂል አይነት ነው” ሲል ተሳልቋል።
በዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እየተካሄደ ያለውን ግልፅ ህገወጥ ተግባር የስፖርት ቤተሰቡ ግራ ቀኙን አገናዝቦ እንዲመለከተው ጥሪውን እናስተላልፋለን ብሏል።