” ወደ 1 ቢሊዮን ብር ኦዲት አልተደረገም የት እንደገባ እንዴትስ እንደወጣም አይታወቅም”
ጠበቆቹ
” ስፖርቱን ላለፉት 35 አመት ለፍቼበታለሁ ገና እለፋለሁ ውስጤ ቁጭት እልህ አለ ስልጣን ግን በፍጹም አልፈልግም”
ጀግናው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ
“ግለሰባዊ አጀንዳ የለንም ይሰቀል ይገደል የምንለው ሰውም የለም ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር የገጠምነው ክርክር ዋናው ዓላማ ስፖርቱን ለመታደግ ብቻ ያደረግነው መሆኑ ታሳቢ እንዲደረግ እንጠይቃለን” ሲል ጀግናው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ ተናገረ።
ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ዙሪያ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍ/ቤት የወሰዱት ጠበቆች ዛሬ በሃይሌ ግራንድ ሆቴል በሰጡት መግለጫ ላይ ኮከቡ አትሌት በሰጠው አስተያየት
” ስፖርቱን እንፈልገዋለን በኛ በኩል ለኦሎምፒክ ኮሚቴ ስልጣን ፍላጎት የለንም በዚህ ስፖርት ላለፉት 35 አመት ለፍቼበታለሁ ገና እለፋለሁ ውስጤ ቁጭት እልህ አለ . በፍጹም ግን ስልጣን አንፈልግም በግላችን ስፖርቱን ከመታደግ ውጪ አመራሮቹን የማሳጣት ፍላጎትንም የለንም ” ብሏል። እንደ ሃይሌ እምነት ” ኬንያ የወሰደችውን ርምጃ እንዲወሰድ የሚታሰር ሰው እንዲኖር አንፈቅድም ይህን ችግር ተሸክመንም ሎስ አንጀለስ መሄድ የለብንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተፈጠረውን ችግር መፍታት ስላልቻለ ብቻ ነው ወደ ፍ/ቤት የሄድነው … በዚህ ጉዳይ መደበኛ ፍርድ ቤት በመሄድ የመጀመሪያ ባለሙያዎች ሳንሆን አንቀርም ይሄ በእውነት ያሸማቅቃል ” ሲል አስተያየት ሰጥቷል።
- ማሰታውቂያ -
ጠበቆቹ በበኩላቸው በሰጡት መግለጫ ” ከሳሾቹ የኢትዮጵያ ቴኒስ እና ቦክስ ፌዴሬሽኖች ሻለቃ ሃይሌ
ገ/ስላሴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ም/ል ፕሬዝዳንት ገዛኧኝ አበራ መሆናቸውና እነሱን ወክለው ችሎት ላይ እንደሚቆሙ አስረድተዋል ። ” እንደ ቅደም ተከተላቸው የኢትየጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እንደ ተቋም በግል ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ ዋናና ምክትል ጸሃፊዎቹ አቶ ዳዊት አስፋውና አቶ ገዛኧኝ ወልዴ እንዲሁም ሃቃቤ ነዋይ ዶ/ር ኤደን አሸናፊ መከሰሳቸውን የገለጹት ጠበቆቹ አራት ፌዴሬሽኖች ክሱን ለመቀላቀል ጠይቀው ጉዳዩን እያዩ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል። ” አራት ፌዴሬሽኖች የዚህ ክስ አካል ለመሆን ጠይቀውናል እያጠናነው ነው ከማን ጋር ነው የምንጋጨው ብለው የሰጉም አሉ ማንም በህግ አንጻር እኩል ነው ብለን ነው የምናምነው የምንጋጨውም ግለሰብ የለም መንግስት ጣልቃ ይገባል ብለንም አንሰጋም” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠበቦቹ አጽንኦት በሰጡት መግለጫቸው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኦዲት አልተደረገም ወደ 1 ቢሊዮን ብር በካሽና በአይነት ያለው ሂሳብ ኦዲት እንዲደረግ ጠይቀናል ወደ 48 ሚሊዮን ብር ለአኖካ ስብሰባ ተብሎ መንግስት ክፍያ ፈጽሟል እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ክፍያ ፈጽመው ኦዲት አልተደረገም ከ400 ሺህ ዶላር በላይ የሆኑ ትጥቆች በየአመቱ ከአዲዳስ ይላካል የት እንደገባ አልታወቀም
ኦሎምፒክ በተደረገ ቁጥር ወደ 600 ሺህ ዶላር የሚገመት ትጥቅ ድጋፍ ይደረጋል ለመላው አፍሪካ ወደፐ 500 ሺህ ዶላር ድጋፍ ተደርጓል ለኦሎምፒክ ውድድር ተሳትፎ 30 ሺህ ዶላር ለስልጠና ተብሎ ከ15-20 ሺህ ዶላር በየአመቱ ይመጣል 198 ሺህ ዶላር ወጣቶችን ለማትጋት ተብሎ ይሰጣል እስካሁን ግን ምንም ኦዲት አልተደረገም ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም የሚጠበቅበት ሃላፊነቱን አልተወጣም በዚህም አዝነናል ዋናው ጥያቄያችን ከላይ የገለጽናቸው ገቢዎች የት ገቡ ወይም ለምን ወጪ ተደረጉ የሚለው ምላሽ ያስፈልገዋል ችሎቱን የጠየቅየውም ይህንን ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ጠበቆቹ አቶ አያሌው ቢታኒ ፣ አቶ ሃይሉ ሞላና አቶ ጳውሎስ ተሰማ ለመደበኛ ችሎት አቀረብን ባሉት የክስ ማብራሪያ ግንቦት 5 እና ሰኔ 14/2016 የተደረጉት ህገወጥ ጉባኤና ውሳኔዎቹ ይሰረዙ፣ ተገቢ በሆነ አግባብ አጠቃላይ ወጪ ላይ ኦዲት ይደረግ በፓሪስ ኦሎምፒክ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንደተካሄደ የሚያሳይ ነገር ስላለ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር እና በፈረንሳይ ኤምባሲ በኩል እነማን ሄዱ እየማን ተመለሱ የሚለው እንዲጣራ ጠይቀናል ሲሉ አብራርተዋል። “ኦሎምፒክ ኮሚቴው በ64 ሚሊዮን ብር ወጪ የውሃ ማምረቻ ፋብሪካ ለማሰራት ማሽኖችን ከውጪ አስገብቷል የገቡት ማሽኖች እውነት ለፋብሪካው ስራ የሚጠቅሙ ናቸው የሚለው ይጣራል ሲሉም ገልጸዋል።
ለመንግስታዊ ተቋሙ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ዳኝነት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ያቀረብነው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘቱ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍ/ቤት እንደ ወሰዱት ያብራሩት ጠበቆቹ
ባህልና ስፖርት ሚ/ር መስሪያ ቤቱም ችሎቱ ፊት ቀርቦ ምላሽ ይሰጣል ለደረሰው ጉዳት ወጪ ይሸፍናል ሲሉ ተናግረዋል። በግልና በኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ላይ የተወሰነው የ11 አካውንት እገዳ ጊዜያዊ ነው እገዳው እስከ ችሎቱ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜ ድረስ የጸና ነው ” በማለትም ሂደቱን ገልጸዋል
ጠበቆቹ አጽንኦት ሰጥተው እንደገለጹት
“የሀገራችንን ስፖርት ለመታደግ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ እንድንሳተፍ የተሰጠን እድል በመሆኑ ስራውን የምንሰራው በደስታ ነው ዋና አላማው የአገሪቱን የስፖርት ሀብት መታደግን ነው ግለሰቦች ተኮር አይደለም ውጤት ጠፍቷል ይሄ ደግሞ እንደ ዜጋ ያገባናል ውጤት ከጠፋ ድጋፎች ይቀንሳሉ ያለፉት ሶስት እሎምፒኮች ውጤት ደግም ለቀጣዩ ስላሰጋን ስፖርቱን ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት ተቀላቅለናል” ሲሉ ገልጸዋል።