“ከሀገሬ ህዝብ ከፍተኛ የሞራል ካሳ እፈልጋለሁ የኔ የሞራል ካሳ ደግሞ የደረሰብኝን የተቀነባበረ ተንኮል እንዲቃወምና ለአትሌቶቻችን ፍትህ እንዲሰጥ ሲያደረግ ነው”
“የኦሎምፒክ ኮሚቴው በቶኪዮ ኦሎምፒክ ከረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በፓሪስ ኦሎምፒክ ከሃይሌና ከእኔ ጋር ተጋጨ …በቀጣይ ኦሎምፒክ ተረኛው አትሌት ማን ይሆን ..? ” አትሌት ገዛኧኝ አበራ
*…. የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሁለተኛ ሰው ስታዲየም እንዳይገባ መደረጉ አነጋጋሪ ሆኗል።
- ማሰታውቂያ -
የማራቶን የኦሎምፒክ ባለታሪክና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ም/ል ፕሬዝዳንት ገዛኧኝ አበራ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍትህ የሰፈነበት የሞራል ካሳ እፈልጋለሁ ሲል ጠየቀ።
የፌዴሬሽኑ ም/ል ፕሬዝዳንት ገዛኧኝ በግሉ ከፈረንሳይ ኤምባሲ ቪዛ አስመትቶ ወደ ፓሪስ ቢያቀናም የወንዶች 10ሺህ ሜትር ፍልሚያን በስታዲየሙ ተገኝቶ በድል ተመለሱ ብሎ የሸኛቸውን አትሌቶች ማበረታታትና ማግኘት ሳይችል ቀርቷል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የገዛኧኝ የስታዲየም መግቢያ ባጅ በኦሎምፒክ ኮሚቴው በመሰረዙ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከማይረሳቸው ጀግኖቹ መሃል አንዱ የሆነውና የኦሎምፒክ የማራቶን ድልን ከ32 አመት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ያደረገው ጀግናው አትሌት ገዛኧኝ አበራ የኦሎምፒክ ኮሚቴውና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ወደ ፓሪስ ከተጓዘው የልኡካን ቡድን ውጪ አድርገውት መጓዛቸው ሳያንስ ባጁ በመሰረዙ መቆጣቱን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እወቁልኝ ብሏል።
ም/ል ፕሬዝዳንቱ እንደተናገረው ” በጣም ተበሳጭቻለሁ አዝኛለሁ ስሜቴ ተጎድቷል ቶኪዮ ላይ በረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ላይ የተሰራው አሳፋሪ ድርጊት በእኔ ላይ ተደግሟል ይሄ የሆነው እሷ እያለች መሆኑ አስገርሞኛል.. እሷ እየጮኧች ዞረች እኔ አልጮህኩም ቁጣዬን አፍኜዋለው የሚለየን በመጮህና ባለመጮህ ነው” ሲል ተናግሯል። ኦሎምፒክ ኮሚቴውም በቶኪዮ ኦሎምፒክ ከረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በፓሪስ ኦሎምፒክ ከሃይሌና ከእኔ ጋር ተጋጨ በቀጣይ ኦሎምፒክ ተረኛው አትሌት ማን ይሆን ..? ሲልም ገዛኧኝ ተሳልቋል።
ትላንት በፓሪስ የወንዶች 10ሺህ ሜትር ፍልሚያ ላይ ከኢትዮጵያ የሄዱ 139 ሰዎች ስታዲዮም ገብተዋል ከነሱ አንሼ የስታዲዮም መግቢያ ተከለከልኩ ዶክተር አሸብርና አቶ ቢልልኝ ጋር ደወልኩ አያነሱም ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ጋር ደውዬ ሳናግራት ምን ይደረግ ከአትሌቶቹ ተቀበል አለችኝ ይሄ ትልቅ አሳፋሪ ድርጊት ነው ለዚህም ከኢትዮጵያ ህዝብ የሞራል ካሳ እጠብቃለሁ” ብሏል።
አትሌት ገዛኧኝ ሲናገር ” ከሀገሬ ህዝብ ከፍተኛ የሞራል ካሳ እፈልጋለሁ የኔ የሞራል ካሳ ደግሞ የህዝቡን ከእውነት ጋር ቆሞ የደረሰብኝን የተቀነባበረ ተንኮል እንዲቃወምና ለአትሌቶቻችን ፍትህ እንዲሰጥ ሲያደረግ ነው አትሌቲክሳችን መጫወቻ መሆን የለበትም ህብረተሰቡም በቃ ሊል ይገባል ይሄ ነው የኔ ትክክለኛ ካሳ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
“የኦሎምፒክ ኮሚቴው ገንዘብ በአትሌቱ ላብ የመጣ ነው 156 ሚሊዮን ብሩ የህዝብ በመሆኑ መንግስት የግድ ኦዲት ማስደረግ አለበት. ተሸፋፍኖ መቅረት የለበትም ባለሙያዎቹ ቦታውን ካልያዙ በየአራት አመቱ የሚነሳው ግጭት የዛሬ አራት አመትም መቀጠሉ አይቀርም” ” ያለው አትሌት ገዛኧኝ “በኦሎምፒክ ኮሚቴውና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ መሃል ከፍተኛ ልዩነት አለ የዶክተር አሸብርና የረዳት ኮማንደር ደራርቱ ዕርቅ ግለሰባዊ እንጂ ተቋማዊ አይደለም የምለው ለዚህ ነው” ሲል የሚሰማውን በግልጽ ተናግሯል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የፓሪስ ኦሎምፒክ የቴክኒክና የህዜብ ግንኙነት ሰብሳቢ አቶ ቢልልኝ መቆያ ለቲክቫህ ስፖርት “ “አትሌት ገዛኸኝ አበራ ወደ ፓሪስ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እንዲመጣ ነው ሁሉ ነገር የተመቻቸለት …. የይለፍ መግቢያ ጉዳይ ግን እኔን ሳይሆን አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እና ዶ/ር ጊዮን ሰይፉን ነው የሚመለከተው በእነርሱ አማካኝነት ነው ለማንም የሚቀየረውም የሚስተካከለውም ” በማለት የሰጡትን አስተያየት ም/ል ፕሬዝዳንቱ ገዛኧኝ አበራ ውሸት ነው ሲል አስተባብሏል።
አትሌት ገዛኧኝ እንደተናገረው ” በኦሎምፒክ ጉዳይ ማንኛውም አይነት ውሳኔ በሚወሰንበት ሰአት ፕሬዝዳንቱ የተከበሩ ዶክተር አሸብር ወ/ ጊዮርጊስ ፣ የአትሌቲክስ ቡድን መሪ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ፣ የቴክናክ ቡድን መሪ አቶ ቢልልኝ መቆያ ፣ ቺፍ ዲሚሽኑ ዶ/ር ጊዮን ሰይፉ፣ ም/ል ዲሚሽኑ ገዛኧኝ ወልዴ፣ ዓቃቤ ነዋይ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ
/ እንግሊዛዊቷ/ ኤደን አሸናፊ ዋና ጸሃፊው ትውልደ ኢትዮጵያዊ / አሜሪካዊው/ አቶ ዳዊት አስፋው አነዚህ ሳያውቁ ምንም ውሳኔ አይወሰንም አቶ ቢልልኝ ይሄ እየታወቀ እኔን አይመለከሀኝም ጉዳዩ አቶ ገዛኧኝ ወልዴና ዶ/ ር ጊዮንን ነው የሚመለከተው ማለቱ ተናበው እንደማይሰሩ ማሳያ ነው ” ሲል ተናግሯል።
አቶ ቢልልኝ የአትሌት ገዛኧኝ የተያዘለት ሆቴል ከፍል አሁንም ባዶ ነው የይለፍ መግቢያውንም መነጋገርና ማስተካከል ይቻላል” ቢሉም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ም/ል ፕሬዝዳንት ገዛኧኝ አበራ ግን ተቃውሞታል።
” የምን ባዶ ክፍል ..? ይሄ ውሸት ነው ፓሪስ ከመጣው በኋላ ነው የሰረዙት አውቀው ላደረጉት የምን መነጋገር ነው..? ከአዲስ አበባ ለመጡት 139 ሰዎችንኳ የተለያየ ሆቴል ነው ክፍል የያዙላየው የኔ ባዶ ሊሆን ቀርቶ ለሁሉም ክፍል ያገኙ አይመስለኝም ” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ዛሬ ደግሞ የ800 ሜትር ሯጯ ጽጌ ዱጉማ አሰልጣኝ አለሙ ዋቅጅራ አትሌቷን እንዳላገኝና የመግቢያ ቦታዬ እንዲገደብ ተደርጎብኛል ሲል ቅሬታውን ገልጿል። “የአትሌቷ አሰልጣኝ አይደለህም ወደ ኢትዮጵያ ተመለስ ተብያለሁ ይሄ ደግሞ ቂም በቀል ነው ” ሲል ቅሬታውን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አሰምቷል።