በውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኙት አዞዎቹ በክለቡ ቦርድ ውሳኔዎች ተላልፈዋል።
በሊጉ ለሁለት ጊዜያት ያህል በመውረድ በድጋሚም በመመለስ እየተካፈሉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው አርባምንጭ ከተማ በአሰልጣኝ በረከት ደሙ መሪነት በያዝነው የውድድር ዘመን ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አራት ተሸንፎ በአራቱ አቻ ወጥቶ አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል በደረጃ ሰንጠረዡ 18ኛ ላይ ለመቀመጥ የተገደደው ክለቡ በትላንትናው ዕለት አመሻሹን የክለቡ ቦርድ ባደረገው ውይይት ለክለቡ ህልውና ይሆናሉ ያላቸውን ውሳኔዎች ወስኗል።
በዚህም መሠረት በቀጣዩ የዘጠነኛ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚኖረው ጨዋታ ቡድኑ ማሸነፍ ካልቻለ በመቀጠልም ሊጉ ከኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ሲመለስ በሚኖሩት ተከታታይ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች ማሸነፍ ካልቻለ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን እንደሚያሰናብት ሲወስን ለቦርዱ ተጠሪ የሆኑ ሦስት የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም እንዲሁም የደጋፊ ማህበሩ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ የክለቡ ቦርድ በዕለቱ ያሳለፈው ውሳኔ ሆነዋል።



