ዋሊያዎቹ በካሜሩን ያውንዴ የሚያደርጉትን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን ለመዘገብ ሙሉ ወጪያቸውን ተችለው ወደ ስፍራው ሊያቀኑ የነበሩ 25 ጋዜጠኞችን የመውሰድ ዕቅድ መክሸፉ ተነገረ።
ደጋፊዎችን ወደ ካሜሩን ለመውሰድ ሙሉ ሃላፊነቱን የተረከበው የሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ባለቤት አቶ ሲሳይ አድርሴ እንደገለጹት “ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመነጋገር 25 ጋዜጠኞችን ሙሉ ወጪ ተችሎ ወደ ካሜሩን የመውሰድ ዕቅዳችን የከሸፈው የራሳቸውን ጥቅም ባስቀደሙና ላንሄድ እንችላለን በሚል ስጋት ውስጥ የገቡ በጣት የሚቆጠሩ ራስ ወዳድ ጋዜጠኞች በሰሩት ተንኮል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ “ከራስ ጥቅም ይልቅ ለሀገራቸው እግርኳስ ቅድሚያ የሰጡና የሀገራቸውን እድገት የሚመኙ የስፖርት ጋዜጠኞችን ለማበረታታት ከፌዴሬሽኑ ጋር በመነጋገር ከፍተኛና የተሳካ የተባለ ስራ ስንሰራ ብንቆይም በስግብግብ ጋዜጠኞች ተንኮል ባለመሳካቱ አዝነናል። እነኚሁ ጋዜጠኞች ሀሰተኛ መረጃ ለስፖንሰር አድራጊዎቹ ተቋማት አመራሮች በመግለጽ በመሃላችን መተማመን እንዳይኖር አድርገዋል።
ፌዴሬሽኑና ሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን በኛና በተቋማችን ላይ ማዘዝ አይችሉም እኛን ስፖንሰር አድርጉን በነሱ በኩል ምንም ጥቅም አታገኙም በሚል ተቋማቱ ላይ ጥያቄ እንዲጫር አድርገው ጋዜጠኞቹ ከየተቋማቱ ማረጋገጫ ደብዳቤ ካላመጡ ገንዘቡን አንፈቅድም በማለታቸው የተቋማቱን ስምምነት እንዲፈርሰ አድርገዋል። ከፌዴሬሽኑ ጋር በመነጋገርም ችግሩ ከአቅም በላይ መሆኑን በመረዳት ዕቅዳችንን ሙሉ በሙሉ ሰርዘናል።
የስፖንሰር አድራጊው ተቋም አመራሮች ደውለው የተፈጠረውን ችግር ሲገልጹ በቀጥታ የሰሙ ጋዜጠኞችም በተፈጠረው ነገር እነርሱም ተከፍተዋል” በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል።
አቶ ሲሳይ በግላቸው ባገኙት ስፖንስር ወደ ካሜሩን የሚጓዙ አራት ጋዜጠኞችም እንዳሉ አስረድተው ደጋፊዎችን የመውሰዱ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉን አሰረድተዋል። የፊታችን እሁድ ጥር 1/2014 በካሜሩን ያውንዴ የሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ሲጀመር ምሽት 4 ሰአት ላይ ኢትዮጵያ ከኬፕቬርዴ ጋር በምታደርገው ጨዋታ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድቧን የመጀመርያ ጨዋታ ታደርጋለች ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
አስተያየት ይስጡ