ዋልያዎቹ የፊታችን እሁድ በይፋ ለሚጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከታህሳስ 17 ጀምሮ ወደ አዘጋጇ ሀገር ካሜሩን በመጓዝ ዝግጅታቸውን እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል ።
ወደ ስፍራው ከማቅናታቸው በፊት ከተቻለ ሁለት ወይም ሶስት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም ባሳለፍነው ሀሙስ ከሱዳን ብሄራዊ ቡድን ጋር ከተደረገው ጨዋታ በኋላ ከሴኔጋል አሊያም ከዚምባቡዌ ብሄራዊ ቡድን ጋር ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል ። በዚህም ብሄራዊ ቡድኑ ከዚህ በኋላ ሌላ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሳያደርግ በመጪው እሁድ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ለሚደረገው የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ጨዋታ ዝግጅቱን የሚቀጥል ይሆናል ።
በተያያዘም ብሄራዊ ቡድኑ በካሜሩን በቆየባቸው ባለፉት ዘጠኝ ቀናት ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ሲሸፈንለት የቆየ ሲሆን ከነገው ዕለት ጀምሮ ግን ወጪው በአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ( ካፍ ) የሚሸፈን ይሆናል ። እንዲሁም እስካሁን የነበረበትን ሆቴል በመቀየር ካፍ ወዳዘጋጀለት ሌላ ሆቴል የሚያመራ ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ