የአዲስ አበባ ከተማ ሲቲ ካፕ መስከረም 15 ይጀመራል

የምድብ ድልድሉም ይፋ ሆኗል

ስምንት ክለቦች የሚሳተፉበት 15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከመስከረም 15 እስከ 30/2014 በአበበ ቢቂላ እንደሚካሄድ ይፋ ሆነ።

ቤስት ዌስተርን ሆቴል በተካሄደ መግለጫ የአዲስ አበባ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መከላከያ አዳማ ከተማ፣ ባህርዳር ከተማ፣ ፋሲል ከነማና ከውጪ የደቡብ ሱዳኑ ሙኒኪ ኤፍ ሲ ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናና ባህርዳር ከተማ በሲዳማ ካፕ ይሳተፋሉ የሚለውን መረጃ ያስተባበሉት የፌዴሬሽኑ ሃላፊዎች ሶስቱም ክለቦች በሲቲ ካፑ እንደሚካፈሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ውድድሩን በዲ ኤስ ቲቪ የማስተላለፍ ሙከራ ተደርጎ ባይሳካም በአገሪቱ አንድ ሚዲያ እንደሚተላለፍ አመራሮቹ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

በዚህም መሠረት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የቲኬት ዋጋ ይፋ የተደረገ ሲሆን ሲካሄድ ለክቡር ትሪቩን 500ብር ለጥላ ፎቅ 300ብር ለከማን አንሼ 200 ብር መሆኑ ታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአመታዊው የሲቲ ካፕ የሰጠው ትኩረት ዋጋ የሚያሰጠው ነው ሲሉ ገልጸዋል።

“በከተማ አስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ በመገኘታቸው አመስግናለሁ”ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ዣንጥራር በበኩላቸው” የከተማው ፌዴሬሽንና ስፖርት ኮሚሽን በጋራ በሚያከናውኑት የዘንድሮ ሲቲ ካፕ ዙሪያ አብረን እንድንሰራና መመርያ እንድንሰጥ ላደረጉት ጥሪ አመሠግናለሁ የከተማውን ወጣት ልብ በሚይዝ መልኩ የከተማው እግር ኳስ አድጓል ብለን ባናምንም የከተማው እድገት የተሻለ ቦታ እንደሚደርስ ጭላንጭል አይተናል የከተማው ክለብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደገበት ሰአት የሚካሄድ ሲቲ ካፕ በመሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው”
ሲሉ አስረድተዋል።

“የሲቲ ካፕ ውድድር ላይ የሚካፈሉት ክለቦች በጋራ በፍጹም ዲሲፕሊን ውድድራቸውን እንዲያጠናቅቁ የከተማውን ስም የማስጠበቅ ስራ እንዲሰሩ እጠይቃለሁ” ያሉት አቶ ዣንጥራር “ስፖርት ለሀገሪቱ ሰላም ወሳኝ ሚና ስላለው ለመከላከያ ሰራዊታችን ድጋፍ የሚሰጥ ውድድር እንዲሆንም እመኛለሁ” ሲሉ የስራ መመርያ ሰጥተዋል።

በእለቱ በጣው የምድብ ድልድል መሰረት

ምድብ አንድ

– ኢትዮጵያ ቡና
– አዲስ አበባ ከተማ
– መከላከያ
-ሙኑኪ (ተጋባዥ)

ምድብ ሁለት
– ቅዱስ ጊዮርጊስ
– ባህር ዳር ከተማ
-አዳማ ከተማ
-ፋሲል ከነማ

በመሆን ተደልድለዋል ።

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport