*… ባለፉት አመታት ማህበሩ ፍቃዱን አላሳደሰም….
የአዲስ አበባ ከተማ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበርን አጠናክሮ የባለሙያዎችን ጥቅም ማስከበር በሚችልበት አቅም ለማድረስ ያለመ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ተካሄደ።
በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ አረጋ በተመራውና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ሚካኤሌ አርዓያ እንዲሁም የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት የማህበራት ማደራጃ ተወካይም ተገኝተው ማህበሩን ለማጠናከር በሚጠቅሙ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
- ማሰታውቂያ -
ማህበሩ ባለፉት ስድስት አመታት ፍቃዱን ሳያሳድስ ከመቅረቱም በላይ የከተማውን ዳኞችና ታዛቢዎችን ጥቅም ማስጠበቅ ያልቻለ፣ የማህበሩን ተልዕኮዎችና አላማዎችን ሳያስከብር የቆየ መሆኑን ተሰብሳቢዎቹ የተማመኑበት ሆኗል። ዳኞቹና ታዛቢዎቹ ባለፉት 6 አመታት የደረሰባቸውን መንገላታት በማስረዳት መብታቸውን የሚያስከብር ማህበር እንደሌላቸው በመግለጽ ለአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ በተለይ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ አቶ ደረጄ አረጋ የቅድሚያውን ሀላፊነት በመውሰድ ውይይቱ መዘጋጀቱ ታውቋል።
ፌዴሬሽኑ ተበድለናል መብታችን አልተከበረም ካሉ ቅሬታ አቅራቢ ዳኞችና ታዛቢዎች ጋር ውይይቶችን አድርጎ ሰባት ተወካዮች የተመረጡ ሲሆን ፍቃዱን ሳያሳድሱ ባለፉት ዓመታት እንደ ማህበር ሲንቀሳቀሱና ማህበሩን ሲመሩ ከነበሩት አመራሮች ጋር ዛሬ ያደረጉት ውይይት ስምምነት ተደርሶበታል።
ውይይቱ ሲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ከተማ ዳኞችና ታዛቢዎችን ህጋዊነት በመጠበቅና ጠንካራ ማህበር ለማቋቋም በመስማማት የተመረጡት አስተባባሪዎቹ ሁሉም የአዲስ አበባ ዳኞችና ታዛቢዎች እንዲገኙ ጥሪ በማድረግ ጥቅምት 20/2015 የምስረታ ጉባኤውን ለማካሄድ ወስነዋል።