አማራ ክልል ለፕሬዝዳንትነት ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸውን አቶ ተካ አስፋውንና ኢንስ.ሰውነት ቢሻውን ዕጩ አድርጎ አቀረበ
በይስሐቅ በላይ
ምክንያቱ ባልተገለፀ ሁኔታ ከሰመራ
ወደ አዲስ አበባ የተዛዋወረው የኢትዮጵያ
እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤና ምርጫ
የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፤ ለፕሬዝዳንትነትና
ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ለመመረጥ
የሚደረገው ግብግብና ሩጫም እስከ መጨረሻዋ
የማሳወቂያ ቀንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
ፕሬዝዳንታዊና የስራ አስፈፃሚ ኮሜቴ
አባልነት ምርጫ እስከዛሬ ያልታየና የጠነከረ
የምረጡኝ ግብግብ የታየበት ነው የተባለው
የዘንድሮው ምርጫ የዕጩዎችን የማሳወቂያ
የመጨረሻ ቀነ ገደብ ነገ የሚጠናቀቅ ቢሆንም
ክልሎችና ፌዴሬሽኖች እጩዎቻቸውን
መርጠው ለማሳወቅና ድጋፍ ለመስጠት ፈተና
ውስጥ መውደቃቸው ብዙዎችን ከወዲሁ
እያነጋገረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
እጩዎችን ማሳወቂያ ብሎ የቆረጠው
የመጨረሻ ቀን ነገ /ረቡዕ/ ሲሆን እስካሁን
እጩዎቻቸውን በይፋ ያሳወቁት ጥቂት
ክልሎችና ፌዴሬሽኖች መሆናቸው ነው
እየተሰማ ያለው፤ ሀትሪክ ከታማኝ ምንጮች
ባገኘችው መረጃ መሰረት የአማራ ክልል
ፌዴሬሽን በብዙዎች ዘንድ ለፌዴሬሽኑ
ፕሬዘዳንትነት ሲመኝዋቸውና እንዲመጡ
ሲመቻቸው የነበሩትን የህግ ባለሙያው አቶ
ተካ አስፋውንና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ
የማይነቃቃ ሀውልት ለመተከል የበቁትን
ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ለስራ
አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ያለምንም ውዝግብና
ጭንቀት በሙሉ ድምፅ መወከላቸው በይፋ
የተረጋገጠ ሲሆን ድሬዳዋ በበኩሉ የኢትዮጵያ
እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ
ጁነዲን ባሻህን በድጋሚ ለመጪዎቹ አራት
ዓመታትም ከፌዴሬሽኑ ፅ/ቤት እንዳይወጡ
እጩ አድርጎ መወከሉ ነው የተሰማው፡፡
በምርጫው ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል
ተብለው የሚጠበቁት የኦሮሚያና የትግራይ
ክልሎች እስካሁን እጩዎቻቸውን ለማሳወቅና
ለመወሰን እንደተቸገሩ የተሰማ ሲሆን
ምናልባትም ትናንትናና ዛሬ የሚወክሏቸውን
እጩዎች ያሳውቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ይፋ ያልሆኑ ወይም ማረጋገጫ ያልተገኘባቸዉ
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የኦሮሚያ
እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቀድሞው የባንኮች
የቅድስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች
የነበረውን አንተነህ ፈለቀን ለፕሬዝዳንትነት
የኦሉምፒክ ኮሜቴን ለረጅም ዓመታት በዋና
ፀሐፊነት ያገለገሉትን አቶ ታምራት በቀለን
ለስራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባልነት እጩ
ለማድረግ እንደወሰነ ሲነገር አቶ ተክለወይኒን
ለፕሬዘዳንትነት እጩ አድርጎ ይልካል ተብሎ
በስፋት ሲነገር በቆይታ ከእሳቸው ይልቅ
ሌሎች ሁለት እጩዎችን በተለይ አመለሸጋው
የቀድሞው አርቢትርና የቢዝነስ ሰው የሆነው
አቶ ሰለሞን አለምሰገድን ለስራ አስፈፃሚ
ኮሜቴ አባልነት በእጩነት ለማቅረብ እንዳሰበ
ነው በተባራሪ ወሬ ደረጃ እየተሰማ ያለው፡፡
እስካሁን ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት
ሰአት ድረስ ውጤቱ በጉጉት እየተጠበቀ ያለው
አዲስ አበባ ማንን ይወክላል?የሚለው ሲሆን
ከሰባት የበለጡ አመልካቾች ለፕሬዝዳንትነትና
ለስራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባላልነት እጩ ሆነው
ለመቅረብ ያመለከቱ ሲሆን ማን አዲስ አበባን
ይወክላል? የሚለው በጉጉት እንዲጠበቅ
አድርጎታል፡፡ በዚህ በኩል አዲስ አበባ
ኢንጅነር ኃይለየሱስ ፍስሐን ለስራ አስፈፃሚ
ኮሜቴ አባላልነት ዕጩ አድርጎ የወከለ
ሲሆን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ እስካሁን ማንን
እንደሚወክል የታወቀ ነገር የለም፡፡ በዚህ
በኩል በተለይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከ50
ዓመት በላይ በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት
ስኬታማ ጊዜን በማሳለፍ ስሙን በወርቅ
ታሪክ ለማፃፍ የበቃው አሰልጣኝ አስራት
ኃይሌ በአሰልጣኞች ማህበር ተመርጦና
ድጋፍ አግኝቶ ለአዲስ አበባ ያቀረበው ጥያቄ
በአመራሮቹ ችላ ተብሎ መታለፉና ውክልናው
ከእሱ ይልቅ ለሌሎች መስጠቱ ከወዲሁ
እያነጋገረ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ
ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ
ለፌዴሬሽኑ አመራርነት የሚመጡ በስፖርቱ
ውስጥ ያለፉ፤ በቂ ጊዜ ያላቸው መሆን
አለባቸው የሚለው መመሪያና የመንግስት
አቅጣጫ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
ከማስፈፀም ይልቅ አስራት ኃይሌን ውክልና
በመንፈግ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መመሪያ
የጣሰ የሚመስል ውሳኔን አስተላልፏል በሚል
በብዙዎች እየተኮነነ ነው፡፡ አሰልጣኝ አስራት
ኃይሌ ከ50 ዓመት በላይ ህይወቱን በሙሉ
ለእግር ኳሱ ሰጥቶ እንዴት ውክልና ይነፈጋል
በሚል ብዙዎች በአዲስ አበባ ላይ ቅሬታቸውን
እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
የዘንድሮውን ምርጫ አስመልክቶ
እስካሁን የብዙዎችን ይሁንታና ድጋፍ
ያገኘው የአማራ ክልል ያደረገው የእጩዎች
ምርጫ ስፖርት ቤተሰቡንና የመንግስትን
ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው በሚል ውደሳ
እየቀረበለት ነው፤ በዚህ በኩል በተለይ
የቀድሞው የኢ.እ.ፌ ተቀዳሚ ባገለገሉበት
ጊዜ ለሰማቸው መጠሪያ የሚሆን ታላቅ ስራን
የሰሩትን አቶ ተካ አስፋውን እንዲሁም ዘሬም
ድረስ በሰሩት ስራ በስፖርት ቤተሰቡና በህዝቡ
የሚከበሩትንና የሚወደዱትን ኢንስትራክተር
ሰውነት ቢሻውን በብዙ ማግባባትና ማሳመን
ለእጩነት ማቅረቡ ክልሉ ከወዲሁ
በምርጫው እንዲወደስ አድርጎታል፡፡ በዚህ
በኩል በተለይ ወደ ፌዴሬሽኑ ስልጣን
እንዲመጡ በሚዲያውና በስፖርት ቤተሰቡ
በተደጋጋሚ ግፊት ሲደረግባቸው የነበሩት
የህግ አማካሪውና ጠበቃው አቶ ተካ አስፋው
ዳግም ምርጫ ውስጥ መግባታቸውንና
ለፕሬዝዳንትነት መወዳደራቸው ብዙዋችን
አስማምቷል፡፡ አቶ ተካ አስፋው በፌዴሬሽኑ
የስልጣን ዘመናቸው በሰራቸው በርካታ
ሰራዎች የብዘዎችን እምነት ብቻን ሳይሆን
ይሁንታን ከወዲሁ እያገኙ ሲሆን ቀጣዩ
የፌደሬሽኑ ፕሬዘዳንትም ሊሆኑ እንደሚችሉ
እየተገመተ ነው፡፡
በሙያቸው የህግ አማካሪና ጠበቃ የዳሽን
ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ተካ አስፋው
ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ አገሪቱ እግር
ኳስ የመጨረሻው ወንበር ለይ ለመቀመጥ
መንገድ መጀመራችን ብዙዎች እርግጠኝነት
በተሞላበት ስሜት ከምርጫው በፊት እየገለፁ
ይገኛሉ፡፡ እንደዚህ ለማለት ያበቃቸውን
ምክንያት የሚያስቀምጡት እነዚህ አስተያየት
ሰጪዎች አቶ ተካ አስፋው በኢትዮጵያ
እግር ኳስ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ
በሁለቱም ባላንጣና (ተፎካካሪ) ቡድኖች
በሆኑት በቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና
ደጋፊዎች እኩል መወደዳቸውና በፌዴሬሽኑ
የስልጣን ዘመናቸው ፌዴሬሽኑን ከብክነት
ከመታደጋቸው ውጪ የወንዶችና የሴቶች
ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች
በአንድ የስልክ ጥሪ ብቻ የ10 ሚሊዮን
ብር ሽልማት እንዲያገኙ ያስቻሉ ለህግ
የበላይነት የቆሙ የውጪ ጉዞ ሲኖርም
ከፌዴሬሽኑ ካዝና ሳይሆን ከግል ኪሳቸው
በማውጣት የሚጠቀሙና ከፌዴሬሽኑ ካዝና
ሰባራ ሳንቲም የማይወሰዱ የብሄራዊ ቡድኑን
ቱታ ለመውሰድ ከፊት የማይሰለፉ በአጭሩ
በፌዴሬሽኑ ለመጠቀም ሳይሆን ፌዴሬሽኑን
ለመጥቀም የሚመጡ የትልቅ ስብዕና ባለቤት
የሆኑና ከፌዴሬሽኑ ኃላፊነት ከወረዱ በኋላም
ከስቴዲየም የማይጠፉ ብቸኛ የቀድሞ
አመራር መሆናቸው ብዙዎች ለቦታው
በቅድሚያ እንዲያጫቸው ምክንያት እንደሆነ
እየተነገረ ነው፡፡ የአማራ ክልል አቶ ተካ
አስፋውን ለፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንትነት እጩና
አድርጎ ማቅርቡን በተመለከተ አቶ ተካ
የመወከል እድሉን ቢያገኙም ምን ለመስራት
አስበዋል?ምንስ አዲስ ነገር ይዘው ይመጣሉ?
የሚለውን ለማወቅ ወደ ተንቀሳቃሽ የእጅ
ስልካቸው ላይ ብንደውልም አቶ ተካ
ከአገር ውጪ በመሆናቸው ጥረታችን
የተሳካ ሊሆን አልቻለም፡፡አቶ ተካ አስፋው
ወደ አገር ቤት የሚመለሱ ከሆነ በቀጣይ
ዕትማችን በእጩነታቸውና ምን ለመስራት
እንዳሰቡ?ምንስ አዲስ ነገር ይዘው እንደመጡ
አነጋግረናቸው ለመቅረብ እንሞክራለን።
ከዚሁ ከጠቅላላ ጉባኤው ምርጫና
የእጩዎች ውክልና ዜና ሳንወጣ የደቡብ
ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስልጣን
ዘመኑን ባጠናቀቀው ፌዴሬሽን ውስጥ በስራ
አስፈፃሚው ኮሚቴ አባልነትና በቴክኒክ
ኮሚቴ ሰብሳቢነት ሲያገለግሉ ለነበሩት ለአቶ
ዘሪሁን ቀቀቦና የቀድሞውን አርቢትር ሸረፋ
ደሌቾን ለስራ አስፈፃሚ ኮሜቴነት በእጩነት
ለመወከል መወሰኑ ነው እየተሰማ ያለው፡፡
አስተያየት ይስጡ