ለፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ የኮሚኒኬሽን እና ማርኬቲንግ ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ከካፍ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ክለቦች የኮሚኒኬሽን እና የማርኬቲንግ ባለሙያዎች ለሦስት ቀናት ቦሌ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል ሲሰጥ የነበረው የክፍል እና የተግባር ስልጠና ዛሬ ተጠናቀቀ። ስልጠናውን የሴካፋ ማርኬቲንግ እና ኮሚኒኬሽን ባለሙያ እና የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር (ካፍ) የሚዲያ ኦፊሰር በመሆን አንድሪው ጃክሰን ኦሪያድ የሰጡ ሲሆን እግር ኳስን ለማሳደግ የክለብ ሚዲያዎች ሚናዎቻቸው ምን እንደሚመስል እና አንድ የእግር ኳስ ክለብ ራሱን የተሻለ ለማድረግ የሚዲያ ስራው ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት እንዴት መስራት እንዳለበት በሚል ስልጠናው መሰጠት ችሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ከጨዋታ በፊት እና በኋላ ቃለ መጠይቆችን ባለሙያው እንዴት መስራት ይኖርበታል በስታዲየም ውስጥም ፎቶ በሚያነሳበት ወቅት የአነሳስ ትግበራው ምን ይመስላል የሚሉ ይዘቶችን ያዘለ ዝርዝር ጉዳዮችን ማካተት የቻለ ሰፊ ስልጠና ነው መሰጠት የቻለው ከሚዲያ ባሻገር ስልጠናው በማርኬቲንግ ላይም ትኩረት ያደረገ ሲሆን ክለቦች ራሳቸው በይበልጥ ለማስተዋወቅ እና ለመሸጥ ምን አይነት ሂደቶችን መከተል እንዳለባቸውም ጭምር በዚህ ስልጠና ላይ መካተት ችሏል።

ዛሬ ስልጠናው ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የካፍ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኢሳያስ ጂራ በመዝጊያው ዕለት ተገኝተው እንደተናገሩት ይህ ስልጠና የክለቦችን አቅም ለማሳደግ ጉልበት እንዳለው ገልፀው ፕሮፌሽናል የሚዲያ አሰራር ለሀገራችን እግር ኳስ ዕድገት አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል። ስልጠናውን የሰጡት አንድሪው ጃክሰን በበኩላቸው በኢትዮጵያ ቆይታቸው ጥሩ የስልጠና ጊዜ እንደነበራቸው እና ተሳታፊዎችም በጥሩ ተነሳሽነት እንደተከታተሏቸው ጭምር ተናግረዋል።
አስተያየት ይስጡ