ከባለፈው ሳምንት የቀጠለ የመጨረሻ ክፍል
በይስሐቅ በላይ
“ከውጪ ደጋፊ ነው ትባላለህ… ጊዮርጊሶች ደግሞ አታጫውተን፣ ገደልከን እያሉ ያማርሩሃል… በመሀል ሳንድዊች የሆንኩት እኔ ነኝ”
“እኔን ወደ ላይ ያወጡኝ ከፍ ያደረጉኝ የቡና፣ የጊዮርጊስና የሁሉም ክለብ ደጋፊዎች ናቸው”
ኢንተርናሽናል አርቢትር ኪነ ጥበቡ ከአሜሪካ መልስ

…
ሁሌም ያየኝም…ያላየኝም…ኪነ የቅዱስ ጊዮርጉስ ደጋፊ ነው ይልሃል….ልሁና መደገፍ ምንድነው ክፋቱ…?…እንደዚህ የሚያወሩ ሰዎችን እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃቸው…?…እኔ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አዳልቼ…ወይም…በእኔ የተዛባ ዳኝነት…ቅዱስ ጊዮርጊስ ምን ያገኘው ነገር አለ…?…ከአሉባልታ ወይም የሰውን ስም ከማጥፋት በዘለለ ማነው እንዲህ አድርገሀል ብሎ ማስረጃ የሚያቀርብ ወንድ?…ዳኝነት ከጀመርኩበት እስከአሁን ለጊዮርጊስ ይሄን አድርጓል ብሎ ማስረጃ የሚያቀርብ ካለ እሸልመዋለሁ ብቻ ሣይሆን በይፋም ይቀርታ እጠይቃለሁ…ግን ከወሬ ከአለባሉታ በዘለለ ይሄን የሚያደርግ የለም…፡፡
ይሄንን ከላይ ያለውን አስተያየት በተለይ ለሀትሪክ የሰጠው ኢትዮጵያን በኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ በመወከል የከበረ ስም ያተረፈው የቀድሞ አርቢትር ኪነ ጥበቡ ነው፤ ባለፈው ሳምንት ከሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዮቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር ቁም ነገር ያዘለ ቆይታ ያደረገው የቀድሞው ኢንተርናሽናል አርቢትር ኪነ ጥበቡ ዛሬ ደግሞ የመጨረሻ በሆነው ቃለ-ምልልሱ ኮርኳሪና ስሜትን ሰቅዘው የሚይዙ ጥያቄዎች ተነስተውለት ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ እና ኪነ ጥበቡ የመንግስት መቀመጫ በሆነችው አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አካባቢ በነበራቸው ቆይታ በተለይ ለሀሜት ስለዳረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊነቱ፣ ስለሚያደንቃቸው ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች፣ በደጋፊነት የሚታማባቸው ቅ/ጊዮርጊሶች “አንተ እየጎዳኸን ነው እባክህ አታጫውተን” እስከማለት ስለደረሱበት አጋጣሚ፣ ሀገሩን በኢንተርናሽናል መድረክ ስለወከለበትና ለቅጣት ስለተደረገበት ሁኔታ ብቻ ሁሉንም ሳይሰስት አጫውቶናል፡፡ ኪነ ጥበቡ ጊዜውን ሰውቶ ለቃለ- ምልልሱና ሀሜቶችን ለማጥራት ላሳየው ቀና ትብብርና ድፍረት የተሞላበት ምላሽ በአንባቢያን ስም ማመስገን እንወዳለን፡፡
ሀትሪክ፡- ባለፈው ሣምንት ከአንተ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ያጠናቀቀው ብዙዎች ለማወቅ ስለጓጉለት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊነትህ ጋር ስም ተያይዞ ስለመነሳቱ ነው፤ምንም መደባበቅ፣መወሻሸት አያስፈልግም…ኪነ በእርግጥም የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊ ነው…?…
ኪነ፡- የሚገርምህ ነገር እንደዚህ አይነቱ ጥያቄ ዳኝነት ስጀምር ጀምሮ የሚመጣ ጥያቄ ነው…አሁንም ዳኝነት አቁሜ፣ አሜሪካን ሀገር 15 አመት አሳልፌም ያልለቀቀኝ በተደጋጋሚ የምጠየቀው ጥያቄ ነው… ይሄ ጥያቄ መጠየቅ ካለበት…እኔም የግድ መመለስ ካለብኝ እመልሳለሁ…ከዚያ በፊት ግን አንድ ጥያቄ አንተን ራስህን ልጠይቅህ…?…

ሀትሪክ፡- …(ድንገት አቋረጥኩትና)… ኪነ አንተ ዛሬ ተጠያቄ ነህ እንጂ ጠያቄ አይደለህም…እኔ ከአንደ በትህ መስማት የፈለኩት…ኪነ እንደሚታማው የቅ ዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነው አይደለም…?…የሚለውን ነው…?…
ኪነ፡- …(እሱም ከአፌ ነጠቀኝና)…ቆይ እንጂ አትቸኩል…. ልመልስልህ እኮ ነው…ማንኛውም ሰው በተጫዋችነት፣ በአሰልጣኝነት፣ በአመራርነት፣ በዳኝነት ወደ እግር ኳስ ሲመጣ…ኳሱን ወዶ፣ ክለቦችን ወይም ተጨዋቾችን ወዶና አድንቆ ነው…በዚህ መስመር ሳታልፍ ከኳስ ጋር ቅልጥ ያለ ፍቅር አትመሰርትም…ወደ ስታዲየም የምትሄደው አንድ የምትወደው የምትደግፈው ቡድኔ ፍለጋ ነው… አንተም ጋዜጠኛ ከመሆንህ በፊት የምትደግፈው ቡድን የምታደንቀው ተጨዋች እኮ ይኖራል…በዚሁ መንገድ ከሆነ እውነት ነው ደጋፊ ልባል እችላለሁ…ሰፈሬ ጃንሜዳ ነው…ጃንሜዳ መጥቶ የማይሰራ ቡድን የለም…ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ኤልፓ ብቻ ብዙ ቡድኖች ይሠራሉ…በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተደጋጋሚ ይሠራ ስለነበር እነሱን የማየትና የማደንቅ ሁኔታ በጣም ነበር…ደግሞም በዚህ ቡድን ውስጥ የሠፈራችን ልጅ የሆነው አሁን አሜሪካ የሚገኘው ሰብስቤ አሠፋ አለ…የሠፈርህ ልጅ ያለበትን ቡድን የመደገፍ ነገር ይፈጠራል…በእርግጥም በሰዓቱ ከጊዮርጊስ የተሻለ ቡድን የለም…ሠፈራችን ከመስራታቸው አንፃር ከተጫዋቾች ከደጋፊዎች ጋር ሲያዩኝ ወደዚህ ድምዳሜ መጥተዋል… አብዛኞቹ ጓደኞቼ ናቸው…ይሄ ነገርም ትርጉም ያሰጠው ይመስለኛል…ግን ይሄ መሆኑ ችግር አለው ብዬ አላስብም..ምክንያቱም ትልቁ ጥፋትና ኃጢአት የሚሆነው ሙያህንና ድጋፍን ቀላልቅለህ የምትሄድ ህግን በጭፍን ድጋፍ የምታዛባ ከሆነ ብቻ ነው…ምናልባት የእኔ ጎልቶ ታየ ወይም ሰዎች እንደመሳሪያ ተጠቀሙበት እንጂ…ሁሉም የሚደግፈው ወይም የሚያደንቃቸው ተጨዋች አለ…ሳጫወት ያዩም ያላዩም እኔን የጊዮርጊስ ደጋፊ ነው እያለ ያነሳሉ…ግን እዚህ ጋ አንድ ነገር ልጠይቅህ…
ሀትሪክ፡- …ምን….?
ኪነ፡- …ሁሌም ያየኝም…ያላየኝም…ኪነ የቅዱስ ጊዮርጉስ ደጋፊ ነው ይልሃል….ልሁና መደገፍ ምንድነው ክፋቱ…?…እንደዚህ የሚያወሩ ሰዎችን እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃቸው…?…እኔ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አዳልቼ…ወይም…በእኔ የተዛባ ዳኝነት…ቅዱስ ጊዮርጊስ ምን ያገኘው ነገር አለ…?…ከአሉባልታ ወይም የሰውን ስም ከማጥፋት በዘለለ ማነው እንዲህ አድርገሀል ብሎ ማስረጃ የሚያቀርብ ወንድ?…ዳኝነት ከጀመርኩበት እስከአሁን ለጊዮርጊስ ይሄን አድርጓል ብሎ ማስረጃ የሚያቀርብ ካለ እሸልመዋለሁ ብቻ ሣይሆን በይፋም ይቀርታ እጠይቃለሁ…ግን ከወሬ ከአለባሉታ በዘለለ ይሄን የሚያደርግ የለም…፡፡
ሀትሪክ፡- … ያልከውን ይሁንብዬ ልቀበልህ… ግን ኪነ እውነት እንነጋገር ከተባለ…የደጋፊነት ስሜት በውስጥህ ካለ ሙያህን በብቃት እንዳትወጣ አልተጫነህም?
ኪነ፡- …በፍፁም…!…ነገርኩህ እኮ ሙያዬንና ደጋፊን ለይቼ የማይ ሰው ነኝ…ቃል ለገባሁለት፣መሀላ ለፈፅምኩለት ሙያዬ ታማኝ ነኝ…አንድም ጊዜ ጊዮርጊሶች የእኔን ድጋፍ አግኝተው አያውቁም… ደግሞም ዕውነት እንነጋገር ከተባለ ጊዮርጊስ የዳኛ ድጋፍ የሚያስፈልገው ቡድንም አልነበረም… የሚገርምህ ነገር ጊዮርጊሶች ራሳቸው እኔ እንዳጫውታቸው አይፈልጉም…እንደውም ጊዮርጊሶች ምን እንዳሉኝ አንድ እውነት ልንገርህ…“ኪነ ለምን ታጫውተናለህ…?…በቃ አንተ እኛን አታጫውተን… በአንተ በጣም እየተጎዳን ነው…” ነው ሁሉ ብለውኛል…አሸናፊን ታውቃታለህ…?…
ሀትሪክ፡- …አሸናፊ ሲሳይ…የቅዱስ ጊዮርጊሱን አጥቂ ማለትህ ነው…?…
ኪነ፡- …አዎን…!…አሹ አንዴ…ከእርሻ ሰብል ጋር አጫውቼያቸው ሲሸነፉ…በጣም ከመበሳጨቷ የተነሳ ምን እንዳለችኝ ታውቃለህ…?…“…ኪነ…ለምን እኛን ታጫውተናለህ…?…ገና ለገና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነው…ያዳላላቸዋል ይሉኛል እያልክ እኛን በጣም እየበደልከን፣በጣም እየተጫንከን ነው…እባክህ ከቻልክ እኛን አታጫውተን…በመሀል ቤት እኛ እየተጎዳን ነው…ይሄንን እኔ ልበልህ እንጂ…የሁሉም ተጨዋች ሃሣብ ነው…”…ብሎ በምሬት ነግሮኛል…አስበው ከውጪ ደጋፊ ነው ትባላለህ…ከውስጥ ደግሞ ጊዮርጊሶች አታጫውተን ገደልከን እያሉ ያማርሩሃል…በመሀል ቤት ከሁለት ያጣሁበት ሳንድዊች የሆንኩበት ሁኔታ ነው የነበረው…እኔም አሁን ላይ ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስበው…አሸናፊ ሲሳይ… ልክ ነው…ማንነቴን ለማሳየት ስል ጊዮርጊሶችን ጭራሽ የመጫን ሁኔታ ነው የነበረው ብዬ እንዳስብ እያደረገኝ ነው…ዕውነታው ይሄ ነው…ሙያዬንና ድጋፊን ለይቼ የማውቅ ሰው መሆኔን ሰው እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ..አንዴ ቅዱስ ጊዮርጊስና ቡና ሲጫወቱ አሰግድ ተስፋዬ (ነፍሱን ይማረውና) ግብ አስቆጥሮ የሻርክበትን ጨዋታ ብዙ ሰዎች በደጋፊነትህ ያደላህበት ጨዋታ ነው በማለት በማሳያነት ያነሱታል… ይሄንን ትችት ለሚያቀርቡ መልስ አለህ…?
ኪነ፡- …እሱ አጋጣሚ ምን መሰለህ…ቅዱስ ጊዮርጊስና ቡና የሚባሉ ቡድኖችን ብዙ ዳኞች ከሚያጫውቱ ይልቅ ወደ ኋላ ማለትን ይመርጣሉ.. ይሄን ጨዋታ ስትመራ የሚደሰትብህ አታገኝም… በዚህ የተነሣ በዚህ ጨዋታ አንዴ ከተለከፍክ ትጠፋለህ…ብዙ ትልልቅ ዳኞች እነዚህን ቡድኖች በማጫወታቸው ተለክፈው የጠፉ አሉ…አንዴ ታዲያ ምን ይሆናል መሠለህ…ሁለቱን ቡድኖች የሚነጫውት ዳኛ…ቢታስስ…ቢታስስ…ይጠፋል…ሁሉም ምክንያት እየፈጠረ ይሸሻል…በኋላ እኔ ተጠየኩ…ያበጠ ይፈንዳ ብዬ ገባሁበት…ከዚያ በፊት ሁለቱን ቡድኖች በፌስቲቫል ጨዋታ ይመስለኛል አጫውቼያቸው ምንም ችግር አልገጠመኝም…ጨዋታውን በሠላም መርቼ ነው የጨረስኩት…በዚህ ሞራል የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ለመምራት ሜዳ ገባሁ…ፉክክሩ ከባድ ነበር ጊዮርጊስ 3ለ1 በሆነ ውጤት እየመራ ሳለ (ነፍሱን ይማረውና) አሰግድ ተስፋዬ ላይ ፋውል ይሠራበትና ወዲያው ፊሽካ ነፍቼ ቅጣት ምት እሰጣለሁ…አሰግድ ግን ተጨዋቾቹ ፊሽካ ተነፍቷል ብለው በቆሙበት ሰዓት እኔም 9 ከ15 እንዲርቁ እየቆጠርኩ ባለበት ሰዓት በድንገት ይመታና ኳሱ መረብ ውስጥ ያርፋል…በዚህ ጊዜ ቡናዎች ጎል ነው ብለው ስታዲየሙን ቀወጡት…ወዲያው ፊሽካ ነፍቼ አሰግድን ፊሽካ ሳልነፋ ማን ምታ አለህ? ወይ አድቫንቴጅ ነው ብዬ በእጅ ምልክት አላሳየሁህ ብዬ…በድጋሚ ምታ ስለው…እሱም ደጋፊውም ተበሳጩ ሙሉ ስታዲየም ተቀወጠ…ተቃውሞ በእኔ ላይ ተነሣብኝ…ጨዋታውም 3ለ1 በጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ…የሚገርምህ በዚህ ጨወታ ላይ የነበሩ ተጨዋች አሁንም በህይወት አሉ…እነ ደሳለኝ፣ፀጋዬ ባቲ ብርሃኑ ፊየራ…ራሳቸውም የቡና ልጆች ስላሉ ለእውነት ሊመሰክሩ ይችላሉ…አሰግድ ነው የሰውን ስሜት የቀየረው እንጂ እኔን የሚያስወቅስ አይደለም…እንደውም በጨዋታው ወቅት ራሳቸው የቡና ተጨዋች የደጋፊውን ተቃውሞ አይተው ተረጋጋ አይዞህ በማለት ለእኔ ድጋፋቸውን ሲሰጡ ነበር… ተጨዋቾች ቅጣት ነው ብለው በቆሙበት…ምታ ባልተባልክበት ሰዓት መተህ ያገኘኸው ግብ እንዴት ነው የሚፀድቀው…?…በዚህ ሁኔታ የተቆጠረ ግብ ለምን አልፀደቀም…?…ተብሎ የነበረው ተቃውሞ ልነግርህ አልችልም…ከዚያ በኋላ ቡናዎች 3ለ3 አቻ የምንወጣበትን እድል ኪነ አበላሸብን ብለው ወቀሱኝ…አስበኸዋል…?…እንደው የተሻረው አንድ ጎል ይፅደቅ ቢባል እንኳን እንዴት ሆኖ ነው 3ለ3 ጨዋታው ሊያልቅ የሚችለው…?…እንደዚህ አይነት ካልኩሌሽን አለ እንዴ…?…እውነታው ይሄ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …ስለዚህ በዳኝነት ሙያዬ አድልኦ አላደረኩም…ሁሉንም ቡድኖች እኩል ዳኝቻለሁ እያልክ ነው…?
ኪነ፡- …ባለፈው ብዬሃለሁ…በ23 አመት የዳኝነት ህይወቴ አንድም ለፀፀት የሚዳርገኝን ስራ አልሠራሁም..አንዱን ቡድን ከሌላኛው አበላልጬም አላየሁም…ሙያዬንም በክለብ ፍቅርም ይሁን በደጋፊነት ስሜት አሳልፌ አልሰጠሁም…እኔን እኮ ከሀገር አልፎ ለኢንተርናሽናል ደረጃ እንድበቃ ያደረገኝ እኮ አንድ ክለብ ሣይሆን ሁሉም ክለቦች ናቸው…እኔን ወደ ላይ ያወጡኝ፣ከፍ ያደረጉኝ እኮ የቡናም፣ የጊዮርጊስም፣ የኤልፓም፣የጦሩም ደጋፊዎች ናቸው…አበረታተው ያሳደጉኝ…ስሳሳት አርመው… ስበረታ ይበልጥ አጠንክረው…ለትልቅ ደረጃ ያደረሱኝ ጊዮርጊሶችም ቡናዎችም የሁሉም ክለብ ደጋፊዎች ናቸው…በዚህ አጋጣሚ እንደውም ላመሰግናቸው እወዳለሁ…በነገራችን ላይ ኔጌቲቭ የሆነ አስተያየት የሚሰጡ ጥቂቶች ናቸው…እነሱ ደግሞ ብዙኃኑን የቡናም ሆነ የጊዮርጊስና የሌሎችን ክለብ ደጋፊዎች አይወክሉም…ዛሬ ወዳጆቼ የሁሉም ክለብ ደጋፊዎች መሆናቸውም የሚያረጋግጥልህ ይሄንኑ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ ከደጋፊ ስሜት ጋር በተያያዘ ይሁን በሌላ ማረጋገጥ ባልችልም ለረዥም አመት ቅዱስ ጊዮርጊስን የማጫወት እድል አላገኘህም…ለምን እንደሆነ ወደ ኋላ ተመልሰህ ታስታውሰዋለህ…?
ኪነ፡- …እንግዲህ ምክንያቱን የሚያውቁት ውሳኔውን ያሳለፉት ሰዎች ናቸው…ግን በጣም የሚገርምህ ወሬ የሚወራው እኔ ብዙ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዳጫወትኩ…በደጋፊነት እነሱን የጠቀምኩ ያህል ነው… ጥሬ ሀቁ ግን ከዚህ ሀገር እስከምወጣ ድረስ ለአምስት አመት ያህል ቅዱስ ጊዮርጊስን አላጫወትኩም…ወደ አሜሪካ ልሄድ አንድ ሁለት ወር ሲቀረኝ ቅዱስ ጊዮርጊስንና መብራት ኃይልን አንዴ መርቻለሁ እንጂ…ለአምስት አመት የቅዱስ ጊዮርጊስን ጨዋታ አልመራሁም…ይሄን ያህል አመት ሳልመራ ነው ብዙ ሲባል የምትሠማው…ባላጫወትክበት የሚሰነዘሩ ትንንሽ አቅም የሌላቸው አስተያያቶች እንደሆኑም ትረዳለህ…እኛ ሀገር አንዴ ወሬ ከተነዛ መመለሻ የለውም እንጂ…ሙያዬን በደጋፊነት ስሜት የሸጥኩበትን አጋጣሚ አላስታውስም…በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ…ከህሊና ወቀሳም ነፃ ነኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ አሜሪካ የሄድከው በምንድነው?
ኪነ፡- (ኮስተር ቆጣ እንደማለት እያለ) ምን አይነት ጥያቄ ነው? በራሴ ነዋ በማን እሄዳለሁ…
ሀትሪክ፡- … አትቆጣ… ይሄን ጥያቄ ያነሳሁልህ ያለምክንያት አይደለም… ሰዎች በየቦታው የሚያሙህን አንድ የመጨረሻ ጥያቄል ጠይቅህ ፈልጌ ነው… ኪነ ወደ አሜሪካ የሄደው ለጊዮርጊስ ለዋለው ውለታ የክፍያ ያህል ተፈፅሞለት ነው በሚል ስምህ ሲብጠለጠል ስለሰማሁ እሱን እንድታጠራልኝ ፈልጌ ነው…
ኪነ፡- አንተ ራስህን ተራ አሉባልታ ይዘህ መጠየቅ የለብህም… ለአሉባልታና ለተራ ወሬ ምላሽ ባልሰጥ ደስ ይለኝ ነበር… ግን እውነቱን ለመረዳትና ለማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ስል ምላሽ እሰጥሃለሁ… እኔ ወደ አሜሪካ የሄድኩት በማንም ድጋፍ አይደለም…. ሰባራ ሳንቲምም የሰጠኝ የለም… የተለይዩ ሰዎች የአውሮፕላን ትኬት ሳይቀር ሲሸፈንላቸው ኪነ ግን በራሱ ገንዘብ በላቡ ትኬት ቆርጦ ነው ወደ አሜሪካ የሄደው፡፡ አንዳንድ ክፉዎችና ሴይጣን የሰፈረባቸው ሰዎች ግን አንተ በጥያቄ እንዳነሳኸው ውለታ ተውሎልኝ ወደ አሜሪካ እንደሄድኩ አድርገው ሲያወሩ ሰምቼ በጣም አፍሬባቸዋለሁ… ወሬው በፍፁም ውሸት ነው… እኔ ለጊዮርጊስ የዋልኩት ውለታ የለም… ጊዮርጊሶችም ለእኔ የዋሉልኝ ውለታ የለም… ከእነሱ ያገኘሁት ሰባራ ሣንቲም እንደሌለ ይሄንን የተፈበረከ ወሬ የሚያናፍሱ ሰዎች ቢረዱ በጣም ደስ ይለኛል…
ሀትሪክ፡- …ሙሉጌታ ከበደ በቅርቡ ከአሜሪካ እንደመጣ ኢንተርቪው አድርጌው ነበር…የሜዳ ውስጥ ተንኮሌን የሚነቃብኝ ዳኛ ኪነ ብቻ ነው ብሎኝ ነበር…ዕውነት ተንኮሉን ታውቅበት ነበር…?
ኪነ፡- …ሙሌን ጠንቅቄ አውቅዋ ለሁ… ሙሌ የችሎታዋን ያህል የረቀቀች ተንኮለኛም ናት…የሙሌን የተለየ ስለሆነ አነሳነው እንጂ የሁሉንም ተጨዋቾች ባህሪ፣ተንኮላቸውንም ሆነ ችሎታቸውንም ጠንቅቄ አውቃለሁ… ለዚህ የረዳኝ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ጨወታ ባለበት ቀን ሁሉ ስታዲየም እየገባሁ ጨወታ መከታተሌ በጣም ጠቅሞኛል…ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ የሚባል የዳኞች አስተማሪ አለ አንዴ ስልጠና ላይ ምን እንዳለ ታውቃለህ? “ኪነ እናንተን በዳኝነት የሚበልጣችሁ እኮ አንብቦ ወይም የተለየ ትምህርት ተምሮ አይደለም…እናንተን የሚበልጣችሁ ስታዲየም ተገኝቶ ሁሉንም ጨዋታ በመከታተሉ ነው…እዚህ ስታዲየም ለሥራ ጉዳይ ልምጣ…ኪነን አላጣውም…ቁጭ ብሎ ጨዋታ ሲከታተል ነው የማየው…ሁሉንም ጨወታዎች በመከታተሉ በልጧችኋል…እናንተም ከእሱ ተምራችሁ ጨወታ ሳትመርጡ ተከታተሉ…ለዳኝነታችሁ ይጠቅማችኋል” ብሎ በዳኝነት ስልጠና ላይ ምሣሌ አድርጎኝ አስተምሮአቸዋል…እውነትም እንደተባለው ስታዲየም ጨዋታ ይኑር ብቻ ምንም የሚቀረኝ ጨዋታ የለም…ሁሉንም ገብቼ አያለሁ…የዋናውን ተወውና ለምን የ3ተኛና የ2ተኛ ዲቪዚዮን ጨዋታ አይሆንም ገብቼ አያለሁ…ይሄ ነገር በጣም ጠቅሞኛል…ብዙ ዳኞች ጋር ያለው ችግር ጨዋታ የተመደበ ዕለት ካልሆነ ስታዲየም ገብቶ ጨዋታ ያለማየት ችግር አለ…
ሀትሪክ፡- …እኔ የጠየኩህ እኮ ስለ ሙሉጌታ ነው…?
ኪነ፡- …እየመጣውልህ እኮ ነው… የሙሉጌታን ችሎታ ብቻ ሣይሆን ተንኮሉንም የሌሎች ተጨወቾች ባህሪንም ለማወቅ ጨወታ ሳልመርጥ እየገባሁ መመልከቴ በጣም ጠቅሞኛል…ሜዳ ውስጥ ሆነህ ሁሉንም ነገር ለማየት አትችልም..ተመልካች ሆነህ ግን ማን ምን እንደሚሠራ ለማየትና ለማጥናት ይጠቅምሃል…የሙሌንም ተንኮል ስለማውቅ ገና አንድ ነገር ለመስራት ሲያስብ ሙሌ ተጠንቀቅ…አርፈህ ኳስ ብቻ ተጫወት…እምቢ ካልክ አስወጣሃለሁ…ይሄ ህዝብ ቢጮህብኝና ድንጋይ ቢወረውርብኝ አንዴ ነው…ህጉን ከጣስክ አለቅህም መንቅዬ ነው የማስወጣህ ስለው “…አይ ኪነ አንተ ቡዳ ሰው ነህ…አንተ ብቻ ነህ የነቃህብኝ…”…ይለኝ ነበር… የሚገርምህ…ሙሌ ስናገረው…ስቆጣው በጣም ይሰማኝ…በጣምም ያከብረኝ ነበር…ሙሉጌታ በጣም ደጋፊ ስላለው ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው…በዚያ ላይ ሙሌ መች ይሰማል… ከመጀመሪያ ለዳኛ ጆሮስ አለው እንዴ? እኔን ግን እግዚአብሔር ይሰጠው ይሰማኝ ነበር…እንጂ ሙሌ እንኳን ለእኛ ለጎረቤቱ፣የቤተሰቡ ያህል ለሆነ ዳኛ እንኳን የማይመለስ ተጨዋች ነበር….
ሀትሪክ፡- …ለጎረቤቱ፣የቤተሰቡ ያህል ለሆነ ዳኛ የማይመለስ ዳኛ ነው ስትል…?
ኪነ፡- … ሙሉጌታ እኮ ትልቅ ኃይል ያለው…ማንንም የማይሠማ ተጨዋች ነው…መለስ ባህሩ የሚባል ዳኛ ጎረቤቱ ብቻ ሣይሆን የቤተሰቡ ያህል በጣም የሚቀራረቡ ናቸው…አንዴ እሱ እያጫወተው ጉርብትናውንና ቤተሰብነቱን ትቶ ካልተደባደብኩ ያለ ዳኛው ላይ ትልቅ ተቃውሞ ያስነሣ ተጨወች ነው…ያኔ እንደውም እኔ ተቆጥቼዋለሁ…ሙሌ ይሄ ዳኛ እኮ ህጉን ነው የተረጎመው…ቢሳሳት እንኳን እንደዚህ ማድረግ የለብህም…ይሄ ከአንተ የሚጠበቅ አይደለም…ምከንያቱም አንተ እኮ ምሳሌ የምትሆን ተጨዋች ነህ…በዚያ ላይ መለስ ባህሩ እኮ ጎረቤትህ የቤተሰብህ ያህል የሚቀርብህ ሰው ነው…ባለቤትህስ…የእሱ ቤተሰቦችስ ምን ይሉሃል…?…ስለው “ይሁና ታዲያ ምን ላድርግ…?…ለምን የፈለገ አይሆንም…” ሲለኝ አይ ሙሌ ይሄ ከአንተ የማይጠበቅ ነው ስለው…ወዲያው ተመልሶ እሺ ብሎ ይቀበለኛል…ልልህ የፈለኩት…ሙሌ ለተጫዋች ብቻ ሣይሆን ለዳኞችም አስቸጋሪ ነው…እኔ ግን በተለይ ተንኮሉን እነቃበት ነበር….
ሀትሪክ፡- …የዳኝነት ዘመንህ ምርጡ ተጨዋች ማነው…?…ብልህ ማንን ታስቀድማለህ…?
ኪነ፡- …ከሙሉጌታ ከበደ በፊት ማንንም አልጠራም…በእኔ የዳኝነት ዘመን ያየሁት ምርጡ ተጨዋች ሙሉጌታ ከበደ ነው…ግን ከሙሌ ውጪ በየቦታው ለማበላለጥ የሚከብዱህ በጣም ብዙ ምርጥ ተጨዋቾች አሉ…በየቦታው አስቀምጥ ካልከኝ አሰግድ ተስፋዬ፣ኤልያስ ጁኸር፣አሸናፊ ሲሳይ፣ሙሉጌታ ወልደየስ፣ሚሊዮን በጋሻው…ኧረ ማንን ጠርቼ ማንን ልተው…?…የምርጦች ስብስብ ነው የነበረው… አማካዮች ጋር ብትመጣ ጌታቸው ካሳ /ቡቡ/፣ካሳዬ አራጌ፣አሸናፊ በጋሻው፣አንዋር ያሲን (ትልቁ)፣ሰለሞን (ቸርኬ)፣ከተከላካዮች አንዋር ሲራጅ (ትንሿ)፣አፈወርቅ ኪሮስ ከግብ ጠባቂ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ፣ፊቱሼ፣ይልማ ከበደ (ጃሬ)፣ቅጣው፣ቤተም፣አሊ ረዲ…ኧረ ስንቱን ልጥራ…?…በየቦታው በጣም ምርጥ ምርጥ…የማደነቃቸው ተጨዋች ነበሩ…
ሀትሪክ፡- …ስለበረኞች ስታነሣ በአሁን ሰዓት የሀገሪቱ ሊግ በውጪ በረኞች መጥለቅለቁን እንዴት ታየዋለህ…በዚያን ጊዜ ከነበሩት ጋር አነፃፅረህ አውራኝ እስቲ… ?
ኪነ፡- …ይሄ ጥያቄ እንኳን አነሣኸው…ይቅርታ አድርግልኝና ያኔ እኮ ለብ/ቡድን 3 በረኛ ለመምረጥ ትቸገራለህ…ሁሉም በጣም ጎበዞችና ምርጦች ከመሆናቸው የተነሣ አንዱን ከአንዱ አበላልጦ ለመምረጥ ፈተና ነበር ለአሰልጣኞች…አሁን አንድ በረኛ መምረጥ ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ነገር አለ እንዴ?የለም…አሁን እኮ እግር ኳሱ ከውጪ ሀገር በመጡ በረኞች ተጥለቅልቋል…በዚህም የሀገር ውስጥ በረኞች ተሸፍነዋል…የተሻሉ ትልቅ ልዩነት የሚፈጥሩ ቢሆን ከእነሱ የሚያዩነት ነገር አለ ልምድ ያገኛሉ ብለህ ትቀበለዋለህ…ብዙም ልዩነት የሌላቸው እንደውም ካሉት በጣም ያነሱ በረኞች ክለቦችን አጥለቅልቀዋል..ይሄ ነገር ሀገሪቱን በረኛ አልባ እንዳያደርጋት እሰጋለሁ…ወይ የተሻለ ነገር አልቀሰሙ…እንዲሁ በከንቱ ከእነሱ በማይሻሉ በረኞች የጨዋታ ዘመናቸው እየተቃጠለ ነው… ኢኮኖሚውም አለአግባብ እየፈሰሰ ነው…ችግሩም ብ/ቡድኑ ላይም እየተንፀባረቀ ነው…በዚህ ጉዳይ ላይ ፌዴሬሽኑ ለምን እንደተኛ አልገባኝም…ከውጪ በሚመጡ በረኞች ጉዳይ ላይ አንድ ነገር ማድረግ አለበት…ላለመውረድ የሚጫወት…ታች ዲቪዚዮን ያለ ቡድን…የውጪ በረኛ ይዞ የታዳጊዎችን እድል ሲነጥቅ እያየን ዝም ማለት ተባባሪ መሆንም ነውና ከወዲሁ ቢታሰብበት እላለሁ…
ሀትሪክ፡- …የተለየ ቦታና አድናቆት የምትሰጠው አሰልጣኝስ…?
ኪነ፡- …መንግሥቱ ወርቁን ነዋ…!…ኢንስራክተር መንግሥቱ ወርቁ /ነፍሱን ይረውና/ የእኔ ምርጡ አሰልጣኝ እሱ ነው…መንግሥቱን አስበልጬ አነሳውልህ እንጂ ከእሱ ውጪ ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካም፣ኢንስትራክትር ሰውነት ቢሻው፣ አስራት ኃይሌም፣ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱም የሀገሪቱ ምርጥ አሰልጣኞች ናቸው…የአሁኑ የብ/ቡድኑን አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ሲያሰለጥን በቅርበት ባለየውም ካለው ውጤትና ካየነው ቡድን አንፃር ጥሩ አሰልጣኝ ይመስለኛል…
ሀትሪክ፡- …ኢትዮጵያን በኢንተርናሽናል መድረክ ስሟን ካስጠሩት ዳኞት መካከል አንዱ አንተ ነህ… እስቲ እሱን አጋጣሚ አስታውሰኝ…?
ኪነ፡- …ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆንኩት በአጋጣሚ 4 ኢንተርናሽናል ዳኞች ታገዱ…መደረግ የሌለበት ነገር ነው የተደረገው…እነ አለም አሰፋ፣ይሸበሩ ብሩን የመሳሰሉ ዳኞች ሲታገዱ እኛ የተሻልን ዳኞች ስለነበርን ውድድር ውስጥ ገባን…ተወዳድረን አለፈን…በዚህ አጋጣሚ ነው ኢንተርናሽናል የሆነው እን ጂ…ይሄን እድል ለማግኘት ብዙ ጊዜ ይወስድብን ነበር…፡፡
ሀትሪክ፡-ብዙዎች በአፍሪካ የውድድር መድረክ የፍፃሜ ጨዋታ የመራው በአምላክ እንደሆነ ነው የሚውቁት አንተስ ይሄን እድል አግኝቷል…?
ኪነ፡- …በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና የአንጎላና የቱኒዚያ ክለቦች የፍፃሜ የመልስ ጨዋታ (Second Leg) መርቻለሁ…ከዚህ ሌላ የተለያዩ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ትልልቅ ጨዋታዎችን እንደዛው…፡፡

ሀትሪክ፡-የአንጎላና የቱኒዚያ ክለቦችን ጨዋታ ስታነሣ አንድ ነገር ትዝ አለኝ…በዚህ ጨዋታ የተነሣ ከኢንተርናሸናል የውድድር መድረክ ታግደህ ነበር ልበል…?
ኪነ፡- …እሱ የሚገርም አጋጣሚ ነው…እኔን ለካፍ ከሶ ያሳገደኝን የቱኒዚያውን ክለብ ሰውዬ ከዚህ በፊት ከኡጋንዳ ክለብ ጋር ተገናኝተው 3ለ1 በሆነ ውጠት ሲያሸንፉ እኔ ነኝ ያጫወትኳቸው…ይሄ የከሰሰኝ ግለሰብ ታዲያ ከጨዋታው በኋላ በጣም በጣም ነው ያደነቀኝ…እንደውም ምን እንዳለኝ ታውቃለህ…“ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ እንደ አንተ አይነት ዳኝ ሣይ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ይሄንን ስልህ ሰሜን አፍሪካዎቹ የተሻሉ ናቸው ብዬ አይደለም…በጣም ጎበዝ ዳኛ ነህ…በዚህ ቀጥል…” አለኝ…እንግዲህ ይሄ ሰውዬ እንዲህ ብሎ ካበረታታኝ ከአመት በኋላ ነው ከሶ ያስቀጣኝ…፡፡
ሀትሪክ፡- …በዚህ ደረጃ ካሞገሰህ ለምን አስቀጣህ…?…ነው ወይስ ሌላ ችግር ነበር…?
ኪነ፡- …ሌላ ምንም ችግር የለም…የእሱ ቡድን ላይ ፔናሊቲ ሰጠሁ…ፔናቲው ግን አልገባም…ተሳተ… ቡድኑም 3ለ1 አሸንፎ ወጣ…ዋንጫውም ወሰዱ…የሚፈልጉትን አሳክተው እኔን ከመክሰስ ወደ ኋላ አላሉም…ሰውዬው ካፍ ውስጥ ተሰሚነት አለው…ያኔ ኮሚሽነሩ ፋራህ አዶ (ሶማሊያዊ) ነበር…የካፍም ምክትል ፕሬዚዳንት ነበር…ጫናዎት ሲበዙበት…ድፍን ሁለት አመት አከናነበኝ…ተቀጣሁ… ?
ሀትሪክ፡- …ሁለት አመት ሙሉ ከኢንተርናሽናል ጨዋታ ውጪ ሆንክ ማለት ነው…?
ኪነ፡- በእርግጥ ሁለት ዓመት ሙሉ አልቆየሁም… አንድ ዓመት ከስድስት ወር አካባቢ ከቆየሁ በኋላ ነው የተመለስኩት… ወደ ኢንተርናሽናል መድረክ ለመመለስ እድሜዬም ይፈቅድ ስለነበር ከዓመት ከስድስድት ወር ቅጣት በኋላ ተመልሻለሁ…
ሀትሪክ፡- …ቅጣቱ ተነሳልህ ማለት ነው…?
ኪነ፡- …ቅጣቴ እንዲነሣልኝ በተደጋጋሚ በወቅቱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ኢንጂኒየር ግዛውን የጽ/ቤት ኃላፊውን አቶ ይስሀቅ ታፈረን እባካችሁ ካፍን ጠይቁልኝ እያልኩ እወተውታቸው ነበር…እነሱም “እየሞከርን ነው እባክህ ታገሰን” እያሉ ቀን ቀንን እየወለደ ሄደ…በዚህ አጋጣሚ የቅዱስ ጊዮርጊሱን አቶ አብነት ገ/መስቀልን አገኘውና አቶ አብነት ሀገሬን ወክዬ ስሟን እንዳላስጠራ በተቀነባበረ መንገድ አገዱኝ…የታገድኩት እንኳን ሁለት አመት ሁለት ወር በማያስቀጣ ጉዳይ ነው…ስለዚህ እባክህ ለካፍ ሰዎች ንገርልኝ አልኩት…ለአቶ አብነት ይሄን ያልኩት ያኔ የአፍሪካ የወጣቶች ሻምፒዮና አዲስ አበባ ላይ ይካሄድ ስለነበር ከፕሬዚዳንቱ ኢሳ ሃያቱም ከምክትሉ ፋራህ አዶ ጋር ይገናኙ ስለነበር ነው… አቶ አብነትም …“…እንዴ ይሄ እኮ የግለሰብ ጉዳይ ሣይሆን የሀገር ጉዳይ ነው…የአንተ መቀጣት የሀገር መቀጣት ነው…ኢትዮጵያ በአፍሪካ መድረክ ወኪል ማጣት የለባትም…ስለዚህ ለእኔ ተወው…እኔ አነጋግራቸዋለሁ…”…አለ…እንዳለውም ፕሬዚዳንቱንና ምክትሉንም አነጋገራቸው፤“…ሀገራችን አላአግባብ ነው የተቀጣችው…ይሄ ዳኛ ከተጣለበት ቅጣት ከግማሽ በላይ እንደውም ከአንድ አመት ከስድስት ወር በላይ ጨርሷልና ልታነሱላት ይገባል…”…ብሎ ተሟገታቸው…ዋናውም…ምክትሉም “እሺ ተነጋገረን እናነሳለታለን…ይሄን ውድድር ጨርሰን ወደ ካፍ ስንመለስ ውሣኔውን እንልክለታለን አሉት…ባሉት መሠረት በሶስተኛው ቀን እገዳው መነሣቱን የሚገልፅ ደብዳቤ ከካፍ ተላከልኝ…ቅጣቱ ተነሣ…ወዲያው ወደ ኢንተርናሽናል መድረክ ተመለስኩ…በዚህ አጋጣሚ…
ሀትሪክ፡- …በዚህ አጋጣሚ ምን…?
ኪነ፡- …በዚህ አጋጣሚ የሰውን ክሬዲት ማስቀመጥ ስላለብኝ ነው ይሄን የማነሳው…አቶ አብነት ገ/መስቀልን ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ…አቶ አብነት ጉዳዩ የአንድ የኪነ ጉዳይ ነው ሣይል…የተቀጣው ኪነ ሳይሆን ሀገር ናት…ብሎ ትልቁን የሀገር ምስል ተመልክቶ…ቅጣቱ እንዲነሣ ስለታገለልኝ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እፈልጋለሁ…የአኔ ቅጣት ሲነሣ ወደ መድረኩ የተመለሰችው ሀገራችን ናት ኢንተርናሽናል…አቶ አብነት ሀገር ማዕከል አድርጎ ባደረገው ጥረት ወደ ኢንተርናሽናል መመለስ ችያለሁ፤አቶ አብነት ከእግር ኳሱ ምንም ሳይጠቀም ለእግር ኳሱ፣ለሙያተኞች የሚለፋ የሚደክም ሰው በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል፡፡
ሀትሪክ፡- …ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግኜህ ከመለቴ በፊት ቀረ የምትለው ነገር ካለ…?
ኪነ፡-…ምናልባት ይሄን አጋጣሚ ተጠቅሜ ብናገር ደስ የሚለኝ ስለጋዜጠኞች ነው…ብዙ ጊዜ ስጠየቅ ስለጋዜጠኞች ተጠይቄ አላውቅም…አሁን ግን ባልጠየቅም እናንተን በተለይ ከድሮ ጀምሮ በህትመት ሚዲያ ላላችሁትና ለእግር ኳሱ የለፋችሁትን ጋዜጠኞች አጋጣሚውን ተጠቅሜ ባመሰግን ደስ ይለኛል…ከድሮ ጀምሮ በጋዜጦች የፖለቲካ ጋዜጣ ላይ ሳይቀር ሃሣባችንን እንስጥ ነበር…በህትመት ሚዲያ ላይ የተሰማራችሁትን በህይወት ያሉትንም የሌሉትንም ከፍ ማድረግ እፈልጋለሁ…አቶ አበበ፣ ወንድወሰን፣ኤፍሬም፣ጋሽ ከበደ መንግሥቱ፣ታሪኬ ቀጭኔ፣ጥሩነህ ካሳ፣መላኩ ወ/ሰንበት፣መሸሻ ወልዴ፣ ገነነ መኩሪያ(ሊብሮ)፣አንተ ራስህን…አሁን ላለው ስፖርትም ሆነ ሚዲያና ጋዜጠኞች መሠረት የጣላችሁ፣በር የከፈታችሁ ናችሁና ልትመሰገኑ ይገባል…ውለታችሁም ሊዘነጋ አይገባም…በተረፈ ከረዥም አመት በኋላ ከአንባቢዎች ጋር እንድገናኝ ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ በድጋሚ ሀትሪኮችን አመሰግናለሁ፡፡
ክፍል አንድን ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ 👇
ኢትዮጵያዊው ኮሊና “በ23 ዓመታት የዳኝነት ሕይወቴ አንድም ለፀፀት የሚዳርገኝ ስራ አልሰራሁም” ኢንተርናሽናል አርቢትር ኪነ ጥበቡ ከአሜሪካ መልስ
አስተያየት ይስጡ