“አዳማ ትልቅ ቡድን ነው፤ ድሉ እና ቡድኔን የምታደግበት ጎል ማስቆጠሬም ይቀጥላል”አብዲሳ ጀማል /አዳማ ከተማ/

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከተማ በአብዲሳ ጀማል ሶስት ግቦች ሐዋሳ ከተማን 3-1 በማሽነፍ ጣፋጭ ድል አስመዝግቧል። የአዳማ ከተማውን አጥቂና የሻሸመኔውን ተወላጅ ስለ ዛሬ ጨዋታ ስለ ድላቸው እና ሀትሪክ ስለመስራቱ የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጠይቆት ምላሽን ሰጥቷል።

ስለ ዛሬ ጨዋታና ድላቸው

“ከሐዋሳ ከተማ ጋር የነበረንን ጨዋታ አስቀድመን ብዙ ነጥቦችን ጥለን ስለነበር እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ነበርን። ምክንያቱም እነሱ የእኛን ውጤት ማጣት ተከትለው አውርደውን ነበር የመጡት። ያን እናውቅ ነበር። አሰልጣኛችን እነሱ አንድ ሁለት በሚመጡብን ሰዓት በመልሶ ማጥቃት መጫወት እንዳለብን ነገረንና አሸነፍን። የዛሬው ድል ለእኛ በጣም ጣፋጭ እና የሚገባን ነበር። ውጤቱም የሚያስፈልገን ስለነበር ተደስተንበታል”።

ድሉ ይቀጥል እንደሆነ

“በሚገባ ነዋ! ምክንያቱም እስካሁን ባደረግናቸው ጨዋታዎች ነጥብ የጣልነው ከተጋጣሚዎቻችን አንሰን አልነበረም። በተለይ ከሀዲያ ሆሳዕና እና ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረግናቸውን ጨዋታዎች በአጨራረስ ችግር ውጤት አጣንበት እንጂ እነሱንም ድል ማድረግ እንችል ነበር። አሁን ግን ችግራችንን በመነጋገር ስለቀረፍነው በቀጣይ ጨዋታዎቻችን እንደ ዛሬው ሁሉ ድላችን የሚቀጥል ነው የሚሆነው”።

3 ግቦችን አስቆጥሮ ሀትሪክ ስለመስራቱ

“ይሄን ያህል ግብ አስቆጥራለው ባልልም ግብ እንደማስቆጥር ግን አውቅ ነበር። ጎል ማግባት ደግሞ ከእኔ የሚጠበቅ ነው። አዳማን ስኬታማ ለማድረግም ትልቅ ሀላፊነት አለብኝ። ለዛም ነው ጎሎችን ያስቆጠርኩት 4ኛው ሀትሪክ ሰሪ ስለሆንኩም በጣም ተደስቻለሁ”።

ስለ ጠንካራ እና ደካማ ጎናቸው

“ቡድናችን ከደካማ ጎን ይልቅ ብዙ ጠንካራ ጎኖች ነው ያሉት። ድክመት ብዬ የማስበው ደግሞ የዝግጅት ጊዜ ስራን በደንብ ስላልሰራን ልንቀናጅ አለመቻላችን እና ጎል ሲገባብን የመውረድ ነገር ነበረብን። አሁን ግን ወደ መቀናጀቱ እየመጣን ይገኛል”።

ስለ አዳማ ከተማ

“ቡድናችን የሊጉ ትልቅ ቡድንና በቅዱስ ጊዮርጊስ ደረጃም የሚታወቅ ነው። ከዚህ በፊት የነበረንን ጥንካሬያችንንም እናስቀጥላለን”።

አዳማ ከተማን ወራጅነት ያሰጋዋል ስለመባሉ

“አዳማ ትልቅ ቡድን እና ለውጥ የሚያመጣ ስለሆነ በፍፁም የሚያሰጋን ነገር ምንም የለም። ሊጉ በርካታ ጨዋታዎች ስላሉት ከዛ ይልቅ ጥሩ ውጤት እንደምናመጣም ነው የማውቀው”።

በመጨረሻ

“በቤት ኪንግ ለክለቤ ጎሎችን እያስቆጠርኩ ነው። ወደ ኮከብ ግብ አግቢዎቹ ፉክክር ውስጥም መቀላቀል እና ቡድኔን መታደግም ትልቅ እልም አለኝ ይህን ካልኩ ለዛሬ እዚህ ደረጃ መድረሴ እኔን ከፕሮጀክት ተጨዋችነት በማምጣት ለአርሲ ነገሌ ቡድን በቋሚ ተጨዋችነት ያጫወተኝን አሰልጣኜን ራመቶን እንደዚሁም ብዙ ነገሮችን ያደረጉልኝን ቤተሰቦቼን እና ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ”።

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor