ክፍል አንድ
በይስሐቅ በላይ
ኢትዮጵያዊው ኮሊና
“በ23 ዓመታት የዳኝነት ሕይወቴ አንድም ለፀፀት የሚዳርገኝ ስራ አልሰራሁም”
ኢንተርናሽናል አርቢትር ኪነ ጥበቡ ከአሜሪካ መልስ
- ማሰታውቂያ -
ይህንን ከላይ ያለውን ምስል ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል? አይ የሰው መመሳሰል ብለው ያልፉታል? ወይስ የዓለም እግር ኳስን የማይዘነጋው አይነ ትልልቁና ፀጉር አልባው ጣሊያናዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ኮሊና አይንዎ ላይ ድቅን ይላል፤ እንዳዛ ብለው ካሰቡ በእርግጥ አልተሳሳቱም፤ የዛሬው እንግዳችን ኢንተርናሽናል አርቢትር ኪነ ጥበቡና ጣሊያናዊው ኮሊና የመልክም፣ የሙያም መመሳሰል አላቸውና፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የዳኝነት ጥቁር ልብሱን ለብሶ፣ ፊሽካውን አፉ ላይ አድርጎ፣ ቀይ እና ቢጫ ካርዱን ደረት ኪሱ ከቶ 23 አመታትን በሙያው በማገልገል ያሳለፈው ኢንተርናሽናል አርቢትር ኪነ ጥበቡ ላለፉት 15 አመታት ኑሮውን ካደረገባት በስልጣኔ ጣሪያ ከነካችው ሀገረ አሜሪካ ለእረፍት ወደ ትውልድ ሀገሩ መጥቷል፤ በሚሰጣቸው ቆራጥ የዳኝነት ውሣኔዎችና የህግ አተገባበር ከአገር አልፎ በአፍሪካ ደረጃ አንቱታን ያተረፈለት ቁመተ መለሎውን የመሀል ዳኛ ኢንተርናሸናል አርቢትር ኪነ ጥበቡን የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ 23 አመታትን በሃሳብ ፈረስ ወደ ኋላ አስጋልቦት ታሪኩን እንዲያጫውተው ተናግሮ አናግሮት የመጀመሪያውን ክፍል ከዚህ በታች ባለው መልኩ አጠናክሮ አቅርቦታል፡፡ ሁለተኛውን ክፍል ለሳምንት ለማቅረብ ቀጠሮ እንዲያዝለት ከወዲሁ አጥብቆ የሚጠይቀው ጋዜጠኛው ከኢንተርናሽናል ዳኛው ጋር ያላነሳው ነገር የለምና አብራችሁን ቆዩ፡፡
ሀትሪክ፡- ብዙዎች አንተን ኮሊና ከሚባለው ዳኛ ጋር ያመሳስሉሃል፤ እንደውም ኪነ ከማለት ይልቅ የቅፅል ስምህ ያህል በጣሊያናዊው ታዋቂ ዳኛ ስም የሚጠሩህም አሉ…ይህን ታውቃለህ…?
ኪነ፡- …ቅፅል ስሜ ኮሊና መሆኑን አላውቅም…ገና ከአንተ መስማቴ ነው…እኔ ሳላውቅ ቅፅል ስሙ ወጥቶልኝ ከሆነም በጣም የማከብረውና በችሎታው ትልቅ ቦታ በምሰጠው ኢንተርናሽናል ዳኛ ስም በመጠራቴ አልከፋም…ደስ ይለኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- …አንተ በግልህ ኮሊናን እንዴት ትገልፀዋለህ…?…ከአንተ ጋር ስለመመሳሰሉስ ምን ትላለህ…?…
ኪነ፡- …እኔ እስከአሁን በአለም ላይ ካየኋቸው ዳኞች የመጀመሪያ ቦታ የምሰጠው ዳኛ ጣሊያናዊውን ኮሊናን ነው…የአለም እግር ኳስ በታሪኩ ካገኛቸው ትልቅ ስራ ከሰሩ ዳኞች አንዱ ነው…ለዚህም ነው ዛሬም ድረስ ዳኝነትን አቁሞም የሚከበረውና የሚወደደው፤ከእኔ ጋር መነፃፀሩን በተመለከተ እንዳልኩህ ነው…ከተከበረ ዳኛ ጋር በመነፃፀሬ…በእሱ ስም መጠራቴ…የኩራት ስሜት ይፈጥርልኛል፤ለሀገሬ ኮሊና መሆኔ…በዛ ደረጃም መታሰቤም እንደዛው…የመልክ መመሳሰላችን፣የፀጉር ስታይላችን (መላጣችን)፣ ሙያችን አመሳስሎን ይሄን ስያሜ እንዲሰጠኝ ያደረገ ነው ብዬ የማስበው፡፡
ሀትሪክ፡- …እንኳን ደህና መጣህ ሳልልህ ወደ ሌላ ጥያቄ በመምጣቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ…ዘገየህ ብለህ ካልተቀየምከኝ አሁንም ጥያቄዬን የምጀምረው…እንኳን ደህና መጣህ በማለት ነው…?
ኪነ፡- …ችግር የለውም አልዘገየኸም…እናንተም እንኳን ደህና ቆያችሁኝ…በጣም ከናፈኳቸው፣ ከሚወዱኝ፣ከሚያደንቁኝና የአዲሱ ትውልድ አካል ከሆነው የስፖርት ቤተሰብ ጋር በሀትሪክ ድልድይነት ከረጅም ዓመት በኋላ በህትመት ሚዲያ የምገናኝበትን ዕድል ስለሰጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ጠቅልለህ ወደ አሜሪካ ከሄድክ ስንተ ዓመት… ግን…ቆይ…ቆይ…አሁንም በጣም ይቅርታ… ከዚህ ጥያቄዬ በፊት…የተገናኝንበት ቀን የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ዕለት በመሆኑ እንኳን ለብርሃን ጥምቀቱ አደረሰህ የሚለውን ላስቀድም…?…
ኪነ፡-…በጣም አመሰግናለሁ…እንኳን አብሮ አደረሰን…ይህቺ ቀን ለእኔ በጣም የተለየችና ታሪካዊ ቀን ናት…ራሴንም እንደ ዕድለኛ ነው የምቆጥረው…ምክንያቱም የጥምቀትን በዓል በሀገሬ ከወገኔ ከሕዝቤ ጋር ሆኜ በአንድነት ያከበርኩት ታቦት የመሸኘት ዕድል ያገኘሁት ከ15 ዓመት በኋላ ነው…ላለፉት 15 ዓመታት በተለያየ ምክንያት ይሄንን እድል ተነፍጌ ነበር…አሁን እግዝአብሔር ለዚህ ክብር አብቅቶኛልና በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ጠቅልለህ ወደ አሜሪካ ከሄድክ እንደዋዛ ስንት ዓመት አስቆጠርክ…?
ኪነ፡- …በጣም ረጅም ጊዜ ነው…15 ዓመት ሞልቶኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- … ከዚህ በፊት መምጣትህን የሰማሁ ይመስለኛል…ነው አሁን ስትመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው…?
ኪነ፡-…ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ብቅ ብዬ ነበር…የሀገር ናፍቆት፣የሕዝቡ ፍቅር መቼ ያስቀምጥሀል… ተነስና ወደ ሀገርህ ብረር….ብረር…ይልሀል…፤ወደዚህ ስመጣ ብዙም አልቆይም ብዬ ነበር…አሁን ግን ከሁለት ወር በላይ ሆኖኛል…ጭራሽ ይሄ አልበቃ ብሎኝ ቆይታዬን አራዝሜያለሁ…
ሀትሪክ፡- ብዙዎቻችን በልጅነታችን ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ? ስንባል…ፓይለት፣ኢንጂኒየር፣ ዶክተር ምናምን እያልን ነው ያደግነው…ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን የበቃው ኪነ…ዳኛ የሆነው ዳኛ መሆንን ተመኝቶ ነው…?
ኪነ፡- …እውነት ለመናገር ዳኛ የመሆን ምኞቱ በውስጤ አልነበረም…ከዚህ ይልቅ ችግር ወይም አጋጣሚ ነው ወደዚህ ሙያ ያመጣኝ ብል ይቀለኛል…እግር ኳስ በጣም እወድ ነበር…ስታዲየም ገብቼ ማየት በጣም ፍላጎት ቢኖረኝም…በምን ልግባ…?…በገንዘብ እንዳልገባ ገንዘብ የለኝም…በዚህን ጊዜ ዳኛ መሆን የነፃ መግቢያ ያሰጣል የሚባል ነገር ሰማሁና ለመግቢያው ስል የዳኝነት ኮርስ ለመስጠት ምዝገባ አለ ሲባል ተመዘገብኩ…ገባሁበት…ለስታዲየም የነፃ መግቢያ ስል የገባሁበት ዳኝነት እየዋለ እያደረ በደም ስሬ ሳይቀር እየገባ መጣ…እየወደደኩትም መጣሁ፤በፍቅር ተሰለፍን ቀጠልንበት፤በመጨረሻም ትልቋን ሀገር የመወከል፣ስሟን የማስጠራት ዕድል ፈጠረልኝ…ለእውናም፣ለክብርም በቃሁበት…
ሀትሪክ፡- …ብዙ ተጨዋቾች ሳድግ ሮናልዶን፣ሜሲን፣ ሩኒን ወይም ሮናልዲኒሆ ጎችን እሆናለሁ… እያሉ ይመኛሉ…ኪነስ ወደ ዳኝነቱ ከገባ በኋላ ማንን እንደ ሮል ሞዴል እያየ እየተመኘ ነው ያደገው…?
ኪነ፡- የዳኝነት ምስጢሩ ከገባኝና እየወደድኩት ከመጣሁ በኋላ በአለም እግር ኳስ ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን የመከተልና እንደ እነሱ ለመሆን የመመኘት ነገር በውስጤ እየተፈጠረ መጣ…እንደ ጣሊያናዊው ኮሊና አይነት በዓለም የታወኩና የተወደድኩ ዳኛ ብሆን ብዬ እስከመመኘት ደርሻለሁ…ለካስ ከአፍሪካ ተነስቶ የአለም ዋንጫን የፍፃሜ ጨዋታ መዳኘትም ይቻላል? የሚል ትልቅ ተነሳሽነት በውስጤ እንዲፈጠር ያደረገው ፈረንሳይና ብራዚልን በአለም ዋንጫ የመራው አፍሪካዊው ….ን ለመሆንም ተመኝቼ ነበር…ከዚህ ዳኛ ጋር አፍሪካ ዋንጫ ላይ አብረን ስለነበርን በጣም ያበረታታኝ…“ከበረታህ አንተም አለም ዋንጫ ድረስ መግባትት ችላለህ፤ወደዛ ለመግባት ሩቅ አይደለም…አሁን እኛ እየወጣን ነው…የምትተኩን እናንተ ናችሁ” ይለኝ ነበር…የእሱ ተፅዕኖም በዳኝነት ህይወቴ ላይ ቀላል አልነበረም…
ሀትሪክ፡- …እስከአሁን የውጪዎቹን ነው የጠራኸው…ይሄ ሠውዬ የሀገር ውስጥ ሞዴል የለውም እንዴ? ተብሎ እንዲታሰብ አያደርግም ትለለህ…?
ኪነ፡- …ከሀገር ውስጥም በጣም ብዙ ጎበዝ…ጎበዝ ዳኞች ነበሩ…ከሁሉም ግን እንደ እሱ ብሆን ብዬ የተመኘሁት በሚሰጠው ዳኝነት መንፈሳዊ ቅናት ሲያሳድርብኝ የነበረው ሠለሞን አለምሰገድ የተባለው ዳኛ ነው…ሠለሞን በተለያየ ምክንያት ብዙ አልሄደበትም እንጂ ዳኝነት የሚፈልገው ቆራጥነትን፣ ድፍረትን፣እውቀትን ከተሟላ ተክለ ሰውነት ጋር ያለስስት የተሰጠው ለዳኝነት የተፈጠረ ሰው ነበር… ሰለሞን የእኔ ባቼ ነው…ግን ተሰጥኦው እንድትመኘው ሞዴል እንድታደርገው ያስገድድሃል…
ሀትሪክ፡- … ስለ ሰለሞን አለምሰገድ ብቃት እኔም አንደኛው ምስክር ነኝ…ብዙ ርቀት ያለመጓዙን ምክንያት ምንድነው ትላለህ….?
ኪነ፡- …ብዙ ዳኞችን እየበላ የሚያስቀረው ይሄ የፈረደበት የቡናና የቅ/ጊዮርጊስ ጨዋታ ነው…ሰለሞንንም ለክፎ ከመንገድ ያስቀረው ይሄ ጨዋታ ይመስለኛል በእኔ የግል ትዝብት…ሠለሞን ትልቅ የዳኝነት ልብ ያለው ዳኛ ነበር…በችሎታው ላይ ማንም ጥያቄ አያነሳበትም ምንአልባት የኩፐር ቴስትን ጉዳይ እንደ ችግር ካላነሳህበት በስተቀር ምንም የማታወጣለት ዳኛ ነው…እሱ በየሣምንቱ በሚሰጣቸው ዳኝነቶች እየተጨበጨበለት ነበር የሚወጣው…ያ ነገር በውስጤ መንፈሳዊ ቅናትን ፈጥሮብኝ እንደነበር አስታውለሁ…ሰለሞን መቻልንና ፖሊስን ሳይቀር በብቃት መርቶ የሚወጣ ዳኛ ነው…በዚህም በጣም አደንቀው…እንደ ሞዴልም ሳየው የነበረ ዳኛ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- …ስለ ሰለሞን ስታነሣ አንድ ነገር ትዝ አለኝ…በእናንተ ዘመን የነበሩት ዳኞች ከዳኝነት ብቃታቸው ሌላ በተክለ ሰውታቸው፣በተለየ ፎርማቸው፣የፊሽካ አነፋፋቸው፣በስታይላቸው የተለዩ የጨወታው ተጨማሪ ድምቀቶች ነበሩ…አንተ፣ሰለሞን አለምሰገድ፣ አለም አሰፋ፣ተድላ(ነፍሱን ይማረውና)፣በቀለ ኪዳኔ…የመሳሰሉት በዚህ ይጠቀሳሉ በዚህ ላይ ምን ትላለህ…?
ኪነ፡- …በነገራችን ላይ አንድ ዳኛ ዳኛ የሚባለው ጥቁር ለብሶ ሜዳ ስለገባና ፊሽካ ስለነፋ ብቻ አይደለም…ከችሎታህ ባልተናነሰ ፎርምና ስታይልም…ጨዋታ ማክበርም ያስፈልጋል…እንዳልከው ሁላችንም በጣም ረዣዥሞች ነን…የየራሳችን የጨዋታ አመራር፣የውሣኔ አሰጣጥና፣የፊሽካ አነፋፍ ስታይል ሁሉ አለን…ተመልካች ተጨዋች ለማየት እንደሚመጣው ሁሉ የዳኞችን ስታይልም ለማየት የሚመጣበት ጊዜ ነበር…ተፈጥሮ ያለስስት ሁሉን ነገር ሰጥታን ነበር…በዚያን ጊዜ ዳኛ አንዴ የወጣበት የፈላበት ጊዜ ነበር…በዚያን ጊዜ ለዳኞች ትንሽ ከፈት ከፈት ብሎ ነበር…ኢንተርናሽናል ዳኞች ታግደው ነበር…በዚያ አጋጣሚ ነው ሾልከን የወጣነው…ይቅርታ አድርግልኝና በአሁን ዘመን ያሉትን ዳኞች ስመለከት ቁመትም ሠውነትም ያለው ዳኛ ብዙም አላጋጠመኝም…በአምላክ ተሰማ ይመስለኛል ረዘም ያለ ቁመና ያለው ዳኛው…ተጨዋቾቹንም ሳያቸው በጣም ደቃቃ ሆነውብኛል ብዙዎቹ…በእኛ ጊዜ ተጨዋቹም ዳኛውም የፈረጠመ…የረዘመ ነበር…ተክለ ሰውነት ከቁመት ጋር ሲታጀብ ጥሩ ነው… የውጭ ቡድኖችን ለማጫወት ስትወጣ ዝግባ ዝግባ የሚያካክሉ ተጨዋቾች ናቸው የሚገጥሙህ…አሳንሶ የሚመለከትህ ወይም አይን የማትሞላ ከሆነ ችግር ነው…እኔ እንግዲህ ረዥም ነው የምባለው አይደል…ውጪ ለማጫወት ስሄድ ወደ ላይ በጣም ተንጠራርቼ የማያቸው ተጨዋቾች ሁሉ ነበሩ… ከአምበሎች ጋር ስንጨባበጥ ከመፈርጠማቸው የተነሳ ማሽን የጨመቀህ ሁሉ እስኪመስልህ ድረስ ነው የሚጨብጡህ…ፊዚካሊ ብቁ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው…እንዳልከው የእኛ የተለየ ነበር…ግን የአምላክ ስጦታን ጠብቀን አሳድገነው ይመስለኛል እንደዛ የሆነው…
ሀትሪክ፡- …ጥቁሩን የዳኝነት ልብስ ለብሰህ ፊሽካ በአፍህ አርገህ ሃያ ዓመት አካባቢ አግር ኳሱን አገለገልክ ልበል…?
ኪነ፡- …የምን ሃያ ዓመት? 23 ዓመት አካባቢ አላጫወትኩም ብለህ ነው?የአንድ ወጣት እድሜን ገብሬበታለሁ…
ሀትሪክ፡- …23 ዓመት ሙሉ በታማኝነት ያገለገልከው ዳኝነትስ በምላሹ ምን አተረፈልህ?
ኪነ፡- እኔ በማማረር አላምንም…ብዙ ፈተናዎችና መሰናክሎች ቢያጋጥሙኝም በዳኝነት ሙያዬ ያተረፍኩት ይበዛል…በዳኝነት ሙያዬ ተጠቅሜበታለሁ፣አትርፌበታለሁ…ይሄንን ሁሉ የሕዝብ ፍቅር ያለስስት የሰጠኝ የዳኝነት ሙያዬ ነው…ይሄ ሁሉ ሰው አውቆኛል…ሀገር የመወከል ትልቅ ኃላፊነትንም ሰጥቶኛል…ይሄንን ሁሉ ሀገር ያየሁትም በዚሁ ሙያዬ ነው…ይሄ ሁሉ በገንዘብ ይገኛል? አይገኝም፤ ከዚህ አንፃር አትርፌበታለሁ…
ሀትሪክ፡- …በኢኮኖሚ በኩልስ ገንዘብ አግኝተህበታል…?…ተለውጠህበታል…?
ኪነ፡- …ምንም አላገኘሁበትም ብዬ መከራ ማውራት አልፈልግም…ዳኝነት ሀብት ላይ ወስዶ ባይጥለኝም ምንም አላሳጣኝም አግኘቼበታለሁ ብል ነው…ውስጤም ፈጣሪዬም የሚደሰቱት…በኢኮኖሚውም የተትረፈረፈ ነገር ባይኖረኝም እግዝአብሔር የፈቀደልኝን አግኝቼበት አልፌያለሁ…ከሀገሪቱ ትላላቅ ተጨዋቾች ያላነሰ ክብር ያስገኘልም ይሄው ሙያዬ ነው…ይሄ ሁሉ በገንዘብ ይገዛል?…ዳኛ ባልሆን አገኘው ነበር? አላገኘውም…በገንዘብ የማይታመን ብዙ ነገር አግኝቼበታለሁ…ዳኝነት ካሳጣኝ ነገር ይልቅ ያተረፈልኝ ይበልጣል ባይ ነኝ…
ሀትሪክ፡- …ታዲያ እውነታው ይሄ ከሆነ ለምን ሀገር ጥለህ ጠፋህ…?
ኪነ፡- …እሱ ሌላ ታሪክ አለው…ሀገር ጥዬ የሄድኩበት ምክንያት ሌላ የራሱ ታሪክ አለው…ከማግኘትና ከማጣት ጋር የሚያያዝ አይደለም…
ሀትሪክ፡- …እሺ እሱን እንመለስበታለን…ግን የአንተን መኮብለል ስመለከት ግርም የሚለኝ አንድ ነገር አለና እሱን ልጠይቅህ…?…ብዙ ጊዜ ተጨዋቾች፣አሰልጣኞች፣ አመራሮች ናቸው ሲኮበልሉ፣ሲጠፉ የሚታየው…ዳኛ ሆነህ የጠፋህ የመጀመሪያው ሰው አንተ ትመሰለኛለህ…በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ…?
ኪነ፡- …መጥፋትን በሙያ የምትመድበው አይመስለኝም…እንድትጠፋም እንዳትጠፋም የሚያደርጉህ ሁኔታዎች ናቸው…ሀገርህን ጥለህ ጥፋ ጥፋ የሚያሰኙህ ሁኔታዎች ናቸው…አሁን የወደቀን፣ ያበቃለትን ነገር መውቀስ ፈልጌ ሳይሆን …በወቅቱ በነበረው ስርዓት የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ነው ከሀገሬ የገፋኝ…እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም…ነገር ግን በወቅቱ የነበረው ስርዓት በሀገሬ መስራት እንደማልችል በተለያዩ ፈተናዎችና መከራዎችን ስላሳዩኝ…መሰደድን ነው የመረጥኩት…እነዚህ ሰዎች እስካሉ ድረስ ሀገሬን ተመልሼ አላይም ከተመለስኩ እርም ይሁንብኝ ብዬ አሜሪካ ሄጄ የቀረሁት፡፡
ሀትሪክ፡- …አንተ የስፖርት ሰው እንጂ ፖለቲከኛ አይደለህም…እዚህ ደረጃ ድረስ እንዴት ልትበቃ ቻልክ ብዬ የምጠይቅህ ግራ ስለገባኝ ነው?…
ኪነ፡- …አሁንም እደግምልሃለሁ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም…ግን እኔ የፖለቲካ ሰው ባልሆንም ስፖርቱም፣ስፖርቱ ውስጥ ያለን አንዳንድ ሙያተኞችም ፖለቲካው በሚልካቸው ስልጣኑን አንስቶ በሚያሸክማቸው የፖለቲካ ሰዎች ወይም ሹመኞች ብዙ ተፅዕኖ ይደርስብን ነበር…ማንኛውም ሰው እናንተም የሚዲያ ሰዎች ታውቁታላችሁ የነበረውን ነገር…አሁን ይሄ ይሄ ነው ብዬ ብዘረዝር ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ወይም የወደቀ ነገር ላይ ማውራት ይሆናል እንጂ ብዙ ፖለቲካዊ በደሎች ይደርሱብኝ ነበር…በዚህ ምክንያት ነው አይ ከዚህ በኋላ ሀገሬ ላይ መስራት አልችል ብዬ በዛው ወጥቼ የቀረሁት…ከዚህ ከመጥፋት ጋር በተያያዘ አንድ ነገር ልንገርህ…?…
ሀትሪክ፡- …ምን…?
ኪነ፡- …የመጥፋት ፍላጎቱ ቢኖረኝ ኖሮ ደቡብ አፍሪካ እጠፋ ነበር…ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ የሄድኩት ዳኛ እኔ ነበርኩ…ማንዴላ እንኳን ለስልጣን ሳይበቃ ነው እኔ የሄድኩት…ደቡብ አፍሪካ አዲስ አገር ናት…ለኑሮ፣ለስራ በጣም ምርጥ ናት በሚባልበት በዚያ ዘመን መጥፋት ብፈልግ እጠፋ ነበር…አንደኛ በጣም ወጣች ነኝ…ሁለተኛ ብዙዎች እንድጠፋ በጣም አግባብተውኝ ነበር…ከዚህ ሌላ ጣሊያን ሀገር እንግሊዝም በትራንዚት ይሁን በሌላ ምክንያት ሄጄ ነበር…ግን የመጥፋት ሃሳቡ በውስጤ ስላልነበር አላደረኩትም…ሀገሬንና እናቴን ጥዬ የትም አልሄድም ብዬ ነው የቀረሁት… ግን ነገሮች በሀገሬ መኖር እንደማልችል ሲነግሩኝ ነው በመጨረሻ የወሰንኩት…
ሀትሪክ፡- በአሜሪካ ኑሮህን ካደረክ 15 ዓመት አካባቢ አስቆጥረሃል፤ከአሜሪካ የሚመጣ ሰው ስራህ ምንድነው ተብሎ አይጠየቅምየሚለውን አባባል አክብሬ ስራህ ምንድነው የሚለውን ጥያቄ ሕይወት በአሜሪካ እንዴት ነው? በሚል ብለውጠው ትመልስልኛለህ?
ኪነ፡- …ስለ ስራ ብትጠይቀኝም እኔ ችግር የለብኝም…በአሜሪካ የሚናቅ ስራ የለም…ሁሉም ስራ ይከበራል…ሕይወት በአሜሪካ እንደት ነው? ላልከው…እውነት ለመናገር አሜሪካ ከሰራህበት ምርጥ…በጣም ደግ ሀገር ናት…ከሰራህ ጥሩ ኑሮ መኖር ትችላለህ…
ሀትሪክ፡- …ብዙ ሰው አሜሪካን ሀገር ገንዘብ የሚታፈስበት ሀገር እንደሆነች አድርጎ በሃሳቡ ይስላታል… አንተ ህያው ምስክር ነህና አሜሪካ ሄደህ ገንዘብ አፍሰህበታል…?…
ኪነ፡- …ምን እኔን ትጠይቀኛለህ…አንተም እንደ እኔ ባትኖርባትም አሜሪካንን ከአንዴም ሁለቴ መጥተህ አይተሃታል…ዲሲም ተገናኝተን የለ? አንተ ራስህን ልጠይቅህ በአሜሪካ ዝም ብሎ ገንዘብ ሲታፈስ አይተሃል?
ሀትሪክ፡- …አንተ ተጠያቂ እንጂ ጠያቄ ስላልሆንክ ራስህ መልስ ስጠኝ…?…
ኪነ፡- …አንተም በአይንህ ስላየኸው ብዬ ነው…እኔ በአሜሪካ ቁጭ ተብሎ ገንዘብ ሲታፈስ አላየሁም… ሀገሪቱ እንዳልኩህ በጣም ደግ ሀገር ናት… ከሰራህ ታከብርሃለች፡፡ ከሰራህ ታገኛለህ..ጥሩ ኑሮም ትኖርባታለህ.. ግን የምታገኘው ለፍተህ ደክመህ ነው… ስትሰራ ስትለፋ ዝም ብሎ የሚታፈስ ነገር የለም…ኮቪድ የፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ ቤቴ ቁጭ ብዬ የሚሰጠኝ un employment ክፍያ አለ… አሜሪካ እያለሁም እዚህ እስከመጣሁበት ጊዜ ድረስ የሚሰጠኝ ገንዘብ አለ…ግን አያረካም…ሰርተህ የምታገኘው ነው የሚያረካህ…ሰርቼ በማገኘው በጣም ደስተኛ ነኝ…ብዙ ትርፍ ፈልገህ ብዙ ስራ በመስራት ራስህን ካልጎዳህ በስተቀር…ራስህን እየጠበቅ…በቂ እረፍት እያደረክ የምትሰራ ከሆነ ከራስህ አልፈህ ቤተሰቦችህን…ከአንተ በታች ያሉትን የመርዳት አቅም የምታገኝባት ሀገር ናት…በአጠቃላይ ግን ደስተኛ ነኝ…፡፡
ሀትሪክ፡- … አሁን በምላሽህ በጣም ደስተኛ እንደሆንክ ነው የገለፅክልኝ…በአንድ ወቅት ግን ተማረህ ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ሁሉ ወስነህ እንደነበር የሰማሁት ውሸት ነው ማለት ነው…?
ኪነ፡- …(እንደ መሳቅ እያለ)…ውሸት አይደለም…እውነት ለመናገር መጀመሪያ እንደሄድኩ አካባቢ ደስተኛ አልነበርኩም…ለባህሉም፣ለአየሩም ለሁሉም ነገር እንግዳ ስትሆን በሌላ በኩል ናፍቆቱ፣ፍቅሩ ብዙ ነገር ረብሾኝ አልመች ብሎኝ ተቸግሬ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር ፕሮሰሱ ይሄንን ያህል ጊዜም ይወስዳል ብዬ ስላልጠበኩ ነው መሰለኝ አንድ ስድስት ሰባት ዓመት አካባቢ ለመላመድ በጣም ተቸግሬ ለመመለስ ሁሉ አስቤ ነበር…የሚገርምህ ነገር ግን ስራ እሰራለሁ…ገንዘብም አገኛለሁ ግን ደስተኛ አልነበርኩም…አእምሮዬ አይረካም ነበር…ከጓደኛህ፣ከሀገርህ ተለይተህ መኖርን መልመድ ከባድ ነው፤ ከወረቀትና ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ወደዚህ መምጣት አልችልም ነበርና ትንሽ ከብዶኝ ነበር… ግን እንደዚህ እንደ አሁኑ ነፃ ስትወጣ ደስ ይላል…አሜሪካ እንዳልኩህ ደግ ሀገር ናት…ስራ የሚወድ…የሚያከብርን ሰው እሷም ታከብራለች…ካለከበርካት እሷም አታከብርህም…
ሀትሪክ፡- …ከዚህ ከአሜሪካ ጉዞህ ጋር በተያያዘ ስታነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ…ወደ አሜሪካ እንደ ነገ ልትሄድ ስትል እንደዛሬ ጨዋታ መርተህ ተጨዋቾችን በቀይ ካርድ አንበሽብሸህ ነበር የሄድከው፤ እሱን አጋጣሚ ታስታውሰዋለህ…?
ኪነ፡-.. (በጣም ሳቅ)…. እውነት ነው እንዴት አስታወስከው ባክህ?…(አሁንም ሳቅ)…ነገሩምንድነው መሰለህ አንተ እንዳልከው እንደ ነገ ለመሄድ ስል ሣይሆን ከሁለት ቀን በኋላ ወደ አሜሪካ ልሄድ ስል የመከላከያንና የመብራት ኃይልን ጨዋታ እንድመራ እመደባለሁ..ከሁለት ቀን በኋላ ለመሄድ ሻንጣዬን ሁሉ አዘጋጅቻለሁ…ግን ብሄድም ሙያዬን ማክበር ስላለብኝ ኃላፊነቴን በአግባቡ ተወጥቼ መሄድ ነው ያለብኝ ብዬ ተዘጋጅቼ ነበር የገባሁት…ስማቸውን አሁን ረስቼዋለሁ ሁለት ተጨዋቾች ግብግብ ለመግጠም ይገባበዛሉ…ተው…!…ብላቸው ሊሰሙኝ አልቻሉም…አይ እንግዲህ የማትሰሙ ከሆነ አልኩና ከኋላ ኪሴ ቀይ ካርዱን መዘዝኩና ለሁለቱም እንካችሁ አልኳቸውና አስወጣኋቸው…በቀይ ከወጡት ሁለት ተጨዋቾች አንደኛው ከጓደኛዬ ጓደኛ ጋር ቅርበት ነገር አለው…በጣም አማሮ ምን ቢለው ጥሩ ነው…
ሀትሪክ፡- …ምን አለው…?
ኪነ፡- …“ኪነ የሚባለው ጓደኛህ ወደ አሜሪካ ሊሄድ የመጨረሻ ጨዋታ አጫውቶን የመሸኛ ነው ብሎ ነው መሰለኝ ቀይ ካርድ አያንበሸብሸንም መሰለህ” ብሎት በጣም አስቆኛል…አየኸው ሰው ከየት ወዴት እንደሚያገናኘው /ሳቅ/..
ሀትሪክ፡- …ግን ኪነ አንተ ሀገር ጥለህ እየሄድክ…የመጨረሻ ጨዋታህ እንደሆነ እያወክ…ለምን ጨከንክባቸው…?
ኪነ፡- …እንዴ ምን ማለት ነው…?…ሀገር ጥዬ እንኳን አሜሪካ ለምን ማርስ ላይ አልወጣም…?…የዳኝነት ባጄን፣ልብሱን እስከለብሰኩ ድረስ ተፈፃሚ ማድረግ ያለብኝ በታማኝነት አገለግላለሁ ብዬ የገባሁትን ሕግ ነው…ገና ለገና አሜሪካ እሄዳለሁ፣የመጨረሻ ጨዋታዬ ነው ብዬ ህጉን አላጣምም…ሙያዬን አክብሬ፣ሕጉን ተግብሬ ነው መሄድ የነበረብኝ ያንን አድርጌያለሁ…እንደተባለው ባደረግ ኖሮ ሙያዬን አዋርጄ የሄድኩ ያህል ይሰማኝ ነበር…ቀይ ካርዱ መሸኛ አለመሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ዳኝነትን ማቆም በሚገባህ ሰዓት ነው ያቆምከው…ፊሽካህን የሰቀልከው…?…
ኪነ፡- …አይደለም…!…ብዙ የዳኝነት ዘመኖች ከፊቴ እያሉኝ ነው ያቆምኩት…ኢንተርናሽናል ባጄ እንኳን ገና ቀሪ ጊዜ እያለው ከእነ ሙሉ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ክብሬ ነው የሄድኩት…እድሜዬ ራሱ ለኢንተርናሽናል ዳኝነት በጣም ገና ነበር…ብቆይ እንኳን በሀገር ውስጥ በኢንተርናሽናል ደረጃ ብዙ አመት የማጫወት እድሉ ነበረኝ፡፡
ሀትሪክ፡-በዳኝነት ዘመንህ ምነው ቀይ ካርድ ወይም ፔናሊቲ ባልሰጠው ብለህ የምትቆጭበት ጨዋታ አለ?
ኪነ፡- በቁጭት ደረጃ የማነሣው ጨዋታ የለም…በሀገር ውስጥ ሁሉም ሠላማዊ ነው…ግን መቆጨት ሣይሆን ፔናሊቲ መስጠት ሲገባኝ አልሰጠሁም ብዬ የማስታውሰው አንድ ጨዋታ አለ፤ የአርባ ምንጭና የመድን ጨወታ፤አርባ ምንጭ ላይ ነበር ፍልሚያው፤ አርባ ምንጭ ከዚያ በፊት በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት አልቀመሰም…ጊዮርጊስ አልቀረው ሁሉንም አሸንፏል…ወደ አምስት ተከታታይ ጨዋታ አሸንፈው ስድስተኛው ላይ እኔ ተመደብኩ…አርባምንጭ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የገባበትን ጨዋታ እኔ ነበርኩ ያጫወትኳቸው…ለዚህ ጨዋታ ተመድቤ ስሄድ በከተማው ብዙ ተወራ… በማይክራፎን ሣይቀር ኢንተርናሽናል አርቢትር ኪነጥብቡ ነው የሚመራው ተባለ…ጨዋታው መጀመሩ አይቀርም ተጀመረ…ህዝቡን ልነግረህ አልችልም ግጥም ብሏል…ሜዳው አባራ ነው…ጨዋታው እንደተጀመረ መድኖች አግብተው መምራት ጀመሩ…መጀመሪያ የነበረው ድባብ ወዲያው ተቀየረ… አርባ ምንጮች በጣም ረበሹኝ…ጨወታውን ትተው ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ…ፔናሊቲ ለማግኘት ይወድቃሉ ይነሳሉ…ካልተሰጠን ይላሉ ይጮሃሉ…ደጋፊውም አብሮ ያብዳል…ድንጋይ ይወረውራል…ፖሊስ በቦታው ተመድቧል ግን ፖሊስም አይከላከልም…በቃ እነዚህ ሰዎች ሊጨርሱን ነው አልኩኝ… መድኖች ደግሞ በቃ የሚያቆየችው አልተገኘም…በዚህ መሀል እያሉ አንድ የመድን ተጨዋች ፔናሊቲ ውስጥ ተጠልፎ ይወድቃል…ፔናሊቲው በትክክል ያሰጣል…እኔ ግን የምን ፔናሊቲ ነው…ቀጥል ስል… መድኖች በተራቸው አበዱ…
ሀትሪክ፡- …የሚያሰጥ ከሆነ ለምን አልሰጠህም…?
ኪነ፡- …ሰውዬ ምን ሆነሃል…?…በዛ የጋለ ስሜት…ድንጋይ እንደዝናብ እየወረደ ባለበት ሰዓት ያንን ፔናሊቲ ብሰጥ ምን እደሚፈጠር አስበሃል…?…ህዝብ ነው የሚያልቀው…በህይወቴ ትእግስት አድርጌ የመራሁት ጨዋታ እሱ ነው…መድኖች ለምን ከለከልከን ብለው አበዱ ተረጋጉ ብላቸው ሊሰሙ ነው? ከበቡኝ…እኔም በጣም ተበሳጨሁና…እናንተ አብዳችኋል ይሄንን ፔናሊቲ ብሰጥ በህይወት ሣይሆን አስክሬናችሁ ነው የሚወጣው…በሰላም ብትሄዱ አይሻልም? አልኳቸው…ደቂቃው አልቆ ነበር…ትንሽ እንደተጫወቱ ፊሽካዬን ስነፋው ሜዳው ተወረር…ምን…ምን …የሚያክል ድንጋይ እየመጣ ፊታችን ላይ ይወድቃል…ሁኔታው በጣም ያስፈራል…በመሃል ደግነቱ ፖሊሶች ሲከቡን ትንሽ እፎይ አልን …ብታምን ባታምንም ጨዋታው ካለቀ በኋላ ሜዳ ውስጥ ከ1 ሰዓት በላይ ቆይተናል…በቃ መሄድ አልቻልንም…መጨረሻ ላይ ከእነ ተጫወትንበት ልብስ ከእነላባን ልብሳችን ከሆቴል መጥቶልን አንድ አስተባባሪ በመኪና ደብቆን ወላይታ ሄደን አደርን…ሻወር እንኳን የወሰድነው ወላይታ ሄደን ነው…ያን አጋጣሚ መቼም አልረሳውም…መድኖች 2ለ0 ሊሆኑ የሚችሉበትን እንጂ የውጤት ለውጥ ስለማያመጣ ራሳችንን ሰውን ለማዳን ስል መከልከሌን አስታወሳለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ሜዳ ውስጥ በጣም የሚያስቸግርህ ተጨዋችስ ማን ነበር…?…
ኪነ፡- …በዚህ በኩል ጌታቸው ካሳ (ቡቡ)ን ነው የማስቀድመው…በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በአማካይ ስፍራ በጣም የማደንቀው ጌታቸው ካሳ /ቡቡን/ ነው ከካሳዬ አራጌ ጋር፤በጣም ይችላል.. በጣም ጎበዝ ተጨዋች ነው…
ሀትሪክ፡- …ግን እኮ በዚህ ደረጃ ለምታደንቀው ቡቡ… በተደጋጋሚ ቀይ ካርድ ሰጥተኸዋል…ይሄ ሁኔታ ሆን ብለህ እንደምታጠቃው አያስገምትም?
ኪነ፡- …(እየሳቀ)…አዎ…በተደጋጋሚ ቀይ ካርድ ሰጥቼዋለሁ…የሚገርመው አንድ ክለብ ብቻ እያለ መሰለህ በየሄደበት ክለብ ይሄን ቀይ ካርድ ሳሸክመው ነው ያለፍኩት…መብራት ኃይል፣ቡና ብቻ በየሄድበት ቀይ ሰጥቼዋለሁ…ቡቡ ከሜዳ ውጭ እግዚአብሔርን የሚፈራ…ሰውን የሚያከብር ሰው ነው…ሜዳ ውስጥ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው…የሚጀምርህ ደግሞ ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ነው የሚጀምርህ…ሲነካም ሳይነካም…“እይልን እንጂ…ለምን አታጫውተንም” ብሎ መነጫነጭ ይጀምራል… ተው አስወጣሀለሁ ስለው ሊሰማኝ ነው…!…ያኔ…አላርፍ ካልክ እልና ቀዩን መዝዤ ጀባ እለዋለሁ… ብቻ በዚህ አይነት በተደጋጋሚ ቀይ ካርድ ሰጥቼዋለሀ..የቀይ ካርዱ መብዛት ከእሱ በላይ እኔን በጣም አሳስቦኝ…ይሄ ነገር ከመደጋገሙ የተነሣ ሌላ ስሜት ይፈጥራል…ይሄ ልጅ ከሜዳ ውጪ ሰውን ቀና ብሎ የማያይ ሰው ነው…ለምን አላነጋግረውም አልኩና…አንድ ቀን ጠርቼ ጠየኩት…
ሀትሪክ፡- …ምን ብለህ…?
ኪነ፡- …ስማ ቡቡ ከእኔ ጋር ችግርህ ምንድነው…?…ችግርህ የሜዳ ነው…?…ከኳስ ጋር ነው…?…ወይስ ከእኔ ጋር የግል ፀብ አለህ…?…የግል ችግር ከሆነ አንነጋገርና እንፍታው አልኩት…አለበዚያ በቤተሰብ ችግር አለብን ብዬ ለፌዴሬሽኑ ላመልክትና ሁለተኛ አንተ ያለህበትን ቡድን አላጫውት አልኩት…
ሀትሪክ፡- …ምን አለህ…?
ኪነ፡- …መልስ ሊሰጠኝ ቀርቶ ቀና ብሎ ሊያየኝ ነው…“ኧረ ኪነ ምንም የግል ፀብ የለኝም…ሜዳ ውስጥ በጣም ስሜታዊ ስለምሆን ነው በጣም ይቅርታ አድርግልኝ” ይለኝና ይቅር ተባብለን እንለያየለን… እንደ አጋጣሚ በቀጣይ ጨዋታ ስንገናኝ ከቡቡ ጋር ስለታረቅን አገር ሠላም ነው በሠላም ይጫወታል ብዬ ሳስብ…ቡቡ እንደገና ይነሳበታል…ይጀምረኛል…የነበረውን እርቅና ይቅርታ እረስቶት “ኪነ እይልን እንጂ..አጫውተን እንጂ እያለ” ድጋሚ በጠበጠኝ…ጦርነትም ከፈተብኝ…በየጊዜው ማስወጣት እኔን ሰለቸኝ…በኋላ ጠራሁትና…ስማ ቡቡ ሜዳ ውስጥ ትሞታታለህ እንጂ…ቀይ ካርድ አልሰጥህም አልኩት…እንዳልኩህ ቡቡ ትልቅ ተጨዋች ነው…ሜዳ ውስጥ የክለቡን ውጤት ከመፈለግ በጣም ስሜታዊ ነው…በዚህ ስሜታዊነቱ ነው ከእኛ ጋር የሚጋጨው…ከቡቡ ሌላ ሚካኤል ሽፈራውም እንዲሁ ሜዳ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ነው…ከሜዳ ውጭ ደግሞ መሬት ነው…ከአንገቱ ዝቅ ብሎ በሁለት እጁ ነው የሚጨብጥህ…
ሀትሪክ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነህ በሚል ትታማለህ፤ በእርግጥ ደጋፊ ነህ?
ኪነ፡- ምን መሰለህ… በእርግጥ … የዚህንና የሌሎች ጥያቄዎችን መልስ ሳምንት ይጠብቁን፡፡
የተከበራችሁ አንባቢያዎቻችን የቀድሞው ኢንተርናሽናል አርቢትር ኪነ ጥበቡ 23 አመታትን ያስቆጠረው ተዝቆ የማያልቅ የዳኝነት ህይወቱን በአንድ እትም ማጠናቀቅ የማይቻል በመሆኑ ለቀጣይ ሣምንት በይደር ማቆየትን መርጠናል፤ በቀጣይ ሣምንት ከአርቢትሩ ጋር ስንመለስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነው በሚል ስለሚደርስበት ሀሜት፣በዳኝነት ዘመኑ ስለሚያደንቀው ተጨዋችና አሰልጣኝ፣ስለ ሙሉጌታ ከበደ ተንኮል፣ስለ መብራት ኃይሉ ተከለካይ ተስፊቲና በሌሎች ያልተነሱ አዳዲስ ጉዳዮች ከኢንተርናሽናል አርቢትር ጋር የምንጫወተው ብዙ ቁም ነገር አለን…የሣምንት ቀጠሮአችሁ ከወዲሁ ከሀትሪክ ጋር ይሁን፡፡