በትላንትናዉ ዕለት ጅማሮዉን ባደረገዉ የሀያ ሁለተኛዉ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዕለት ቀዳሚ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሀምበሪቾ ዱራሜን አንድ ለዜሮ በሆነ ዉጤት አሸንፏል።
በተመጣጣኝ የጨዋታ ፉክክር በጀመረው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐ ግብር ገና በጅምሩ ሀይቆቹ በቸርነት አዉሽ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ በጥብቅ መከላከል እና በመልሶ ማጥቃት በመጫወት ላይ የነበሩት ሀምበሪቾዎችም በ8ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማዉን ኳስ ትግስቱ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ግን በአግዳሚዉ አናት ላይ ዉጭ ወጥታለች ።
በተደጋጋሚ ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ይጥሩ የነበሩት ሀምበሪቾዎች በ 46ተኛዉ ደቂቃ ላይ በድጋሚ አስቆጪ የሚባል የግብ እድል ማግኘት ችለዉ ነበር ፤ በዚህም ከኋላ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ትግስቱ በግንባሩ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን የግቡ አግዳሚ ኳሷን መልሷታል።
- ማሰታውቂያ -
ከደቂቃዎች በኋላ ዳግም ከቀኝ መስመር በኩል የተገኘዉን ቅጣት ምት አጥቂዉ ካሪም በቀጥታ ወደ ግብ መትቶ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷ የግቡን አናት ታካ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም የመጀመሪያ አጋማሽ ያን ያህል አስደንጋጭ ሙከራ በሁለቱም ክቦች በኩል ሳይደረግ ተጠናቆ ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሯል ፤ በዚህም ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የጨዋታ ብልጫ እያሳዩ የመጡት ሀይቆቹ ሙከራዎችንም ማድረግ የጀመሩ ሲሆን ከነዚያም መካከል በ58ተኛዉ ደቂቃ ላይ እንየዉ ካሳሁን ከግራ መስመር በኩል ከቅጣት ምት ድንቅ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ ፓሉማ መልሶባቸዋል።
እንደነበራቸዉ ብልጫ በተደጋጋሚ የተጋጣሚ ቡድን ሶስተኛዉ የሜዳ ክፍል ላይ ይደርሱ የነበሩት ሀይቆቹ ዳግም በ66ተኛዉ ደቂቃ ላይ አስቆጪ ዕድል መፍጠር ችለዉ ነበር ፤ በዚህም አሊ ሱለይማን ከታፈሰ ሰለሞን የተቀበለዉን ኳስ በቺፕ ወደ ግብ ልኮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ተከላካዩ ዲንክ እንደምንም ደርሶ ኳሷን ከመስመር አድኗታል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ ላይም በ79ነኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሯል ፤ በዚህም ከቀኝ መስመር በኩል ተቀይሮ የገባዉ ኢዮብ አለማየሁ ያሻገረዉን ኳስ የሀምበሪቾዉ ተከላካይ ዲንክ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሮ ሀዋሳዎች እንዲመሩ አድርጓል።
በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ በራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመጫወት በመልሶ ማጥቃት የሚያገኟቸዉን እድሎች ለመጠቀም ሲጥሩ የነበሩት ሀምቀሪቾዎች የጨዋታዉ ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር እየተቀዛቀዙ ቀጥለዉ በተጨማሪም በአብዱልሰላም እና አብዱልከሪም የሱፍ አማካኝነት አንድ ሁለት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ ጨዋታዉ በሀዋሳ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በምሽቱ መርሐግብር ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታቸዉን ያለ ግብ በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት ምሽት አንድ ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃ ላይ ያን ያህል በርከት ያሉ ሙከራዎችን መመልከት ባንችልም ፤ ነገር ግን ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴን አስመልክተዉናል ።
በዚህ ሂደት ጅማሮዉን ባደረገዉ መርሐግብር በ12ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂዉ ዮሐንሰ በሰራዉ ስህተት የተገኘዉን ኳስ አማካዩ መስዑድ መሐመድ ለአቡበከር ሻሚል አቀብሎት ተጫዋቹም በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ራሱ ግብ ጠባቂዉ መልሶ ኳሷን ተቆጣጥሯል።
ከራሳቸዉ የግብ ክልል መስርተዉ ለመዉጣት ጥረት ያደርጉ የነበሩት አፄዎቹ በ19ነኛዉ ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከመሐል ክፍል የተሻገረለትን ኳስ የግብ ዘቡን ካለፈ በኋላ ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሷ ለጥቂት ወጥታለች። ከእነዚህ ተጠቃሽ ሙከራዎች በኋላ በቀሪ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ክለቦች በይበልጥ ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ የጨዋታ እንቅስቃሴን ሲያስመለክቱ ቆይተዉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ አዳማ ከተማዎች በ66ተኛዉ ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል የተጋጣሚ ቡድን ሶስተኛው የሜዳ ክልል ላይ ከደረሱ በኋላ ለሙሴ የሰጡትን ኳስ ተጫዋቹ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ዮሐንስ ግን በግሩም ብቃት አምክኗታል። ከዚች ሙከራ በኋላ በ74ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባዉ የፋሲል ከተማዉ የፊት መስመር ተጫዋች ደንቅ ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷ በግቡ አናት ላይ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
መርሐግብሩ ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ደቂቃዎች በቀሩበት ወቅም በ90+2ኛዉ ደቂቃ ላይ ብሩክ አማኑኤል ከኋላ መስመር የተሻገረዉን ኳስ የአዳማ ተከላካዮች ሲመልሱት አግኝቶ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ሰይድ ግን በሚገርም ብቃት ኳሷን ግብ ከመሆን ታድጎ ጨዋታዉ ያለ ግብ በአቻ ዉጤት ተጠናቋል።