ድሬዳዋ ከተማ ሻሸመኔ ከተማን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ቀን 10:00 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት በጀመረው ጨዋታ ገና በመባቻዉ ሻሸመኔዎች አማካኝነት ግብ አስቆጥረዉ የነበረ ቢሆንም ሂደቱ ከጨዋታ ዉጭ በሚል ተሽሯል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታዉ ተመልሰዉ እንቅስቃሴዉን ለመቆጣጠር የሞከሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ23ተኛዉ ደቂቃ ላይ በሙህዲን ሙሳ አማካኝነት የመጀመሪያ ሙከራዎችን አድርገዋል ።
በዚህ ሂደት ወደ ጨዋታዉ የገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በ32ተኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ዕድል መፍጠር ችለዉ ነበር ፤ በዚህም አጥቂዉ ካርሎስ ዳምጠዉ ከኋላ ክፍል የተሻገረለትን ኳስ በቀጥታ ቺፕ አድርጎ ለማስቆጠር ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷ በግቡ አናት ላይ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
ከመልካም አጀማመራቸው በኋላ በይበልጥ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመንቀሳቀስ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች መጫወትን ምርጫቸዉ ያደረጉት ሻሸመኔ ከተማዎች አጋማሹ መጠናቀቂያ 45ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ከግራ መስመር በኩል ሙህዲን ሙሳ ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ ካርሎስ ከርቀት ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በጥሩ የጨዋታ መንፈስ የተመለሱት ሻሸመኔ ከተማዎች በ54ተኛዉ ደቂቃ ላይ ወጋየሁ ቡርቃ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን የላከዉን ኳስ ኢዮብ ገ/ማርያም በግንባሩ በመግጨት ቢሞክርም የግብ ዘቡ አብዩ ካሳየ በጥሩ ቅልጥፍና ኳሷን ተቆጣጥሯል።
ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እየተደረገበት እና በሙከራ ረገድ ግን ተቀዛቅዞ በቀጠለዉ ሁለተኛዉ አጋማሽ በ75ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪዉ ካርሎስ በድጋሚ ድንቅ እድል አግኝቶ ቺፕ አድርጎ ቢሞክርም ኳሷን ግብ ጠባቂዉ መልሶበታል። በዚህ ሂደት እየቀጠለ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በደረሰዉ ጨዋታ በ82ተኛዉ ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ድንቅ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂዉ አቤል ሲመልስበት።
በደቂቃዎች ልዩነት ግን ሻሸመኔዎች ድንቅ ዕድል አጊኝተዉ ነበር በዚህም እዮብ ገ/ማርያም ያሻገረዉን ኳስ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ግብ ጠባቂዉ አብዩ በድንቅ ቅልጥፍና ኳሷን አዉጥቶ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በወላይታ ዲቻ የ1ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ምሽት አንድ ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ፊሽኻ በጀመረዉ የምሽቱ መርሐግብር ፈረሰኞቹ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ጫና ፈጥረዉ ለመንቀሳቀስ እና ሙከራዎችንም ለማድረግ ሲጥሩ የነበረ ሲሆን በዚህም ከአንድ ሁለት ኢላማቸውን ካልጠበቁ ሙከራዎች በኋላ በ22ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ሄኖክ ከማዕዘን ያሻማዉን ኳስ አጥቂዉ አማኑኤል ኤረቦ በግንባሩ ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ገጭታ ወጥታለች።
በዚህ ሂደት መከናወን በቀጠለዉ ጨዋታ ዲቻዎች በይበልጥ ከወደ መስመር ከሚነሱ ኳሶችን ዕድሎችን ለመፍጠር እና ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ በ25ተኛዉ ደቂቃ ላይም የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚህም የፊት መስመር ተጫዋቹ ብስራት በቀለ ከርቀት ያደረገዉን ድንቅ ሙከራ ግብ ጠባቂዉ ባህሩ ነጋሽ ተቆጣጥሯል።
በመጀመሪያዉ አጋማሽ መጠናቀቀያ ወቅት ፈረሰኞቹ ጥሩ የሚባል ተጠቃሽ ዕድሎችን ማግኘት ቢችሉም ሳይጠቀሙባቸዉ ቀርተዋል። ከነዚህም መካከል አማካዩ ዳዊት ተፈራ (ozil) በተከላካዮች መሐል ድንቅ ኳስ ለአጥቂዉ አማኑኤል ኤረቦ ቢያሾልክለትም ነገር ግን አጥቂዉ ከግብ ዘቡ ቢኒያሜ ገነቱ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ኳሷን አምክኗል።
አዕረፍት መልስ በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ቢኒያም በላይ ያሻገረዉን ኳስ አጥቂዉ ሞሰስ ኦዶ በቀጥታ ወደ ግብ ጨርፎ ለማስቆጠር ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል። በዚህ ሂደት በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ቢሆንም በሙከራ ረገድ ግን ቀዝቃዛ በነበረዉ ሁለተኛው አጋማሽ በ71ኛዉ ደቂቃ ላይ ወላይታ ዲቻዎች በአማካዩ አብነት ደምሴ አማካኝነት ድንቅ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም በግብ ጠባቂዉ ባህሩ ነጋሽ
ጥረት ኳሷን ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በ79ነኛዉ ደቂቃ ላይም ቢኒያም ፍቅሬ በመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ኳስ ለዘላለም አባተ አቀብሎት ተጫዋቹም በግሩም ሁኔታ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር ከደቂቃዎች በኋላም ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ በስህተት ወደ ኋላ የመለሰዉን ኳስ ያገኘዉ አጥቂዉ ቢኒያም ወርቅአአገኘዉ ኳሷን እየገፋ ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የግቡ ቋሚ ግን ሙከራዋ ግብ እንዳትሆን መልሷታል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ መርሐግብር በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ፈረሰኞቹ ጫና ፈጥረዉ ቢጫወቱም የአቻነት ግብ ማግኘት ሳይችሉ ጨዋታዉ በወላይታ ዲቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።