በዕለቱ የመጀመሪያ መርሐግብር መቻል ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
ቀን 10:00 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘ ፊሽካ በጀመረዉ የዕለቱ ጨዋታ ገና በመባቻዉ ቡናማዎቹ መነሻዉን ከአማኑኤል አድማሱ ባደረገ ኳስ በመስፍን ታፈሰ አማካኝነት ድንቅ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ከዚህ ሙከራ ከደቂቃዎች በኋላም ቡናማዎቹ በአንተነህ ተፈራ አማካኝነት በ9ነኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ሙከራ ካደረጉ በኋላ በዚያዉ ኳስ የተገኘዉን የማዕዘን ኳስ ዋሳዋ ጂኦፍሬ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷን የግቡ ቋሚ መልሷታል።
በዚህ ሂደት በጀመረዉ ጨዋታ መቻሎች በሂደት ወደ ጨዋታዉ ገብተዉ በ20ኛዉ ደቂቃ ላይ ጨዋታዉን መምራት ጀምረዋል ፤ በዚህም ሳጥን ዉስጥ ምንይሉ ወንድሙ ግብ ጠባቂዉን ለማለፍ በሚሞክርበት ወቅት የተሰራበት ጥፋት ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ተጫዋቹ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ግለቱ ተፋፍሞ በቀጠለዉ ጨዋታ መቻሎች በሽመልስ በቀለ አማካኝነት ከርቀት ድንቅ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂዉ በረከት ሲመልስ ፤ በፍቃዱ አለማየሁም አስደናቂ ሙከራን ማድረግ ችሏል። አጋማሹ ተጠናቆ በተሰጠ የጭማሪ ደቂቃ ላይ ግን ቡናማዎቹ የአቻነት ግብ አግኝተዋል። በዚህም ከኋላ ክፍል ዋሳዋ ጆፍሬ ያሻማዉ ኳሷ ግብ ጠባቂዉ መቆጣጠር ሳይችለዉ አምልጦት ያገኘዉ አማኑኤል አድማሱ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ክለቦች ምንም እንኳን በሙከራ ረገድ የተቀዛቀዘ ሁለተኛ አጋማሽ ያሳልፉ እንጅ ነገር ግን ቡናማዎቹ በይበልጥ ኳስን መስርተዉ ከራሳቸዉ የሜዳ ክፍል ለመዉጣት በመሞከር እና መሐል ሜዳዉን በመቆጣጠር ጫናዎችን ለመፍጠር እና ዕድሎችን ፈጥረዉ ጨዋታዉን ለመምራት ሲጥሩ ፤ በተቃራኒው መቻሎች ደግሞ ወደ መስመር ካደሉ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር እና ግብችን አስቆጥረዉ በጨዋታው ላይ መሪ ለመሆን ሲጥሩ ተስተውሏል። በዚህ ሂደት የቀጠለዉ ጨዋታ በቀሪ ደቂቃዎች ላይ ግብ ሳይቆጠርበት አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ፍፃሜዉን አጊኝቷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በባሲሩ ዑመር የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ሲዳማ ቡናን ማሸነፍ ችለዋል።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት ምሽት አንድ ሰዓት ሲል በጀመረዉ ተጠባቂ ጨዋታ የሊጉ መሪ ሆነዉ ጨዋታዉን የጀመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የጨዋታዉን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር በአንድ ሁለት ቅብብል ተጋጣሚ ቡድን ሳጥን ውስጥ ከደረሱ በኋላ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበሩ ሙከራዎች መካከል በግራ መስመር በኩል አዲስ ግደይ ከደስታ ዮሐንስ የተቀበለዉን ኳስ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም መክብብ ደገፉ ግን ኳሷን ግብ ከመሆን ታድጓል።
የተጋጣሚያቸው የጨዋታ ሂደት ላይ የተመረኮዘ የጨዋታ መንገድን ይዘዉ ወደ ሜዳ የገቡት ሲዳማ ቡናዎች በአብዝሀኛዉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመስመር በኩል የነበሩ ጫናዎችን በመዝጋት እና አልፎ አልፎ በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችም ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሎ አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል። በሁለተኛዉ አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች በርከት ያሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸዉን ተጫዋቾች ቀይረዉ በማስገባት ጨዋታዉን ለመቆጣጠር ሞክረዋል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ 76ተኛዉ ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናማዉ አማካኝ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ባሲሩ ዑመር ላይ በሰራዉ ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
በ81ኛዉ ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ የተገኘዉን ኳስ በቅርበት የነበረዉ አጥቂዉ ኪፕሩል በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ፍሬዉ ጌታሁን ግን በግሩም ብቃት ኳሷን መልሷል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ በ86ተኛዉ ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የመሪነት ግብ አግኝተዋል። በዚህም በግራ መስመር በኩል ኤፍሬም ወደ ዉስጥ ያቀበለዉን ኳስ አማካዩ ባሲሩ ዑመር ወደ ግብነት ቀይሮ በመጨረሻው ደቂቃ ክለቡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታዉን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።