መነሻ ገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ “ለቅ/ጊዮርጊስ ተሰልፌ በመጫወቴ ብደሰትም ብዙ ነገሮች ይጠበቁብኛል” አማኑኤል ተርፉ /ቅ/ጊዮርጊስ/
ቅዱስ ጊዮርጊስቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግዜናዎች

“ለቅ/ጊዮርጊስ ተሰልፌ በመጫወቴ ብደሰትም ብዙ ነገሮች ይጠበቁብኛል” አማኑኤል ተርፉ /ቅ/ጊዮርጊስ/

አጋራ
አጋራ

ቅ/ጊዮርጊስ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ያለፉት ሁለት ጨዋታዎቹ ላይ እየተጠቀመበት ያለ ወጣት ተጨዋች ነው፤ አማኑኤል ተርፋ ይባላል፤ ይህ ተጨዋች ከክቡር አቶ ይደነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ውድድር ላይ የተገኘ ሲሆን ለቅ/ጊዮርጊስ የታዳጊ ቡድንና ለኢትዮጵያም የታዳጊ ቡድን ሙሉ ጨዋታዎችን በመጫወት ስኬታማ ብቃቱን አሳይቷል፤ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ደግሞ ለቡድኑ በቋሚ ተሰላፊነት በገባባቸው ጨዋታዎች ላይ ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል፡፡
ለቅ/ጊዮርጊስ ክለብ በተከላካይ ስፍራው በመጫወት ላይ የሚገኘው አማኑኤል ተርፋን የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ስለ አስተዳደጉ፣ ስለ ኳስ ህይወቱ፣ ስለ ቅ/ጊዮርጊስ ክለብ እና በእግር ኳስ ተጨዋችነት ስለሚኖረው የቀጣይ ጊዜ እልሙ አናግሮት ተጨዋቹ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- የአንተ የትውልድ መገኛህ የት ነው? የትስ አደግክ? ስንት ወንድምና እህቶችስ አሉ?

አማኑኤል፡- የተወለድኩት በቤንሻንጉል ሀሶሳ ከተማ ውስጥ ነው፤ ሁለት እህቶች እና አንድ ወንድም አለኝ፤ እስከ ሶስት ዓመቴም ድረስ ነው እዛ የኖርኩት፤ ቀጥሎ ደግሞ ለስድስት ዓመታት ያህል በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኡጋንዳ ላይ የህፃንነት እድገቴን አደረግኩኝና ከዘጠኝ ዓመቴ ጀምሮ ነው አሁን እስከምገኝበት የዕድሜ ደረጃዬ ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ላፍቶ አካባቢ እየኖርኩኝ ያለሁት፡፡

ሀትሪክ፡- በሕፃንነትህ ዕድሜ ወደ ኡጋንዳ ያመራኸው ለምን ነበር?

አማኑኤል፡- ወላጅ አባቴ ነው ለስራ ወደዛ ባመራበት ሰዓት ሙሉ ቤተሰቡን በወሰደ ጊዜ እኔንም ያኔ ገና የሶስት ዓመት ልጅ በነበርኩ ሰዓት ከእሱ ጋር ልጓዝ የቻልኩት፡፡

ሀትሪክ፡- በኡጋንዳ የስድስት ዓመታት ቆይታ ምን ምን ነገሮችን ታደርግ ነበር?

አማኑኤል፡- በኡጋንዳ ቆይታዬ ትንሽ እንዳደግኩ ትምህርቴን ነበር ስማር የነበረው፤ ወደ አዲስ አበባ ከመጣው በኋላም ይሄን ትምህርቴን በማስቀጠል የ12ኛ ክፍልን አጠናቀቅኩኝ፤ በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ምንም እንኳን ኳሱንና ትምህርቱን አብሮ ማስኬድ ከባድ ቢሆንም እኔ ግን በርቀት ደረጃ የማርኬቲንግ ትምህርቴን እየተማርኩ ነው የምገኘው፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ወደ መጫወቱ እንዴት አመራ?

አማኑኤል፡- ህፃን እያለው ሙሉ ትኩረቴን ወደ ትምህርቴ ላይ ነበር የማተኩረው፤ የቤተሰቦቼ ፍላጎትም ኳስን እንድጫወት ነበር፤ ከኡጋንዳ በተመለስኩ በዓመቱ ግን ያኔ ገና የ10 ዓመት ልጅ ነበርኩና በላፍቶ አካባቢ የሚጫወቱ ታዳጊዎችን ሳይ የኳስ ፍቅሩ በጣም አደረብኝ፤ ከዛም ኳስን ለመጫወት የላፍቶ ፕሮጀክትን ተቀላቀልኩኝ፤ በእዚሁ የፕሮጀክቱ ቆይታዬም ላይ ጠንክሬ ስለሰራውኝ ለዛሬው ይኸውም ብዙ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ሊጫወቱበት ለሚመኙት ለታላቁ የቅ/ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ ልገባ እና የክለቡን መለያም አጥልቄ እስከመጫወት ደረጃም ላይ ደረስኩ፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ ስታመራ አርአያ /ሞዴል/ ያደረግከው ተጨዋች ነበር?

አማኑኤል፡- ማንም የለም፤ ምክንያቱም ያኔ ሕፃን በነበርኩበት ሰዓት ከኡጋንዳ መጥቼ ለላፍቶ ፕሮጀክት ስጫወት የሀገሪቱ ተጨዋቾችን የማየት እድሉ አልነበረኝምና፡፡

ሀትሪክ፡- በላፍቶ ፕሮጀክት ውስጥ ለስንት ዓመታት ሰለጠንክ? በኋላስ ወደየት አመራህ?

አማኑኤል፡- በፕሮጀክቱ የቆየሁት ለስድስት ዓመታት ያህል ነበር፤ ጥሩ ስልጠናንም አግኝቼ ነበር፤ በኋላ ላይ የእኛ ፕሮጀክት ቡድን በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ውድድር ላይ በጥሎ ማለፍ መልክ እንዲሳተፍ በተደረገበት ጊዜ ምንም እንኳን ቡድናችን ተሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ባያልፍም እኔ ግን ምርጥና ጥሩ ብቃቴን በማሳየቴ በቅ/ጊዮርጊስ የታዳጊዎች /u-17/ ቡድን አሰልጣኝ በነበረው ደረጄ ተስፋዬ /አንገቴ/ አማካኝነት የመጠራት እድል በማግኘቴና የተሰጠኝንም የሙከራ ጊዜ በማለፌ ክለቡን ልቀላቀል ቻልኩኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋች እሆናለው ብለህ አልመህ ታውቅ ነበር?

አማኑኤል፡- ኳስን ስትወድ ልጅ ሆነህ እኮ ብዙ ነገሮችን ታልማለህ፤ እኔም መጫወቱን በጀመርኩበት ሰዓት ለሀገሪቱ ትልቁ ቡድን ቅ/ጊዮርጊስ ገብቼ ብጫወት በሚል ያሰብኩበት ሁኔታ ነበርና ያን እውን ሆኖ ሳየው በጣም ነው ልደሰት የቻልኩት፡፡

ሀትሪክ፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ለቅ/ጊዮርጊስ በቋሚ ተሰላፊነት መጫወት ጀምረሃል፤ ይህን እድል በማግኘትህ ዙሪያ ምን ትላለህ?

አማኑኤል፡- በቅድሚያ ይሄን የመጫወት ዕድል በእዚህ የወጣትነት እድሜዬ ለማግኘት በመቻሌ ራሴን እንደ እድለኛ እቆጥረዋለው፤ ተደስቻለውም፤ ብደሰትም ግን ብዙ ነገሮችም ከፊቴ እንደሚጠበቁብኝም በሚገባ አውቃለው፡፡ ምክንያቱም ቅ/ጊዮርጊስ ትልቅ እና ብዙዎች ታዋቂ የሆኑም ያልሆኑም ተጨዋቾች ሊጫወቱበት የሚፈልጉት ቡድን ነውና ከዛ ውጪም ደጋፊውም የተለየ እና ለክለቡ ያለው ፍቅርም ከፍተኛ ስለሆነም የአሁን ሰዓት ላይ ለእዚህ ክለብ በመጫወቴ የተለየ አይነት የደስታ ስሜት በተደጋጋሚም እየተሰማኝ ነው የሚገኘው፡፡

ሀትሪክ፡- ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ራስህን እንዴት ገመገምከው?

አማኑኤል፡- በአሁን ሰዓት ለክለቤ ጥሩ እና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ያሳየው ያህል ጥሩ የሆነ ስሜት እየተሰማኝ ነው የሚገኘው፤ ይሄ ግን እኔን ፈፅሞ አያዘናጋኝም፤ ምክንያቱም እንደ ቅ/ጊዮርጊስ አይነት ትልቅ ቡድን ውስጥ ስትጫወት ብዙ ነገሮች ከአንተ ይጠበቁብሃልና፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና የሚኖረው የዛሬ ጨዋታ ምን መልክ ይኖረዋል? ምን ውጤትንስ ትጠብቃለህ?

አማኑኤል፡- ሲዳማ ቡና ጠንካራ ቡድን ነው፤ ከእነሱ ጋር የሚኖረንም ጨዋታ ቀላል አይሆንም፤ እንደዛም ሆኖ ግን ቡድናችን ካለፉት ጨዋታዎቹ ብዙ ነገሮችን እየተማረ የመጣበት ሁኔታ ስላለ ይህን ጨዋታ በማሸነፍ ከመሪው ቡድን ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነት እንደምናጠብ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ እና ሲሸነፍ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ነው ያለህ?

አማኑኤል፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ማሸነፍ፣ መሸነፍ እና አቻ መለያየት በእግር ኳሱ ውስጥ ያለ እና የሚኖር እንደሆነ ባውቅም ሁሌም ድልን ለለመደው የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ተጫውተህ ስትሸነፍ ግን ተቀባይነቱ ብዙ ስለማይኖር ስሜቱ በጣም ከባድ ነው፤ ያ ስለሆነ ሁሌም ለማሸነፍም ነው የምትጫወተው፡፡

ሀትሪክ፡- የቅ/ጊዮርጊስን የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ አጠቃላይ ጉዞን እንዴት እየተመለከትከው ነው?

አማኑኤል፡- ውድድሩን ስንጀምር 70 ፐርሰንት ሁሉንም ተጋጣሚዎቻችንን ካለን ልምድ በመነሳት እንደምናሸንፋቸው እርግጠኞች ነበርን፤ አሁን ላይ ሊጉን እንደምናየው ግን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ስናመራ የምናገኛቸው ቡድኖች ከባድ እየሆኑብንና ለእኛ ደግሞ ጠንክረው ስለሚመጡብን ከእዚህ በኋላ ያለቡንን ጨዋታዎች ለሻምፒዮናነት ከመጫወታችን አንፃር እያሸነፍን ለመጓዝ በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ስታድግ ነባር ተጨዋቾቹ እንዴት ተቀበሉ?

አማኑኤል፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን በምጫወትበት ሰዓት ወደ ዋናው ቡድን ሄጄ በተመላላሽነት እሰራ ነበር፤ ያኔም ነበር ሲኒየር ተጨዋቾቹ እኔን ያውቁኝ እና ያበረታቱኝ የነበሩት እና አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ አድጌ የዋናውን ቡድን ስቀላቀል ብዙም እንዳልቸገር ነው ያደረገኝ፤ የቅ/ጊዮርጊስ ነባር ተጨዋቾች በአሁን ሰዓት ለእኔ በመምከርም ሆነ ጉድለቶቼን በመጠቆም በብዙ ነገሮች እንድሻሻል እያደረጉኝ ነው፤ ለዛም አመሰግናቸዋለውኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ተሰልፎ የመጫወት እድሉን ከማግኘት ጋር በተያያዘ ለራስህ የተለየ ግምት ትሰጣለህ?
አማኑኤል፡- በፍፁም ገና መቼ ተጫውቼ፤ ወደፊትም ቢሆን ብዙ የመጫወት እድልን ሳገኝ ራሱ ራሴን በተለየ መልኩ አላይም፤ የሚያስኮፍሰኝም ነገር አይኖርም፤ የእኔ ዋናው እቅድም ኳሱ ስራዬ ነውና ጥሩ ነገርን ለክለቤ በመስራት መመስገንን ነው የምፍልገው፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነታቸው በጣም የምታደንቀው እነማንን ነው?

አማኑኤል፡- ከሀገር ውስጥ ከሆነ ሳላህዲን ሰይድን ነው፤ ከውጪዎቹ ደግሞ ሊዮኔል ሜሲን፡፡

ሀትሪክ፡- ሳላህዲን ሰይድ የእናንተ ክልል ያፈራው ተጨዋች ነው፤ ስለ እሱ እና ስለ ክልላችሁ ምን ትላለህ?

አማኑኤል፡- ሳላህዲን በችሎታው የማደንቀው ተጨዋች ከመሆኑ ባሻገር እኔንም ጥሩ ደረጃ ላይ እንድደርስ ካለው ልምድ በመነሳት እየመከረኝ ነው፤ አመሰግነዋለው፤ የእኛን ክልል ቤንሻንጉልን በተመለከተ ደግሞ በርካታ ተጨዋቾችን ለሀገር እግር ኳስ ያፈራ ስለሆነ በእዚህ ደስ ይለኛል፤ ወደፊትም ብዙ ተጨዋቾችን ክልላችን ማፍራቷ የማይቀር ነው፤ እኔም ወደፊት ጥሩ ደረጃ ላይ ስደርስ ለክልሌ ማድረግ የምፈልገው ነገር አለ፡፡

ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ተመርጠህ ተጫውተሃል፤ ስሜቱን እንዴት አገኘኸው?

አማኑኤል፡- ያኔ ሙሉውን ጨዋታ ማለትም ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሩዋንዳ እና ከኡጋንዳ ጋር ደግሞ በምድብ ጨዋታ ላይ እና በፍፃሜ ጨዋታ ላይ ነበር ልጫወት የቻልኩት፤ ለቡድኑ ተመርጬ በመጫወቴ በጣም ነበር የተደሰትኩት፤ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳናና ደረጄ ተስፋዬ የሚመራው ይኸው ቡድንም ጥሩ ነበር፤ ሻምፒዮና መሆን ይገባውም ነበር፤ ግን እግር ኳስ ሆነና ውድድራችንን በሁለተኝነት ልናጠናቅቅ ችለናል፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ምን እያለምክ ነው?

አማኑኤል፡- ለብሔራዊ ቡድን ተመርጬ መጫወት እፈልጋለው፤ ከክለቤ ቅ/ጊዮርጊስ ጋር ደግሞ የሊጉን ዋንጫ ከማንሳት ባሻገር በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ በመሳተፍ እስከ ዋንጫ ባለቤትነት በሚያስደርስ ደረጃ ስኬታማ ውጤትን ማስመዝገብ እፈልጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?

አማኑኤል፡- በእግር ኳስ ጠንክረህ እና በርትተህ ከሰራ የማይደረስበት ነገር ምንም የለም፤ ለዛም ስል ነው ሁሌም ጠንክሬ ስለሰራው ዛሬ በዚህ ስፍራ ላይ ልገኝ የቻልኩት፤ ለእዚህ እንድበቃ ደግሞ ትልቁን አስተዋፅኦ ካደረጉልኝ ሰዎች መካከል አንዱ እንደ ሁለተኛ አባቴ የማየው አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ /አንገቴ/ ነው፤ እሱ በብዙ ነገሮች ቀርፆኛል፤ በጣም ነው የማመሰግነው፤ ከእሱ ሌላ ደግሞ ቤተሰቦቼን፣ የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋቾችን፣ የስታፉ አባላትን፣ አመራሮቹን እና የላፍቶ ፕሮጀክት አሰልጣኜን ብሩክን ላመሰግናቸው እፈልጋለውኝ፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...