አዳማ ከተማ በቀድሞ በክለቡ ተጫዋቾች ዮሴፍ ዩሐንስ እና የቀድሞዉ የክለቡ ሀኪም በነበረዉ አቶ ዮሐንስ ጌታቸው በቀረቡበት አቤቱታዎች ምክንያት የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፎበታል።
በአሁን ወቅት በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘዉ እና የቀድሞዉ የአዳማ ከተማ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የነበረዉ ዮሴፍ ዮሐንስ በአዳማ ቤት እያለ የ2013 ዓ/ም የሐምሌ እንዲሁም የ2014 ዓ/ም የግንቦት እና የሰኔ ወር ደሞዝ አልተከፈለኝም በማለት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ አቤቱታ አቅርቦ ነበር።
በጉዳዩ ዙሪያ ክለቡ ለአቤቱታው ምላሽ እንዲሰጥ የዲሲፕሊን ኮሚቴዉ ጠይቆ ክለቡ ምላሽ አለመስጠቱን የዲሲፕሊን ኮሚቴዉ ገልፆ በ7 ቀናት ውስጥ የተጫዋቹን ደሞዝ ክለቡ እንዲከፍል አለበለዚያ ከዝውውር መስኮት እንዲታገድ ውሳኔ መወሰኑን አስታዉቋል።
- ማሰታውቂያ -
እንዲሁም በተጨማሪ የቀድሞዉ የክለቡ ሀኪም አቶ ዮሐንስ ጌታቸዉ የ2011 ዓ/ም የግንቦት እና የሰኔ የሁለት ወር እንዲሁም የ2012 ዓ/ም የሰኔ የአንድ ወር ደሞዝ እና የፊርማ ክፍያ 70 ሺህ ብር አልተከፈለኝም በማለት ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ወስዶት ነበር።
የዲስፕሊን ኮሚቴዉ ጉዳዩን ከሁለቱም ወገን ሲመለከት ቆይቶ አዳማ ከተማ ለአቶ ዮሐንስ ጌታቸዉ የ2012 ዓ/ም የሰኔ የአንድ ወር ደሞዝ እና የፊርማ ክፍያ 70 ሺህ ብር በሚቀጥሉት 7 ቀናት እንዲከፍል ዉሳኔ አስተላልፏል።
በተጠቀሱት ቀናት ዉስጥ ይህ ሳይሆን ከቀረ አዳማ ከተማ በተጫዋች ምዝገባ እና ዝውውር እንዳይስተናገድ እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ሲል የዲስፕሊን ኮሚቴዉ ውሳኔ አሳልፏል።