“የተጨዋቾች ዝውውር የሚጸድቀው በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በመገኘት ብቻ ይሆናል”
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን
*…..ፋሲል ከነማ በቀድሞ አሰልጣኙ ክስ ከዝውውር መስኮቱ ታግዷል…
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት የፊታችን ሀምሌ 8/2015 እንደሚከፈት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
- ማሰታውቂያ -
ፌዴሬሽኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶችም ሆነ የወንዶቹ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ሀምሌ 8 ተከፍቶ መስከረም 25/2016 እንደሚዘጋና ዝውውሩ ለ82 ቀናት ክፍት እንደሚሆን አስታውቋል።
ፌዴሬሽኑ በሰጠው ማሳሰቢያ የተጨዋቾች ዝውውር ህጋዊነት የሚጸድቀው በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን
ጽ/ቤት በመገኘት ብቻ እንደሆነ በመግለጽ የክልል የእግርኳስ ፌዴሬሽኖች ዝውውርን ማጽደቅ እንደማይችሉ አስታውቋል። የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ በተጨዋቾችና በክለቦች መሃል ልዩነት ሲፈጠር ፌዴሬሽኖች ለክለቦቹ ያደላሉ የሚለውን ስሞታ የሚያስቀር ሆኗል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፋሲል ከነማን ከዝውውር ማገዱን አስታውቋል። የፌዴሬሸኑ የፍትህ አካላት የሆኑት የዲሲፕሊንና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች በቀድሞ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ሃይሉ ነጋሽ / ቲጋና/ እና በክለቡ መሀል የተፈጠረውን የክስ ሂደት ከመረመሩ በኋላ ክለቡ የአሰልጣኙን ቀሪ የ6 ወር ደመወዝ እንዲከፍል የወሰኑትን ውሳኔ ተግባራዊ ባለማድረጉ ሀምሌ 8 ከሚጀመረው የዝውውር መስኮት ተሳታፊነት ማገዱን አስታውቋል።
” አሰልጣኙ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ወስኖ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ያጸናውን ውሳኔ ክለቡ አልተገበረም በሚል
ለጽ/ቤቱ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል ከቀጣዩ የዝውውር መስኮት የታገዳችሁ መሆኑን እንገልጻለን” በማለት ውሳኔውን ለክለቡ አሳውቋል።
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ አመራሮች የፍትህ አካላቱ ውሳኔን ካልተቀበሉ ወደ ዓለምአቀፍ የግልግል
ፍ/ቤት የመሄድ የመጨረሻ መብት እንዳላቸው ይታወቃል።