- ማሰታውቂያ -
በቅድሚያ ምስጋና
የለንደን ቆይታዬን የምጀምረው በምስጋና
ነው፤ በቅድሚያ ለዚህ ቦታ ትመጥናለህ ይገባሀል
ብለው ዕድሉን የሰጠኝን የኢትዮጵያ የስፖርት
ጋዜጠኞች ማህበርን ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ፡
፡ የነገሮች ሁሉ ምክንያት ናቸውና፡፡ ከዚህ ውጪ
በለንደን የተሻለ ቆይታ እንዲኖረኝ ማረፊያ ቤት
ከማዘጋጀት ጀምሮ በለንደን ባይተዋርነት ሳይሰማኝ
አዝናኝና ጣፋጭ ጊዜን እንዳሳልፍ ከፍተኛ
ርብርቦሽ ያደረጉትና ወንድማዊ ፍቅራቸውን ያለ
ስስት የሠጡኝን የድል (ቪክ ኦሎምፒያ) ባርና
ሬስቶራንት ባለቤት እንዲሁም ከመነሻው እስከ
መጨረሻው ከጎኔ በመሆን ዕውነተኛ ወንድማዊ
ፍቅራውን ያሳዩኝና አብረውኝ የማይረሳ ጣፋጭ
ጊዜን ያሳለፉት የትሪቡን ስፖርት አዘጋጆች
ጋዜጠኛ ኤፍሬም የማነ እና ጋዜጠኛ ፍቅር
ይልቃልን እንዲሁም የኢ.ቢ.ኤስ ስፖርት ዋና
አዘጋጅ የሆነውን ጋዜጠኛ ፍስሀ ይድነቃቸውን
ለነበረን የማይረሳ ጣፋጭ ጊዜ በአንባቢዎቼ ስም
አመሰግናለሁ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በግዙፉ
የኤምሬትስ ስቴዲየም ተገኝቼ የአርሰናል እና
የሌሲስተር ጨዋታ እንድከታተል “ይህ ታሪካዊ
ጨዋታማ ሊያመልጥህ አይገባም” በሚል
ቁጭት የዚህ ታሪካዊ ጨዋታ አካል እንድሆን
የመግቢያ ቲኬት በማመቻቸት አጋርነታቸውን
ያሳዩኝን የትሪቡን ስፖርት አዘጋጆች ጋዜጠኛ
ኤፍሬም የማነ እና ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃልን
ለመልካሙ ስራችሁ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን
በድጋሚ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ፡፡ ዛሬ የለንደን
ማስታወሻዬን በውድድሩና በአዘጋጇ ሀገር
ለንደን እንዲሁም በአትሌቲክሳችን ውስጥ
ተቀብረው ስላሉት አደጋዎች ትዝብቴን
ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ፡፡ በመጪው ሳምንት
ደግሞ ስለ ኤምሬትስ ስቴዲየም፣ አርሰናል
ከሌሲስተር ሲቲ ስላደረጉት ጨዋታ እንዲሁም
የለንደንን ገጠመኞቼንና የቼልሲ ሜዳ የሆነው
ስታምፎርድ ብሪጅ ጉብኝቴን ይዤ እቀርባለሁ፡
፡ መልካም ቆይታ፡፡
ለንደን ክፍል 1
ለንደንን እንደመነሻ
Fare Well London Welcome Doha
“ደህና ሰንብች ለንደን፤ እንኳን ደህና
መጣሽ ዶሀ”
አዎን…! ላለፉት ሁለት ሳምንታት ዓለምን
ሁሉ አንድ ቋንቋን ብቻ ሲያናገር የነበረው
16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዚህ
በኃላ ወደነበርነትና ወደ ታሪክነት ተቀይሯል፡፡
የታላላቅ ስም ባለቤት የሆኑ አትሌቶችን
አስገራሚ ድል፣የታላላቅ አትሌቶች ያልተጠበቀ
አስደንጋጭ ሽንፈቶችን፣ የትራክ ንጉሱን
የአለማችን ፈጣን እግር ባለቤት አሳዛኝ
ሽኝት፣ የቀጣዩ የአለማችን አትሌቲክስ አዳዲስ
ጀግኖችና አልጋ ወራሾች፣ አዲስ የአለም ሪከርድ
የተመዘገበበት ልዩ የደስታም ድባባ፣ከመጠን
ያለፈ የደስታና የሐዘን እንባን እያፈራረቀ
ሲያስኮ መኩመን የነበረው የለንደኑ የዓለም
አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪኩንና ትዝታውን
ብቻ ትቶልን ከዚህ ቀደም እንደነበሩት የዓለም
ሻምፒዮናዎች ወደ ነበርነትና ወደ ታሪክነቱ
ከተቀየረ ዛሬ ድፍን 20 ቀንን ቢያስቆጥርም
ባማረውና በደመቀው ዝግጅትዋ ግን ለንደን
ሁሌም ስምዋ ከፍ ብሉ ሲነሳ፤ስትታወስ
የምትኖርበትን ደማቅ አሻራ ጥላ አልፋለች፡፡
በዚህም ማነው…ባለተራ እንዲሉ ቀጣዩ የዓለም
ሻምፒዮና አዘጋጅ የሆነችው አገር የኳታርዋ
ዶሃም የከበደ አደራዋን ከለንደን እንድትሸከም
አድርጓታል፡፡
ከ202 አገራት የተውጣጡ ከ3200
የፕላኔታችን ፈጣን የሆኑ አትሌቶች ለንደን
ውስጥ ከትመው ለወርቅና ለባንዲራቸው
ሲፋለሙ ቢከርሙም እድል ቀንቷቸው
ውጤታማ በመሆን የአገራቸውን ስም በሜዳልያ
ሰንጠረዥ ውስጥ ማስገባት የቻሉት ከ202
አገራት ውስጥ ከ42 ያልበለጡት ብቻ ናቸው፡፡
ከፊፋው የዓለም ዋንጫና ከኦሎምፒክ
ቀጥሎ የዓለማችን ሶስተኛው ታላቅ ውድድር
የሆነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከዛሬ
ከነበሩት 15 ሻምፒዮናዎች በተመልካች
ብዛት፣ በተሳታፊ አገሮች፣ በአትሌቶች
ቁጥር ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ የተሻለ ሆኖ አዲስ
የውደድሩን ሪከርድ በጊነስ ወርልድ ሪከርድስ
ላይ ለማሰፈር በቅቷል፡፡
ከ2012ቱ የለንደን ኦሎምፒክ የደመቀና
ያማረ መስተንግዶ በኋላ እንዲሁም የ2017
የአለማችን ትልቁን ውደድር በድጋሚ
ማስተናገድ እድል ያገኛቸው ለንደን ያዘጋጀችውን
ታላቅ ድግስ ከግማሽ ሚሊየን (700 ሺ) ህዝብ
በላይ በአካል ተገኝቶ በኦሎምፒክ ስቴዲየም
የተከታተለው ሲሆን በBBC 1 ቴሌቭዥን
ደግሞ ከ9.9 ሚልዮን ህዝብ የውድድሩን
አስገራሚ ድራማዎች፣ አንፀባራቂ ድሎች፤
የአትሌቲክሱ ፈርጦችን ይፋዊ ሸኝት በቀጥታ
የቴሌቭዥን ስርጭት መከታተላቸው ለንደን
በአዲስ ሪከርድ ታጅባ ውድድሯን ለማጠናቀቅዋ
ምስክሮች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጦች ማህበር
በሰጠኝ እድል መሰረት የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ
ፌዴሬሽኖች ማህበር /IAAF/ እንዲሁም የለንደን
አዘጋጅ ኮሚቴ /LOC/ በጋራ ባደረጉልኝ የቀጥታ
ግብዣ በለንደን ተገኝቼ እንደተከታተልኩት
የዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና
ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ ፍፁም የተለየና በልዩ
ልዩ አስገራሚ ድራማዎችና አሳዛኝ ገጠመኞች
የተሞላ እንደነበር ለማረጋገጥ ችያለሁ፡
፡ በዚህ በኩል በተለይ ውድድሩ የተካሄደበት
የለንደኑ ኩዊን ኤልዛቤት ኦሎምፒክ ስቴዲየም
በተመልካች የሚጨናነቀው እንደ ፊልም
በተመረጡ ውድድሮች ወይም የታላላቅ ስም
ባለቤት የሆኑ አትሌቶች ሲወዳደሩ ብቻ ሳይሆን
ሜዳሊያ የማያስገኙ የማጣሪያ ውድድሮች
ሲካሄዱም ጭምር መሆኑ እንግሊዞች እግር
ኳስን ብቻ ሳይሆን ስፖርትን እንደሚወድ በቂ
ማረጋገጫ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
በ2015 ቤጂንግ ባስተናገደችው በ15ኛው
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአጠቃላይ
የተገኘው የተመልካች ቁጥር ከ400 ሺህ ከፍ
አለማለቱን በለንደን ኦሎምፒክ ስቴዲየም
ከተገኘው 700 ሺህ ተመልካች ጋር ሲነፃፀር
እንግሊዛዊያን ለእግር ኳስ ብቻ እንደተፈጠሩ
አድርገን ማሰባችን ስህተት እንደነበርና
እንግሊዞችና እግር ኳስን ብቻ ሳይሆን
ስፖርትን እንደሚወድ ቁጥሮች አፍ አውጥተው
ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡
በለንደን እግር ኳስ ይበላል፤
ይጠጣል፤ ይተነፈሳል
የአዲስ አበባን ዕጥፍ ህዝብ ያላት ለንደን
በ2016 ዓ.ም በተደረገ ቆጠራ ወደ 9 ሚሊዮን
ህዝብ የሚኖርባት የአለማችን ምርጥ ከተማ
ናት፤ ለንደን እንደ አቶም እሳት በሚንቀለቀለው
የእግር ኳስ ከተማነቷ ብቻ ሳይሆን የአለማችን
የፖለቲካ፣ የፋሽን፣ የኢኮኖሚና የባህል
ከተማነቷም ተለይታ ትታወቃለች፡፡ ከ70
አገራት በመጡ ሰዎች ከ300 በላይ ቋንቋዎች
የሚነገሩባት ከተማ በመሆንዋም “አለም
በአንድ ከተማ ውስጥ” የሚል ስያሜ ለለንደን
አሰጥቷታል፡፡ ጥንታዊነቷን
የረቀቁ የስነ-ህንፃ ጥበብ ባረፈቡቸው
ህንፃዎቿ ብዙዎች ለንደንን ከልብ ይወዷታል፡
፡ ለንደንን ከሌሎች ከተሞች የሚለያት ረቂቅ
የስነ-ህንፃ ጥበብ ላረፉባቸው የተለያዩ አሮጌ
ህንፃዎቿ ዋጋ በመስጠት ትናትናን ከዛሬ
ጋር አጣምራ መያዟና በዚህም እንደ መፅሀፍ
የምትነበብ ከተማ መሆኗ የብዙዎችን ትኩረት
እንድታገኝ አድርጓታል፡፡ በቅርቡ ከአውሮፓ
ህብረት ራስዋን ለመለየት ደፋ ቀና የምትለው
ለንደን በውስጧ አቅፋ በያዘቻቸው ላንድማሮኮች
(የቱሪስት መስህቦች) የበርካታ ቱሪስቶች
መጉረፊያ አገርም ናት፡፡
የለንደን ምልክትና የቱሪስት መስህብ
ከሆኑት ውስጥ Buckingham Palace
የሚባለውና 775 ክፍሎችን በውስጡ የያዘው
የንግስቲቱ መኖሪያ ቤት፣ No.10 የጠቅላይ
ሚኒስትሩ መቀመጫ፣ The Tower of
London and Tower Bridge፣ Big Ben and
Parliament፣ የአለማችን ምርጡ ሙዚየም
(National Gallery) የመሳሰሉት ለንደንን
ከረገጡ የግድ ሊያዩዋቸው የሚገቡ የለንደን
መለያ የሆኑ የቱሪስት መስህቦች ናቸው፡፡ ለንደን
በውስጧ ሸሽጋ የያዘቻቸውን ላንድማርኮች
(የቱሪስት መስህቦችን) ለማየት በየዓመቱ
ከመላው አለም ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ
ቱሪስቶች የለንደንን ምድር ያጨናንቃሉ፡፡ ለንደን
አመቱን ሙሉ እረፍት የሌላትና በቱሪስቶች
የተጨናነቀች ከተማ በመሆንዋ ከቱሪስቶች
በሚገኘው ገቢ ኢኮኖሚያዋ በከፍተኛ ደረጃ
ተጠቃሚ ነው፡፡ በ2016 በተደረገ ጥናት ለንደን
ከ31.5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የጎብኝዎችን ቁጥር
ማስተናገዷ ትልቁ ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ ይሄ
ካለፉት አመታት አንፃር ሲታይ 20 ፐርሰት
እድገት እንዳሳየም ነው ባለሙያዎች የገለፁት፡፡
እንደ እነዚህ አጥኚዎች ከሆነ በ2020 ይሄ ቁጥር
በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ግምታቸውን
አስቀምጠዋል፡፡ በእርግጥ ለንደን ውብ ከተማ
በመሆንዋ የህዝቡ መጉረፍ ላያስገርም ይችላል፡፡
ብዙዎቻችን ብዙ ህዝብ ወደ ለንደን የሚጎርፈው
ሌላው መታወቂያዋ የሆነው እግር ኳስን በአካል
ተገኘቶ ለመከታተል ብቻ እንደሆነ አድርገን
እናስባለን፡፡ በእርግጥ ይሄን ማሰባችን ስህተት
ባይሆንም ለንደን የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ
እና የፋሽን ከተማ ብቻ ሳትሆን የእግር ኳስ
ከተማም በመሆንዋ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች
እግር ኳስን ፍለጋ ወደ ለንደን ይበራሉ፡፡
በአካል ተገኝቼ ለመታዘብ እንደ ቻልኩት
ለንደናውያን እግር ኳስን ብቻ ሳይሆን ስፖርትን
እንደሚወዱ ብረዳም ለእግር ኳሱ ግን ፍፁም
የተለየ ፍቅር አላቸው፡፡ በለንደን እግር ኳስ
ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይተነፈሳል፤ ለለንደኖች
እግር ኳስ ሁሉም ነገራቸው ነው፤ እግር ኳስን
በፍቅር ይወዳሉ ብቻ ሳይሆን እግር ኳስን
ይኖሩታል፡፡ ያለ እግር ኳስ ህይወት ያላቸውም
አይመስሉም፡፡
ለንደንን መቀመጫቸው ያደረጉት ወደ
አራት የሚጠጉ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች
መኖራቸው ለንደን የሚፋጅ እግር ኳሳዊ
ሙቀት እንዲኖራት ምክንያት ሆኗል፡
፡ አርሰናል፣ ቼልሲ ዌስትሃም እና ቶተንሃም
በለንደን የሚገኙ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች
ሲሆኑ ፉልሃም፣ ክሪስታል ፓላስ እና ክዊንስ
ፓርክ ሬንጀርስ የለንደን መገለጫ የሆኑ ሌሎች
የሻምፒዮንሺፑ ታላላቅ ክለቦች ናቸው፡፡ እነዚህ
ሃያላን ክለቦች ብዙዎች ለነፍሳቸው ጥያቄ
ምላሽ ለመስጠት ባህር አቋርጠው እግሮቻቸው
የለንደንን ምድር እንዲረግጡ ምክንያት ሆነዋል፡
፡ የእግር ኳስ ፍቅር ካልዎት ምርጫዋ አንደኛ
ለንደን፣ ሁለተኛ ለንደን፣ ሶስተኛ ለንደን ነው፡
፡ ለንደንም እጆቿን ዘርግታ ትቀበልዎታለች፡
፡ በለንደን ነፍስዎ ሀሴት ያደርጋል፡፡ በለንደን
በህይወት ዘመንዎ የማይረሳ ጊዜን የሚያሳልፉ
በመሆንዎ ለንደኖች “A Bad Day of London
is Still Better Than a Good Any Where
Else” (በለንደን መጥፎ የሚባለው ቀን ከሌላው
አገር ጥሩ የሚባለው ቀን የተሻለ ነው) የሚሉት
ወደው አለመሆኑን አይቼ አረጋግጫለሁ፡፡
ወደ ለንደን የተጓዝኩት በተዘበራረቀ
ስሜት ውስጥ ሆኜ ነበር፡፡ በሽብር ስጋትና
በሚደርሱባት ተደጋጋሚ አደጋዎች፤
እንዲሁም ከአውሮፓ ለመነጠል በምታደርገው
እንቅስቃሴ ኢኮኖሚዋ በተነቃነቀበት ሰዓት
ውስጥ ቢሆንም ለንደን ፊቷን አልነሳችኝም፤
እጆቿን ዘግርታ ተቀብላኛለች፡፡ በህይወት ዘመኔ
ዳግም የማላገኘውን እርካታም አጎናፅፋኛለች፡፡
የማትጠገበዋን ለንደን ሳላጣጥማት መምጣቴ
ሌላ የጉዞ ፕላን አድርጌ ዳግም እንድጎበኛት
ፍቅርዋ እያስገደደኝ ነው፡፡
በአትሌቲክስ ቡድናችን
ውስጥ የባልና የአሰልጣኝነት
ሚናዎች መደበላለቃቸው ሌላው
የውጤታችን ማነቆ
እንደዘንድሮው የአትሌቲክስ ቡድን ሁሉም
ነገር የተደበላለቀበት፤ ማን…አሰልጣኝ…?ማን…
ሰልጣኝ…?
ማን…ታዣዥ…?ማን…
አዣዥ…?እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ የሆነ
ጊዜ አላጋጠመኝም፤ሁሉም ነገሩ ድብልቅልቁ
ወጥቷል።ባልና አሰልጣኝነት የተደበላለቀበት
የውድድር ጊዜ ቢኖር የሪዬን ኦሎምፒክ
ጨምሮ ይሄ የአሁኑ ነው ብል አላጋነንኩም፡
፡ በለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባልና
አሰልጣኝነት ተደበላልቀው በፌዴሬሽኑ
አውቅና የተሰጣቸው፣ የአሰልጣኝነት
ማዕረግን የደፉ አሰልጣኞች ዳር ሆነው
ሲመለከቱ አስተውዬ አዝኛለሁ፡፡
አትሌቶች በፌዴሬሽኑ በተመደበላቸው
አሰልጣኝ ከመሰልጠን ይልቅ በባላቸው
መሰልጠንን የመጀመሪያው ምርጫቸው
አድርገው በባሎቻቸው ሲሰለጥኑ
በአትሌቲክስ ቡድናችን መመልከት አሁን
አሁን እንግዳ ነገር አይደለም፡፡አትሌቶች
በባሎቻቸው ሰልጥነው ውጤት ካመጡ
ምን ችግር አለው…? ዋናው ውጤቱ
ነው የሚል የመከራከሪያ ሃሳብ ይዘው
ብቅ የሚሉ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ፤
ትልቁ ችግር ግን ይሄ አይደለም
ፌዴሬሽኑ አሰልጣኞችን በየፊልዱ
ለምን መደበ…? የማያሰለጥኑ፤
አትሌቶችን የማይመሩ ከሆነ ለምን ይሄ
ሁሉ ውጪ ወጥቶ ባህር አቋርጠው
ይሄዳሉ? ውጤት ሲገኝስ የሚሸለመው
ማን ነው..? ለተገኘው ውጤት
ይገባዋል ተብሉ እውቅና የሚሰጠው
ለማን ነው..? ለአሰልጣኙ..? ወይስ
ለባልዬው? የሚለው ግልፅ የሆነ
ምላሽን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ውጪ
አንድን አትሌት ለማሰልጠን ከፍተኛ
ወጪ አውጥቶ እውቀት መገብየት፣
በትምህርት አቅምን ማሳደግ፣ በስልጠና
የልምድ ባለቤት መሆን ሳይሆን
አሰልጣኝ ለመሆን ለአንድ አትሌት
ባል መሆን ብቻ በቂ ነው ወደሚል
ድምዳሜ አይወሰድም ወይ…? የሚል የጠነከረ
ስጋት በውስጤ አለ፡፡ በለንደን ዓለም ሻምፒዮና
በ10 ሺህ እና 5ሺህ ሜትር በዋና አሰልጣኝነት
የተመደቡ አሰልጣኞች በተለይ አንድ ወርቅና
ብር ያገኘችውን አልማዝ አያናን ሲያሰለጥኑ
ወይም ሲመሩ አላስተዋልኩም፡፡ ከውድድር
በፊትም ሆነ በኃላ አልማዝና ገንጥሎ ሲያሰራም
ሆነ ሲመክር የነበረው ባለቤትዋ ሶሬሳ ነው፡፡
የአልማዝ አያና ባለቤት ከሪዮ ኦሎምፒክ ጀምሮ
የእሷ የትዳር አጋር ብቻ ሳይሆን አሰልጣኝም
ሆኖ ሲሰራ እየታየ በሌላ በኩል ፌደሬሽኑ
አልማዝ በምትሮጥበት ርቀት አሰልጣኝ
መድቧል፡፡ የአልማዝን ለማሳያ ያህል አነሳን
እንጂ ከባላቸው ውጪ አንሰለጥንም የሚሉ
አትሌቶች ቁጥራቸው እየበረከተ በፌዴሬሽኑ
በተመደበላቸው አሰልጣኝ ከማመን ይልቅ
በባሎቻቸው የመሰልጠን ፍላጎታቸው ከፍ እያለ
መምጣት ጀምሯል፡፡ በዚህ ጉዳይ ለንደን ላይ
ያነጋገርኳቸው የፌደሬሽኑ የቴክኒክ ክፍል ኃላፊ
የሆኑት አቶ ዱቤ ጁሎ የባሉችና የአሰልጣኞች
የተደበላላቀ አሰራር ችግር እንደፈጠረባቸው
አምነው በቀጣይ ባልነትንና አሰልጣኝነት
አደበላልቀው እንደማይሄዱና ጉዳዩ በህግ
ጭምር ማሰሪያ እንደሚበጅለት ቢገልፁም
ባለፈው ሳምንት ለአትሌቻችን በተደረገው
የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሰአርት ላይ ለአልማዝ
አያና ባለቤት ሶሬሳ የገንዘብ ሽልማት በማበርከት
አትሌቶች በባሎቻቸው መሰልጠን እንደሚችሉ
ዕውቅና መስጠት በሚመስል መልኩ ከአቶ ዱቤ
ጁሎ በተቃራኒው መቆማቸውን አረጋግጠዋል፡
፡ በቀጣይ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚደረገው
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተደበላለቀው
የባልና ሚስት አሰልጣኝነት ጉዳይ አንድ
እልባት ካላገኘና አንድ ቦታ ላይ ካልቆመ ሌላው
የውጤታችን ማነቆ ይሆናል የሚል ስጋት
እንዲኖረኝ የለንደን ቆይታዬ አሳይቶኛል፡፡
የቡድን አንድነትና ፍቅር
በአትሌቶችና በአሰልጣኞች
መካከል ያለመኖሩ ትዝብቴ
እግር ጥሎት የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ
ብሄራዊ ቡድን ቡድን ወደ አረፈበት ታዎር
ብሪጅ ስር ወደሚገኘው ጉማ ሆቴል ቢሄዱ
ይሄንን ሀቅ ማንም ሳይነግርዎ አረጋግጠው
ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ አዎን በአትሌቶቻችን
መካከል ፍቅር አንድነት የሚባለው ነገር
አለመኖሩና ግለኝነት መንገሱን ጉማ ሆቴል
በተመላለስኩበት ጊዜና በውድደር ወቅት አይቼ
አረጋግጫለሁ፡፡ የአትሌቲክሱ አዲሱ የበላይ
አዣዥ የሆነው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴና ሌሎች
የካቢኔ አባላት ቀደም ሲል ሰለ አትሌቶቻችን
አንድነትና በፍቅር መክነፍ ሲነግሩን የነበረው
ተረት ተረት ለመሆኑ የአትሌቶች ግንኙነት አፍ
አውጥቶ ይመሰክራል፡፡ ያለማጋነን ከሚነጋገሩት
አብረው ለውጤታማነት ከሚመካከሩት ይልቅ
በተናጥል የሚንቀሳቀሱ አትሌቶችን ማስተዋል
ያን ያህል ከባድ አይደለም፤ በአጭሩ ለአንድ
አገር የሚሮጡ ሳይሆን ለሌላ አገር የሚሮጡ
ግን “ኢትዮጵያ” የሚለውን ቱታ የለበሱ
አትሌቶች ነው የተመለከትኩት፤ በውድድር
ወቅትም ምንአልባት በወንዶች 5ሺህ ሜትር
ሞ.ፋራህን ለማሸነፉ ዮሜፍ ቀጀልቻና ሙክታር
ኢድሪስ የከፈሉትን መስዋዕት እንደ ቡድን
ስራ ለማሳያነት ካልወሰድነው በቀር የቡድን
ስራ የሚባል ነበር በወንዶችም በሴቶችም ላይ
አልታየም፡፡ በእርግጥ አትሌቲክስ በባህሪው
በግል ጥረት ማሸነፉን የሚጠይቅ፣ የእኔ እበልጥ
ስሜትን የሚፈጥር፣ ህይወትን የሚለውጥ
ገንዘብ የሚገኝበት ውድድር በመሆኑ አትሌቶች
በአንድነት በፍቅር ከንፈው ማየት የማይጠበቅ
እንደሆነ ባልክድም ቢያንስ የለንደኑ አይነት
በዓለም ሻምፒዮና ወቅት ትልቁን ምስል
በማየት አገርን በማስቀደም ከልዩነት ወደ
አንድነት መምጣት በሚቻልበት ዙሪያ ቢስራ
መልካም ነው የሚል እምነቱ አለኝ፡፡ በለንደን
ቆይታዬ እንደታዘብኩት አትሌቶቻችን የተዋደዱ
የሚመስሉ ግን የተጣሉ አንድ መስለው
የተለያዩ ሆነው በአይኔ በብረቱ አይቼ የታዘብኩ
ሲሆን ጊዜ ወስደን ወንበር ስበን ቁጭ በማለት
ልንመክርባቸው የሚገቡ የአትሌቲክሳችን
አብሮን የኖረ ግን ውጤት የሸፈነው አደጋ
መሆኑን የለንደኑ የአለም ሻምፒዮና በግልፅ
አሳይቶኛል፡፡
ሁሌም ሲታወስ የሚኖረው የዩዜይን
ቦልትና የሞ ፋራህ ሽኝት
እውቁ ቦክሰኛ መሐመድ አሊ ጓንቱን
በመስቀያው ቀን እ.ኤ.አ በ1981 ዓ.ም ባደረገው
የመጨረሻ የስንብት ፍልሚያው ገጠመኝ
ከዩዜይን ቦልትና ከሞ ፋራህ ጋር ይመሳሰላል::
ለበርካታ ዓመታት የሪንግ ንጉስነቱን አረጋግጦ
የቆየው መሃመድ አሊ እ.ኤ.አ በ1981 ዓ.ም
ከትሬቨር ቤርዚክ ጋር የሚያደርገውን የቦክስ
ዘመኑ የመጨረሻ ፍልሚያውን አሸንፎ በድል
አድራጊነት ጓንቱን ይሰቅላል ተብሎ ሲጠበቅ
መሐመድ አሊ ባልተገመተና ባልተጠበቀ
ሁኔታ በትሬቨር ቤርዚክ ቡጢ ሪንግ ውስጥ
ተዘርሮ የቦክሱን አለም ለአንዴና ለመጨረሻ
ጊዜ በሽንፈት ተሰናብቷል፡፡ በለንደኑ የአለም
አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ዩዜይን ቦልትና ሞ
ፋራህም የገጠማቸው ነገር ከመሐመድ አሊ
ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱም የመጨረሻውን
ውድደራቸውን የቋጩት ሁሌም በመጥፍነት
ሲያስታውሱት በሚኖሩት ሽንፈት ነው፡፡
ከ2017ቱ የለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ
ሻምፒዮና በመጥፎነት የሚነሳ ወይም የሚታወስ
ነገር ካለ የእነዚህ የሁለቱ የዓለማችን ፈጣን እግር
ባለቤትና የውድድሮች ድምቀት (ከለር) የሆነው
ዩዜይን ቦልትና ምንም አንኳን የአገራችንን የርቀቱን
የበላይነት በመንጠቁ ቢያበሳጨኝም ከ2011ዱ
የዴጉ የዓለም ሻምፒዮና ጀምሮ እስከለንደኑ
የዓለም ሻምፒዮና በውጤቱ ንጉስነቱን ያወጀው
ትውልደ ሶማሊያዊው ሞ ፋራህ ከትራክ ውድድር
ጡረታ መውጣታቸው ለአትሌቲክሱ ዓለም
ትልቅ ሃዘን ሆኖ አልፏል፡፡ የሁለቱ አትሌቶች
ስንብት ከአትሌቲክስ ውድድር በላይ ትኩረትን
የሳበ የለንደኑን ሻምፒዮና የትኬት ሽያጭ ቁጥር
እንዲያሻቅብ፤ ሪከርድ እንዲሰብሩ ምክንያት
መሆኑን ታዝቤያለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ የዩዜይን
ቦልትን ፈጣን እግሮችን የሞ ፋራህ የ5
ሺህ እና የ10ሺህ ሜትር የትራክ አስደናቂ
ድልን በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና
ላይ ለማየት ባለመታደላችን አትሌቲክሱ
ግማሽ አካሉን ያጣ ያህል ቢወሰድም የዓለም
አትሌቲክስ ማህፀን መኻን አይደለምና ከዚህ
በፊት ብዙ ጀግኖችን አጥተን ብዙ አዳዲስ
ጀግኖችን እንዳሳየን ሁሉ በቀጣይም አዳዲስ
ጀግኖች እንደሚወለዱ ተስፋችን የበዛ
ነው፤ በአሸናፊነታቸው ብቻ ሳይሆን ከድል
በኋላ በሚያሳያቸው ለየት ያሉ የደስታ
አገላለፆች የውድደር ሜዳዎች ድምቀቶች
የሆኑትን አንፀባራቂ አትሌቶች ዓለም ሁሉ
ከመቀመጫው ተነስቶ ባርኔጣውን ከፍ
አድርጎ ለእስከዛሬው ድላቸውና ስኬታቸው
እውቅና ሰጥቶ በርካቶች ወደ አትሌቴክሱ
እንዲሳቡ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ
አመስግኖ በእንባ ጭምር በተሸኙበት መድረክ
ላይ መገኘቴና የዚህ ታሪክ አካል መሆኔን
እንደሁም ሞ ፋራህ በሙክታር እድሪስ
መራራውን የመጨረሻ ሽንፈት ከተጎነጨ
በኋላ ለደቂቃዎችም ቢሆን በአካል ማግኘቴና
ስለኢትዮጵያና ሰለኢትዮጵያውያን ጀግኖች
አትሌቶች ማለትም ስለእነ ሃይሌና ቀነኒሳ
በቀለ ያለው ክብርና አድናቆትን በቅርበት
በማውራት የማስታወሻ ፎቶ የምነሳበትን
እድሉን ሞ ፋራህ ሰለፈጠረልኝ እንዲሁም
ቀደም ሲል በቴሌቭዥን መስኮት ብቻ
የማውቀን የሰማይ ስባሪ የሚያክለውን ዩዜይን
ቦልትን በቅርብት የማየትና ፕሬስ ኮንፈረንስ
ላይ ከሩጫው ከተገለልክ በኃላ በቀጣይ ምን
አስበኃል በሚል ላቀረብኩለት ጥያቄ “አሁን
አላውቀውም፤በአሰልጣኝነት ልምጣ ወይም
በሌላ ወደፊት የምናየው ይሆናል”በሚል
ከአንደበቱ በወጡ ቃላቶች ምላሽ ማግኘቴ
የለንደን ቆይታዩን ይበልጥ ጣፋጭና የማይረሳ
እንዲሆን ካደረጉት ነገሮች በግንባር ቀደምትነት
ይጠቀሳል፡፡
(ይቀጥላል)